ባንዲራችን ይፈታ፦ ስለት እንሣል /ዶ/ር ዘላለም እሸቴ/

ባንዲራችን ይፈታ፦ ስለት እንሣል /ዶ/ር ዘላለም እሸቴ/

አዲሱን የፍቅርና የመደመር ጉዞ በአብሮነት ስንያያዘው፥ አንድነታችንን የሚያንፀባርቀው ባንዲራችን ግን በሁለት ጎራ ተከፍሎ ያሳብቅብናል። ይህንን ችግር ለመፍታት የባንዲራችንን ጉዳይ በሦስትዮሽ ከፍለን ማየት ያስፈልገናል። ምክንያቱም የባንዲራችን ምስጢር ምጡቅ ስለሆነ እንዲህ በአንድ ጊዜ ምንነቱ ላይ መድረስ አንችልምና።

የባንዲራችንን ረቂቅ ምስጢር ከኢትዮጵያዊነት ማንነታችን ረቂቅ ምስጢር ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ በየረድፉ በሂደት የሚገለፀውን የባንዲራችንን ክብር እንመልከትና መግባባት ላይ እንድረስ።

 መነሻ ባንዲራችን፦ የዛሬው ባንዲራ የታሪካችን ምልክት 

ታሪክን ተሻግሮ የመጣው አረንጓዴ ብጫ ቀዩ ባንዲራ ነው። የቀድሞ መሪዎቻችን ስማቸውን የሚወክል ፊደል በዚሁ ባንዲራ ላይ ያስቀምጡ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። በቅርቡም ጃንሆይ ዘውድ የተጫነበትን አንበሳ አስቀምጠውበት ነበር። ኮሎኔል መንግስቱም የኮሚኒስቶቹን ምልክት አምጥተውብደበላልቆብን ነበር። የትላንትናውም ኢሕአዴግ አሁን የሚታየውን ኮከብ ጭነውልናል። አርማው ይቀያየር እንጂ፤ታሪካዊው አረንጓዴ ብጫ ቀዩ መሰረታዊ ባንዲራ ምንም ይሁን ምን ትውልድን ተሻግሮ በሁሉም ዘንድ ምንነቱ ሳይቀየር ዛሬ ደረሰ። አንድነታችንን ይህን ነጠላ ባንዲራ (የነገስታት መገለጫ የሆኑትን ምልክቶችን ሁሉ ትተን)  እንደ መነሻ ባንዲራ ዛሬ ብንጠቀም መልካም መግባባት ይሆንልናል።

 መድረሻ ባንዲራችን፦ የነገው ባንዲራ የፍሬያችን ምልክት

 ከዚህ በፊት እንደሆነው ትውልድ የማይሻገር ምልክት ከማድረግ ስህተት ለመጠበቅ፤ ለወደፊቱ በባንዲራው ላይ ለውጥ የማምጣት ሂደት ከተለመደው ለየት ማለት አለበት። 1ኛ/ ይህን ነጠላ ባንዲራችን (ምንም ምልክት የሌለበት) መለወጥ ከመሞከር በፊት በቅድሚያ ትውልድ የሚሻገር አዲስ ታሪክ መስራት አለብን። ወጡ ሳይወጠወጥ እስክምባው ላይ ቂጥ እንዳይሆንብን፤ ባንዲራውን ሳንነካ መጀመሪያ ታሪካችንን በበጎነት እንቀይር። ይህም አዲሱ ታሪካችን ትውልድ እስኪሻገር እንጠብቅና ፍሬውን እንይ። ያኔ አዲሱን ታሪካችንን የሚመጥን ምልክት ባንዲራችን ላይ እናድርግ ብንል ያምርብናል። 2ኛ/ ባንዲራ ለመቀየር በሕዝብ ተሳታፊነትና በሪፈረንደም እጅግ አብላጫ በሆነ ድምፅ ይከናወን ዘንድ ይገባል። እንኳን በዲሞክራሲ ያልተመረጠ መንግስት ይቅርና፤ በዲሞክራሲም የተመረጠ መንግስት ቢመጣ ይህንን ታላቅ ባንዲራ የመቀየር ላፊነት መውሰድ ያለበት መላው ሕዝብ ብቻ ነው።

ስለት እንሣል። ዛሬ ተአምራዊ ጉዞ ያስጀመረን አምላክ እንዲሁ ተዐምሩ እየበዛልን ቢቀጥልስ? ለዘመናት የምንሰማው “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” የሚለው ተስፋ እውነት ሆኖ የጀመርነው የፍቅርና የይቅርታ መንገድ የተቃና ቢሆንስ? የምንመኘው ዲሞክራሲ ነገ ዕውን መሆኑ ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያኑ የሚቀኑበት ቢሆንስ? ፍቅራችንና አንድነታችን ጎልብቶ፤ ዘረኝነት በወንድማማችነት ተተክቶ፤ በአምላክ ስር ያለን አንድ ቤተሰብ ሆነን ብንገለጥስ? ፀሎታችን ተሰምቶ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ቢባርካትና የሁሉ ዓይን ማረፊያ ቢያደርጋትስ? በውኑ ያኔ የረዳንን አምላክ የሚገልጥ ምልክት በባንዲራችን ላይ እናደርግ ይሆንን?

ኢትዮጵያ ከጥሪዋ ጋር የሚሄድ አርማ (የተዘረጉ እጆች)በባንዲራችን ላይ የሚያርፍበት ዘመን ይምጣልን የሚል ምኞት አለኝ። ይህ ዓርማ ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ቢቀመጥ ሊሰጠን ያለውን በረከት በጥቂቱ እንመልከት።

ይህ ዓርማ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲባርካት ለምነን በረከቱን ለመቀበላችን ምስክር ይሆናል።
ይህ ዓርትዮጵያ የተስፋው ቃል ሕዝብ እንደሆነ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነት ያንፀባርቃል።
ይህ ዓርማ ከማናቸውም መንግሥታት ጋር ስለማይወግን ዘላቂነት ይኖረዋል።
ይህ ዓርማ ፈጣሪ ለሕዝቡ ያለውን መልካም ሃሳብ ያሳያልስለዚህም ከአምላክ የተሰጠን ስጦታ ነው።
ይህ ዓርማ ዎች ዘመን ታሪክ ያለውና፤ ታሪካዊ በሆነው ባንዲራችን ላይ ታሪካዊ ለሆነችው አገራችን ምቹ ነው።
ይህ ዓርማ ከማናቸውም ሃይማኖት ምልክቶች ስለማይያያዝ፤ሃይማኖት እንደማይከፋፍለን ምልክት ይሆንልናል።
ይህ ዓርማ በፊት ለአፍሪካ ኩራት የነበረውን ባንዲራችንን ለዛሬ የአፍሪካ ተስፋ በማድረግ ይበልጥ ያከብረዋል።
ይህ ዓርማ የየግል ሃይማኖት ነፃነት ተጠብቆ፤ የፈጣሪ ረድሄትን እንደ አንድ ሕዝብ ተያይዘን መጠየቅ ያስችለናል።    
ይህ ዓርማ ኢትዮጵያ ገፅታ ለውጦ የዓለም ሞዴል ሲያረጋት ለፈጣሪ ታማኝነትና ታላቅነት መታሰቢያ ይሆናል።

 ስጦታ ባንዲራችን፦ የከነገ ወዲያው ባንዲራችን የአፍሪካ ተስፋ ምልክት

 ራዕያችን እየሰፋ ነው። መሪያችን የአፍሪካ ድንበር የውጭ ሰዎች የሰጡን እንጂ አፍሪካ አንድ ሕዝብ ነን እያሉ ነው። ራዕያቸው ሰምሮላቸው የምስራቅ አፍሪካ ቀንድ ብሎም መላው አፍሪካ አንድ ስትሆን፤ የአፍሪካ ባንዲራ ምን ይሆን እንደሆነ መገመት አያስቸግርም። ትላንት በአድዋ የተሰራው የአፍሪካ ድል ለብዙ አፍሪካ ሀገሮች የኢዮጵያን ባንዲራ ቀለሞች በኩራት እንዲዋሱ አድሮጓቸዋል። ትላንት በደም የተሰራው የአድዋ ታሪክ ይበልጥ የሚያደምቅ፤ ዛሬ ደግሞ በፍቅር እየተሰራ ያለው የዶ/ር አብይ ታሪክ ለዳግመኛ የአፍሪካ ድል እያዘጋጀን ነው። ኢትዮጵያ ሞዴል መሆንን ከተያያዘችው፤ የአፍሪካ ተስፋ ምልክት መሆኗ አይቀሬ ነው። ያኔ የአፍሪካ ሕዝብ ባንዲራችንን በስጦታ እንድንሰጣቸው ይጠይቁናል ብዬ እገምታለሁ። አርቲስቱ ቴዲ አፍሮ ባንዲራችን የቃል ኪዳን ምልክትነቱን ሊያሳየን፤ ባንዲራችን በሰማይ ላይ ታየ ብሎን የለ? ታዲያ የአምላክ እጅ የገባበት ይህ ባንዲራ ሊያመጣ ያለው በረከት ምጡቅነት እጅግ የጠለቀ ነው።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ፤ ይባርካታልም።

ኢሜል፦ ethioStudy@gmail.com

LEAVE A REPLY