/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የተለያየ ክስ ተመስርቶባቸው በፌዴራል እስር ቤቶች የሚገኙ 304 የሚሆኑ የህሊና እስረኞች ዛሬ መፈታታቸው ተገልጿል። እስረኞቹ የተፈቱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ በይቅርታ እንዲፈቱ ከወሰኑ በሗላ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።
በፕሬዚዳንቱ እንዲፈቱ ይቅርታ የተደረገላቸው እስረኞች ከሞት እስከ እድሜ ልክ የተፈረደባቸው እንደነበሩ ታውቋል። ከተፈቱት መካከልም 289 “በሽብርተኝነት” ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው እንደነበሩ ጠ/አ/ህግ ጠቁሟል።
ዛሬ ከተፈቱት መካከል ከዓመታት በፊት በስደት ከሚኖርበት ኬንያ ታፍኖ ተወስዶ የሞት ፍርደኛ የነበረው ኢንጂኒየር መስፍን አበበ ይገኝበታል። በአርበኞች ግንቦት ሰባት ተከሰው የነበሩትና እጅግ ዘግናኝ ሰቆቃ ከተፈፀመባቸው መካከል አበበ ካሴና የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ አባል የነበረው ጥላሁን አበጀ መፈታታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
እስረኞቹ ከዛሬ ጀምሮ ከቃሊቲ እስር ቤት እየወጡ ሲሆን በእስር ቤት ባጋጠማቸው ድብደባና አያያዝ ምክንያት የአካል ጉዳትና የጤና ዕክል ያለባቸው እንዳሉም ታውቋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በክልል ያሉ እስረኞችም ከሰኔ 11/2010 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚፈቱም ተጠቁሟል። የወያኔ የደህንነት ሰንሰለት በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ብቻ በተለያየ ጊዜ ያሰራቸውን ዜጎች በህዝብ ትግል ተገዶ እየፈታ ቢሆንም አሁንም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች በየማጎሪያ ቤቱ ተዘግቶባቸው እንደሚገኙ ይታወቃል።