/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ረፋድ አካባቢ አዲስ አበባ ሲደርሱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የከተማዋና አካባቢው ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በብሔራዊ ቤተመንግስት ለክብራቸው በተዘጋጀ የምሳ ግብዣ ላይ አጭር ንግግርም አድርገዋል። በትግርኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር “ዛሬ ታሪካዊ ቀን ነው፤ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያና ኤርትራ አንድ ህዝብ ናቸው፤ ፍቅራችን የእውነትና ከልብ ነው፡… ለተደረገልን ደማቅ አቀባበልና መስተንግዶ እናመሰግናለን” ብለዋል። ፕሬዚዳንቱ ነገ በአማርኛ ቋንቋ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድም በበኩላቸው “ለዚህ ህዝብ 24 ሰዓት ብንሰራለትና ብናገለግለው የሚያንስበት ነው” በማለት የአዲስ አበባና አካባቢው ነዋሪዎች ላደረጉት ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።
ለፕ/ት ኢሳያስ አፈርቂ በብሔራዊ ቤተመንግስት በምሳ ሰዓት ከኦሮሚያ ክልል ር/መስተዳደር ለማ መገርሳና ከተለያዩ ግለሰቦች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሞ ባህል ትልቅ ቦታ እንዳለው የተነገረለትን የፈረስ፣ ጦርና ጋሻ ሽልማት ለፕሬዚዳንቱ አበርክተዋል።
ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ ሀዋሳ ከተማ በማምራት የሀዋሳ ኢንድስትሪ ፓርክን መጎብኘታው ታውቋል።
የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ነገም የሚቀጥል ሲሆን በሚሊኒየም አዳራሽ 25ሺህ ሰዎች በተገኙበት በአማርኛ ቋንቋ ንግግር እንደሚያደርጉና የሙዚቃ ድግስ እንደሚኖርም የወጣው መርሃ_ግብር ያሳያል።
በሌላ በኩል የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አሕመድ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቀን ላይ በፓሪስ እንዲገኙ በዛሬው እለት ቀጥታ ስልክ በመደወል ጥሪ ማቅረባቸውን የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ገልጸዋል።
ኢማኑኤል ማክሮን ጠቅላይ ሚንስትሩ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ታሪካዊ የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ላደረጉት ጥረትና ላስገኙት ስኬትም እንኳን ደስ አለዎት ማለታቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማገዝ ሀገራቸውና መንግስታቸው ቁርጠኛ ነው ማለታቸውንም አቶ ፍፁም ጨምረው ገልፀዋል።