/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል“ኦጋዴን” በተባለ እስር ቤት የማረሚያ ቤት ሀላፊዎችና የፀጥታ ሀይል አባላት ሰዎችን በዘፈቀደ እያሰሩ ለበርካታ ለዓመታት ማሰቃየታቸውን የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድን አስታወቀ።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት እንደገለጸው፤ ኦጋዴን በተባለ እስር ቤት የሚታሰሩ ኢትዮጵያዊያን በጨማ ቤት እንደሚታሰሩ፣ በኤሌክትሪክ የማሰቃየት ተግባር እንደሚፈፀምባቸው፣ የአካል መጉደል እንደሚደርስባቸውና በቂ ምግብ እንደማይሰጣቸው ከዚህ ቀደም በእስር ቤቱ ያሳለፉ ሰዎችን ዋቢ በማድረግ ገልጿል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ያነጋገረው አብዱልሰላም(የ28 ዓመት ወጣት) ለሶስት ዓመታት በኦጋዴን እስር ቤት ሲያሳልፍ አብዛኛውን ጊዜ በጭለማ ክፍል ውስጥ እንዲቆይ መደረጉን፤ በብልቱ ፍሬዎች ላይ በኤሌክትሪክ ማሰቃየት መፈፀሙንና በቂ ምግብ ይቀርብለት እንዳልነበር እንዲሁም በዚያው በኦጋዴን እስር ቤት የነበረች ባለቤቱ በጸጥታ ሀይሎች ተደፍራ ልጅ መውለዷን አስረድቷል።
ሂዩማን ራይትስ ዎች ይህን ሪፖርት ሲሰራ ከአካባቢው ፀጥታ አባላት፣ መንግስት ባለስልጣናት፣ 70 የቀድሞ እስረኞችን ጨምሮ 100 ሰዎችን ማነጋገሩን አስታውቋል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኦጋዴን እየተፈጸመ ያለውን አሰቃቂ ወንጀል የምርመራ ቡድን አቋቁመው እንዲያስጠኑትና ጥፋተኞችም በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።