የኢትዮ- ኤርትራ አዲስ ምዕራፍ – የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ዕይታ

የኢትዮ- ኤርትራ አዲስ ምዕራፍ – የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ዕይታ

  • በ10 አመት ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ በኮንፌደሬሽን ሊዋሃዱ ይችላሉ
  • በኢትዮጵያ አብዮት ሳይሆን ውስጣዊ የሥልጣን መቆራቆዝ እየተካሄደ ነው
  • ፕሬዚዳንት ኢሣያስ እንደዚያን ቀን ሲስቅ፣ ሲዝናና፣—አይቼው አላውቅም

  በተለያዩ ታላላቅ ዓለማቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች በታሪክ ተመራማሪነትና መምህርነት ያገለገሉትና የኢትዮጵያ የሥልጣን ሁኔታና የገበሬዎች አመፅን የዳሰሱበትን “Ethiopian Power and Protest” እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነትን፣ በኢትዮጵያ የተደረገውን አብዮታዊ ለውጥ የቃኙበትን “The Ethiopian Revolution” የተሰኙ መፅሐፍትን ለንባብ ያበቁት ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ፤ በተለይ በኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ ግንኙነት ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር በማድረግ ይታወቃሉ፡፡ ለመሆኑ ፕሮፌሰሩ፤ በሁለቱ አገራት መካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍጠር የተቻለውን የሰላም ስምምነት እንዴት ይመለከቱታል? ከሰላም ስምምነቱስ አገራቱ የሚያገኟቸው ፋይዳዎች ምንድን ናቸው? በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ ላይም አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጋር ያደረገው ዘለግ ያለ ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ እነሆ፡-

  በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ግንኙነት ታሪካዊ ዳራ ለማንሣት ያህል፣ ኤርትራ ነፃነቷን በተቀዳጀች ማግስት  ወደ ጦርነት የተገባበት ትክክለኛ ምክንያት ምን ነበር?

ለጦርነቱ እንደ ምክንያት የምትቆጠረው ባድመ ነች፡፡ ባድመ እንደ ምክንያት የግጭቱ መነሻ ለመሆኗ ደግሞ አፄ ምኒልክ ከጣሊያን ጋር በተፈራረሟቸው ውሎች መሠረት፤ በመሬት ላይ በተግባር ድንበሩን የማስመር ስራ አለመሠራቱ ነው፡፡ ኤርትራ ደግሞ ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ሁለቱ ሃገራት ለሠባት ዓመታት ጥሩ ግንኙነቶች ነበሯቸው፡፡ ባህልን፣ አካባቢን፣ ትምህርትን፣ ኢኮኖሚን፣ ሳይንስን የሚመለከቱ ውሎችንም ሁለቱ መንግስታት ተዋውለው ነበር፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ናቸው፣ ውሎቹን የተፈራረሙት፡፡ በአቶ መለስና በአቶ ኢሣያስ መካከል ደግሞ ልዩ ወዳጅነት የተመሠረተ መስሎ የታየበት ጊዜ ነበር፡፡

ሁለቱን መሪዎች “የአፍሪካ አዲስ ተስፋዎች” በሚል የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሳይቀሩ አሞካሽተዋቸው ነበር፡፡ ታዲያ ከሠባት ዓመታት በኋላ ባድመን እንደ ምክንያት አድርጎ የተፈጠረው ግጭት ምንድን ነው ብለን ስንጠይቅ፤ ዋነኛው መንስኤ የመሬት ጉዳይ ሳይሆን የኢኮኖሚ፣ የርዕዮተ ዓለም፣ የዜግነትና የማህበራዊ ጉዳይ ልዩነቶች ናቸው፡፡ ሁለቱ አካላት ፀረ-ደርግ ትግል አብረው ሲያደርጉ ለእነዚህ የልዩነት ምክንያቶች ትኩረት አልሠጧቸውም ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ ኤርትራ ነፃነቷን ስታገኝ፣ ከኢትዮጵያ ልዩ ጥቅም ፈላጊ ሆነች። እንደውም በኢትዮጵያ እንደ ሁለተኛ መንግስት እስኪቆጠሩ ድረስ የፈለጉትን እየሠሩ፣ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና በመንግስት ጉዳይ እጃቸውን በረዥሙ እያስገቡ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ደግሞ ብዙ አሻጥር ይሠሩ ነበር፡፡ ያኔ አንድ የአሜሪካን ዶላር 5 ብር የነበረ ይመስለኛል፤ እነሱ ሆን ብለው ምንዛሬውን ከፍ አድርገው መሠብሠብ ጀመሩ። ኤርትራ ቡና አምራች አይደለችም፡፡ ከኢትዮጵያ በኮንትሮባንድና በተለያዩ መንገዶች እየወሠዱ፣ በድንገት ኤርትራ ቡና አምራች ሆና ብቅ አለች፡፡

ለውጭ ገበያ ቡና አቅራቢ ሆነች፡፡ ሌሎችም እንደ ሠሊጥና ጥራጥሬ ያሉትንም በተመሳሳይ እሷ ሣታመርት ከኢትዮጵያ እየወሠደች ለውጭ ገበያ ታቀርብ ነበር፡፡ የራሳቸውንም ናቅፋ የተባለውን ገንዘብ ያሳትሙ ነበር፡፡ በኋላ ብር እና ናቅፋ እኩል ዋጋ እንዲኖራቸው እንዲሁም  ግብይቱም በሁለቱ ገንዘብ እንዲሆን ይጠይቃሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አይሆንም፣ የምንገበያየው በዶላር ነው፤ ብር እና ናቅፋን እኩል አድርገን አንቀበልም የሚል ምላሽ ይሠጣል፡፡ በዚህ የተነሣ የኤርትራ መንግስት ተቆጣ፣ የተፈራረምናቸው ውሎች ተሸረሸሩ አለ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ጦርነት ተገባ፡፡ የጦርነቱ ዋና ምክንያት ይህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ  ደግሞ በፀረ ደርግ ትግሉ ወቅት ይዘውት የመጡት መቃቃር አለ፡፡ አፋፍ ላይ ደርሠው ነበር፡፡

በወቅቱ (1977) ጦርነት አፋፍ ላይ ያደረሳቸው ጉዳይ ምን ነበር?

በዚያን ጊዜ ሻዕቢያ ለብቻው ከደርግ ጋር የሠላም ድርድር ማድረግ ጀምሯል የሚል ወሬ ህወኃት ይሠማል፡፡ ይሄ ያስደነግጣቸዋል፡፡ ከመጀመርያውም ህወኃቶች፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት ብለው የተቀበሉት ለደህንነታቸው ሲሉ ነው፡፡

ገብሩ አስራትና አረጋዊ በርሄ እንደሚሉት፤ በወቅቱ ያለመብሰል ወይም ያለማገንዘብ ጉዳይ አይደለም። በወቅቱ እነሱ ኤርትራ በኢትዮጵያ ቅኝ ተገዝታለች ብለው ሲቀበሉ የስትራቴጂክ ምርጫ ነበር፡፡ ይህ ማለት የትግራይ ትግል ከኤርትራው ትግል ጋር ተያያዥ ነው፡፡ የኤርትራው ትግል ካልቀጠለ የህወኃት ትግል ህይወት እይኖረውም ብለው በማሠብ ነው፡፡ በእርግጥም የኤርትራ ትግል ጠቅሟቸዋል፡፡ ኢህአፓ በወቅቱ “የኤርትራ ትግል የቅኝ ግዛት ጉዳይ ነው ብለህ ተቀበል” ተብሎ ነበር፡፡ ኢህአፓ ግን ዝምታን ነበር የመረጠው። ህወኃት እና ሻዕቢያ በዚህ ተሣስረው ነው በመጨረሻ ለድል የበቁት፡፡

በ1977 ጦርነት አፋፍ ላይ ደርሠው የነበረውም ሻዕቢያ ከደርግ ጋር እየተደራደር ነው መባሉ ህወኃትን ያደናገጠ ጉዳይ በመሆኑ ነው። ሌላው እንዲሁ በወቅቱ ሁለቱ ፀረ ደርግ ታጋዮች የተስፋፉበት ጊዜ በመሆኑ፣ በ1977 የተከሠተውን ድርቅ ተከትሎ፣ ህወኃት ህዝቡን ከእልቂት ለማዳን ወደ ሱዳን ሊያሻግር ሲል ሻዕቢያ በሩን ዘግቶባቸው ነበር፡፡ እናንተ የቀበሮ ጉድጓድ ብቻ ተቀምጣችሁ ከህዝቡ ሳትቀላቀሉ፣ ህዝቡን ሳትቀሠቅሱ ድልን መቀዳጀት አትችሉም በሚል ህወኃት ሻዕቢያን ይተች ነበር፡፡ ሻዕቢያ ደግሞ ህወኃትን ይንቀው ነበር፡፡ መልስ አይሠጣቸውም ነበር። ሌላው የፀባቸው ምክንያት ህወኃት የሚያራምደው የብሄር ጉዳይ ነው፡፡

በኤርትራ ዘጠኝ ብሄሮች አሉ፤ ስለዚህ የብሄሮች መብት እስከ መገንጠል የሚለውን ተቀበሉ ይሏቸዋል ህወኃቶች። ሻዕቢያ ደግሞ እኛ ፀረ ቅኝ ግዛት ነው ትግላችን፤ በኛ ጉዳይ አያገባችሁም ይሏቸዋል፡፡ ኋላም ህወኃት-መራሹ ኢህአዴግ፤ አሁን ያለውን የፌደራል ስርአት ሲያቋቁም፣ በወቅቱ የኤርትራ መከላከያ ሚኒስትር የሆነው ጀነራል ስብሃት ኤፍሬምን ሁለት ጊዜ አግኝቼ አነጋግሬው ነበር፡፡ ህወኃት ሃገሪቱን በብሄር ማደራጀቱ ዞሮ ዞሮ እግራቸውን እንደሚቆርጣቸው ነግረናቸዋል፤

የጎሣ ፌደራሊዝም አይጠቅምም ብለናቸው ነበር ብሎኛል፡፡ እነዚህ እንግዲህ ሁለቱ በአንድ ተሰልፈው ደርግን የጣሉ ሃይሎች፣ ከነበራቸው ልዩነት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ይህ ቁርሾ ወደ ሁለቱ ሃገራት ጦርነት ደረጃ ከፍ እንዳደረገው መገመት ይቻላል፡፡

እንግዲህ  ሁለቱ ሃገራት በጦርነት ከተለያዩ ከ20 ዓመት በኋላ ሠሞኑን አዲስ የሠላም ስምምነት ላይ ደርሰዋል…ይህንን የለውጥ ተስፋና ብርሃን እርስዎ  እንዴት አዩት?

በአግራሞትና በመደነቅ ነው ያየሁት፡፡ ምክንያቱም ሂደቱ በጣም ፈጣን ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አስመራ ሄደው ባለ በርካታ ነጥብ ስምምነት መፈራረም ያልተጠበቀና አስገራሚ፣ አንዳንዴም አስደንጋጭ ሆኖ አገኘዋለሁ፡፡ ይህ የሠላም ስምምነቱ የቀጠናውን ሁኔታ ይቀይረዋል የሚል ግምት አለኝ፡፡

የመሪዎቹን የግለሰብ ሁኔታ ስንመለከትም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ መጀመሪያ የአስመራን ምድር ከረገጡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ምሽት የራት ግብዣው ድረስ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፤ ፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ እንደዚያን ቀን ሲስቅ፣ ሲዝናና፣ ሲንቀሳቀስ አይቼው አላውቅም፡፡

ይህ የእርቅ ሂደት ለኤርትራውያንና ለፕሬዚዳንት ኢሣያስ አፈወርቂ ምን አንደምታ ይኖረዋል?

አንድ በኤርትራ ቲቪ አስተያየት የሰጠ ሠውም፤ “በትዕግስት ስንጠብቀው የነበረ መስዋዕት የከፈልንበት ነው፤ ውጤቱ የትዕግስትና የአቅል ነው” ብሏል፡፡ በዚህ አስተያየት ውስጥ የተገነዘብኩት፤ ኢሳያስ ጀግና ነው አለምን ገትሮ የያዘ ነው፤ ከአቋሙ ዝንፍ የማይል ነው ከሚለው በመነሳት፣ የአለመንበርከክነት ውጤት ሆኖ በደጋፊዎቻቸው እንደሚታይ ነው፡፡

ይህ የሠላም ጅምር በዚህ ሁኔታ የነበራቸውን የአለመንበርከክ ድጋፍ የሚያጠናክርላቸው ይመስለኛል፡፡ እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት አፋኝ መንግስት ነው፡፡ ህገ መንግስት የሌላት፣ የዲሞክራሲ ፍንጭ ያልታየባት ሃገር ናት፡፡ በዚህ ምክንያት መድብለ ፓርቲ የሚባል ነገር የለም፡፡ በውጭ ሃገራት ሆነው የሚንቀሳቀሡ 19 ያህል ተቃዋሚ ድርጅቶች ቢኖሩም ያን ያህል ጠንካራ አይደሉም፡፡

ድርጅቶቹ ያላቸው ድክምት እንዳለ ሆኖ፣ ኢሣያስ ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ለጊዜው በዚህ ሁኔታ ሊለዝቡ ይችላሉ፡፡ ሌላው ኤርትራ እንደሚታወቀው፤ ከአለም ማህበረሰብ ተገልላ የቆየች ሃገር ነች፡፡ ከኢጋድ አባልነት እንኳ የወጣች ሃገር ነች።<span lang=”AMH” style=”font

LEAVE A REPLY