ጠ/ትር አብይ አህመድ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ደቡብ...

ጠ/ትር አብይ አህመድ ከህብረተሰቡ ጋር ለመወያየት በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ደቡብ ክልል እንደሚያቀኑ ተገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ዛሬ ማምሻውን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መልዕክት አስተላልፈዋል። በመግለጫቸውም በሀገሪቱ አንዳንድ አከባቢዎች በተለይም ደግሞ በሀዋሳና ወላይታ ሶዶ የተነሱትን ግጭቶች ከህብረተሰቡ ጋር በመወያየት ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ስፍራው እንደሚያቀኑ ገልፀዋል፡፡

እስከዚያ ድረስ ግን በሰላምና ፍቅር የምትታወቀው የትንሿ ኢትዮጵያ የደቡብ ክልል ነዋሪዎች፣ የአከባቢው ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ለአካባቢያቸው ሰላም በጋራ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡ የጸጥታ አካላትም ህብረተሰቡን ባሳተፈና እና ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ የየአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክልል እንሁን በሚል ለሚነሱ ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ስርዓት ያስቀመጠ በመሆኑ ሁሉንም ነገር በሰላም መጠየቅና ማስተናገድ እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡ከወሰን ጋር በተያያዘ በተለያዩ አከባቢዎች የሚነሱ ጥያቄዎችን በጥናት መመለስ ይቻል ዘንድ ይህንን የሚከታተል ኮሚሽን ለማቋቋም መንግስት እያሰበ መሆኑንም ዶ/ር አብይ ገልጸዋል፡፡

ይህ ኮሚሽን ከየአከባቢው የሚነሱ ጥያቄዎችን በመቀበል ስር ነቀል መፍትሔ እንደሚሰጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

LEAVE A REPLY