ኢትዮጵያዊነት የብዙ ንፁህና ክቡር እሴቶቻችን ድምር ውጤት ነው። አንዱ ታዲያ በበጎውም በክፉውም በጋራ መቆማችንና ይህንኑም “ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው…” ብለን ማጠንከራችን ጭምር ነው። ይህንን ብዬ ወደዛሬው ፍሬ ሃሳቤ እንድገባ ፍቀዱልኝ።
ወንድማችን ካፕቴን በሃይሉ ገብሬ ከ14 አስከፊ የእስር ዓመታት በሁዋላ ቤተሰቦቹን ተቀላቀለ። እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!
በጣም ከሚቆጩኝ ነገሮች አንዱ ወላጅ እናቱ ይህችን ቀን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር በደስታ ያለማሳለፋቸው ነው። ለ12 ዓመታት በየሳምንቱ እየመጡ ይጠይቁት ነበር። በዝዋይ እስር ቤት የምንገኘውን ሁሉ “እኔን ልጆቼ፤ አይዟችሁ ማርያም አለችላችሁ!” ይሉን ነበር። በእናትና ልጅ መካከል የነበረው ፍቅርና መተሳሰብ እንዴት እንደነበረ መግለጹ ግን ይከብዳል።… የሚያሳዝነው ያልጠበቅነው አደጋ ደረሰ። እናት በድንገት ታመሙ። መንቀሳቀስም አቃታቸው።
የበለጠ የሚያሳዝነው ግን እኒህ መንቀሳቀስ ያልቻሉ እናት ልጃቸውን በጋሪ ገብተው ለማየት የእስር ቤቱን ሃላፊዎች ቢጠይቁም “ጋሪ መግባት አይችልም” በሚል ሰንካላ ሰበብ ተከልክለው “ልጄ ልጄ!” እንዳሉ፣ እንዳለቀሱ አለፉ። እህት የእናትን ቦታ ተክታ እስከዛሬ ብዙ ባክናለች። ቀናት አልፈው፤ በእግዚአብሔር ፈቃድና በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ዛሬ ወንድማችን ካፕቴን በሃይሉና በርካቶች የነፃነትን አየር ተንፍሰናል። (አሁንም በመሰል ሁኔታ ውስጥ በእስር ላይ ያሉና ዛሬ ነገ እያልን ፍቻቸውን የምንጠብቀው የእናት ኢትዮጵያ ልጆች መኖራቸው ሳይረሳ!)
ከ14 ዓመት አስከፊ እስር በሁዋላ ያ በኢትዮጵያውያን ፍቅር ተለክፎ ከኑሮዬ ኑሯችሁ፣ ከምቾቴ ክብራችሁ ያለን የትናንቱ የ26 ዓመት ወጣት የዛሬው የ40 ዓመት ጎልማሳ ከፍች ማግስት ህክምናን ጨምሮ ለተለያዩ ነገሮች የኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ድጋፍ የሚያስፈልገው መሆኑን በመረዳት የባንክ አካውንት ተከፍቶለታል። አጋርነታችንን እናሳይ። (በሃይሉ ገብሬ acc no 1000062213756, ኦሮሚያ ሕ/ሥራ ባንክ)#tel 0910785155#
ኢትዮጵያዊነት ደምቆና ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ እግዚአብሔርም ያስበናል!