/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ከኦሮሚያ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች በአፋጣኝ ወደ ቦታቸው እንደሚመለሱ የክልሉ ር/መስተዳድር ለማ መገርሳ ተናገሩ። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ለአማራ ቴሌዥን ዛሬ በሰጡት አስተያየት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ወደ ቦታቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ለማ መገርሳ እንደገለፁት “ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ተፈጥሮ በነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት የሰጉ የተወሰኑ የአማራ ተወላጆች መፈናቀላቸውንና ከዚያም በሗላ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ እንዲሁም አንዳንድ አጥፊ ሀይሎችም በፈጠሩት ችግር የተወሰኑ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ይህም አብሮነታችንና የህዝቡን ትስስር የሚጎዳ በመሆኑ በአፋጣኝ ለማስተካከል አስፋጊውን እርምጃ እየወሰድን ነው” ብለዋል።
ዜጎችን በማፋናቀልና ለችግሩ በአፋጣኝ ምላሽ ያልሰጡ የታች የኦህዴድ አመራሮችም ባለፈው ሳምንት በአዳማ በተካሄደው የኦህዴድ 8ኛ ድርጅታዊ ኮንፈረንስ የማያዳግም እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ተገልጿል።
የኦሮምያ ክልል ኮሙንኬሽን ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ከክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ተፈናቅለው ባህር ዳር ከሚገኙት የአማራ ተወላጆች ጋር ዛሬ ማምሻውን ውይይት እያካሄዱ ነው።