ገዱ አንዳርጋቸው በትናንናው ዕለት እነ በረከትንና ትህነግን ሲከላከል ትችት አስተናግዷል። አንዳንዶች ገዱ ያሰበው የማይመስል ሩቅ የፖለቲካ ትንተና አንስተው ሊከላከሉት ሞክረዋል። ገዱን አትውቀሱት የሚሉ አካላት አስተያየት ለለውጡ ካላቸው ቀናኢነት እንደሆነ ይገባኛል። ሆኖም:_
~ገዱ አንዳርጋቸው ራሱ ባህርዳር ላይ በተደረገው ሰልፍ “የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች……”እግር በእግር እየተለተሉ አላሰሩት እንዳሉ ገልፆ ነበር። ትናንት ሌላ ቋንቋ ተናገረ።
~ትናንት ገዱ ሰልፉ ላይ “ይደገም” ተብሎ ከደገመው ለምን እንዳፈነገጠ ግልፅ አይደለም። ምን አልባት በአማራ ክልል ከተሞች “በረከት መጣ” እየተባለ ሲታደን “እናንተ በምትናገሩት ነው እንዲህ የተጠላነው” ተብለው ከ”አሮጌው ዘመን ቁማርተኞች” ወቀሳ ደርሶባቸው ይሆናል። በረከት ክስ አይነት ወቀሳ ነው የሚያቀርበው። በየ ሰልፉ የተዘለፉት የትህነግ ሰዎችም “አሰደባችሁን” ብለው ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ከእጃቸው እርዝመት አንፃር በእነ ገዱ ላይ ምን እንደያዙባቸው ግልፅ አይደለም
~እውነታው ከሆነ ግን ሌላ ነው። እነ ዝማም ከእነ ገዱ ጋር ከመስራት ይልቅ ለትህነግ ወሬ ማቀበል ይቀናቸዋል። ይህን ደግሞ እነ ገዱ በምሬት እንደሚያወሩ በቅርብ የሚያውቁ በግልፅ የሚናገሩት ነው። ትህነግ ብአዴንን እንደፈለገ እየሾረው፣ አላሰራ ብሎት እነ ገዱ ግን ለእሱ ይከራከራሉ!
~እነ ገዱ መማር አይፈልጉም እንጅ መማር ቢፈልጉ የእነ አብይን ያህል ሞዴል ሊኖራቸው አይችልም ነበር። እነ አብይ (ቲም ለማ) “ህዝበኛ” እየተባሉ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል። በትህነግ ሰፈር። ይህን የተባሉት ከምንም አልነበረም። ከሕዝብ የሚያቀራርባቸውን ስራ ስለሰሩ ነው። ትህነግን ከሕዝብ ለመነጠል ስለጣሩ ነው። ለአብነት ያህል ትህነግ ከኦሮሚያ የሚዘርፋቸውን በማጋለጥ፣ ሲያጋልጡም መታወቂያ ሳይቀር እያሳዩ ነው ወደ ሕዝብ ልብ የገቡት። ይህ ሂደት “የቀን ጅብ” የሚል የግልፅ ፍረጃ አድርሷቸዋል። ይህ ትህነግን ከሕዝብ ለመነጠል የተጠቀሙበት የግልፅነት መንገድ እዚህ አድርሷቸዋል። እነ ዶክተር አብይ ለስልጣን የበቁት፣ ይህን የመሰለ ድጋፍ ያገኙት የትህነግ/ኢህአዴግን ገመና በማጋለጥና ከሕዝብ በመነጠል፣ በአንፃሩ ራሳቸውን ወደ ሕዝብ ረድፍ በማስጠጋት እንጅ ትህነግን በመከላከል አልነበረም።
~እነ ዶክተር አብይ የትህነግ ወዳጅ የሆነውንና በቀደም በሰማነው መንገድ ያን ሰፈር ያወግዛል ተብሎ ያልተጠበቀውን አብዲን እንኳ በትህነግ ሰፈር ማዝመት ችለዋል። በእርግጥ አካሄዳቸው ለየቅል መሆኑን የሚያሳየው ኢህዴድ የቆዩትን ፖለቲከኞች በቀላሉ ገሸሽ ሲያደርግ፣ ልሙጥሙጡ ብአዴን ዝማም የተባለች ወሬ አቀባይን ከቢሮው ማባረር አልቻለም። አቶ አለምነው መኮንን እንኳ ዶክተር አብይ ውለታ ውሎላቸው እንጅ በዚህ እንቅልፋም ፖለቲካቸው መቼም አያሸሹትም ነበር።
~እነ ዶክተር አብይ በኦሮሚያ፣ በአጠቃላይ እንደ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ትህነግ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ነን” የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ጋር ለመነጠል የሚያስችል ንግግር አድርጓል ተብሎ ለቀናት የተናደዱበትን የቤት ስራ ሰጥቷቸዋል። ትህነግን የራሱ ሕዝብ ድረስ እንዲደበቅ መከላከል ሳይሆን የራሴ የሚለው ሕዝብ ድረስ ዘልቀው የቤት ስራ ሰጥተዋል። በዚህም ምክንያት ወደ ሕዝብ ልብ ለመግባት፣ ትህነግንም ለማዳከም ጥረዋል።
~ እነ ክንፈ ዳኘው፣ እነ ተክለ ብርሃን፣ እነ ሳሞራና ጌታቸው እነ አብይ የሕዝብ ጥግ ይዘው፣ እነሱን ደግሞ ልክ ልካቸው እየተናገሩ አርቀዋቸዋል። በተቃራኒው እነ ገዱ አንዳርጋቸው በሕዝብ ንቃትና እንደ አጠቃላይ በተፈጠረው ፖለቲካ ምህዳር አንቅሮ የተፋቸውን አካላት ነፍስ እንዲዘሩ እየሰሩ ነው። እየተከላከሉላቸው ነው። እነ አብይ ስር ሆኖ፣ እነ አብይ የሕዝብ ጥግ ይዘው፣ የማይፈልጓቸውን ግልፁን ተናግረው ጥግ ጥግ ሲያስይዙ እያየ አለመማር ግብዝነት ነው። ጭራሹን ሊያቅፈው የሚቋምጥን ሕዝብ ገፍቶ “የአሮጌው ዘመን ቁማተኞች” ስር ስር እየሄዱ እነዚህን ህዝብ ያሽቀነጠራቸው መከላከል ከቆየው የጉልትነት ፖለቲካ አለመማር ነው!
~እነ አብይም አይሳሳቱም ማለት አይደለም። ይሳሳታሉም። ለምሳሌ ያህል ዶክተር አብይ በወልቃይት ጉዳይ የተናገረው ስህተት ነበር። ይህን ስህተት ግን ያላቀደው የጎንደር ጉዞን ለማድረግ አስገድዶታል። ሕዝብ እንደጠላበት ሲያውቅ “ቆንጥጡኝ” ብሏል። በዚህ ትህነግ ተናዶበታል። በዚህ አላበቃም። የወልቃይት ኮሚቴ አባላት ያሉበትን ጨምሮ ሕዝብን በአዳራሽ አነጋግሯል። ትህነግ ይህን ተቃውሟል። ሕገ ወጥ ነት ነው ብሏል። ሕዝብ ተቀይሞኛል ያለው ዶክተር አብይ በዚህም አላበቃም። የወልቃይት ኮሚቴ አባላትን በግል ጠርቶ፣ ከወንበሩ ተነስቶ ይቅርታ ጠይቋቸዋል። በዚህም ትህነግ ሲቀየመው “እንደመራለን” እስከማለት የቻለለትን ሕዝብ ድጋፍ አግኝቷል። በእነዚህ መድረኮች ብአዴን ስር ስር ሲከተል ነበር። ከማጨብጨብ ያለፈ ቁም ነገሩን አልተማረበትም። ዶክተር አብይ ግን ከትህነግ ይልቅ ወደ ሕዝብ የሚያስጠጋውን ረድፍ ይዟል።
~ደግነቱ ገዱ ራሱ ተናግሮታል! “የአማራ ሕዝብ ለወደደው ማር፣ ለጠላው ደግሞ ኮሶ ነው።” ይህን ቃል ገዱ ይረሳዋል ተብሎ አይታሰብም። ድገመው ተብሎ ደግሞታልና! እነ በረከትን የጠላ ሕዝብ ምን እንዳደረጋቸው ታይቷል። አሉ በተባሉበት ሁሉ ያደረገው ተስተውሏል። በየ ሰልፉ ትህነግን እንዴት በግልፅ እንዳብጠለጠለ ተስተውሏል። እነዚህን አካላት ቢጠላቸው ኮሶ ሆኖባቸዋል። እነ ገዱን ገና ሚናቸውን በደንብ ሳይለዩም ማር የሆነላቸው ሕዝብ፣ ሕዝብ ከጠላው አካል ጎን ቆመው ሲከላከሉ ሲያይ ኮሶ እንደሚሆንባቸው ጥርጥር የለውም። ይህን እነ ገዱም የተናገሩት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ይናገሩታል እንጅ አይተገብሩትም! ክፉ አመል ክፉ ነው። አይለቅም። ከእነ ዶክተር አብይ ከመማር ይልቅ የትህነግን ሎሌነት ይስባቸዋል!