ሰንደቅ ዓላማችን የታሪካዊ ማንነታችን ህያው ምስክር ነው!
ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ !
.ሰንደቅ ዓለማ የሕዝብ የማንነቱ አሻራ አምቆ የያዘ በዛሬ እና በትናንት መካካል የታሪክ አደራን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሻጋገረ የሚቆይ ህያው ምልክት ነው ፡፡ ሰንደቅ ዓላማ በትውልድ ቅብብሎሽ ዘመናትን የሚሻገርና ዝንተዓለም የሚኖር የአንዲት ሉዓላዊት አገር መለያ ጭምር ነው ፡፡
ኢትዮጵያ እንደሀገር በቆየችባቸው ረጅም ዓመታት ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋለች ፤ህዝቧም ነፃነቱን እና አንድነቱን አስጠብቆ ለመኖር እንዲሁም የግዛት ወሰኑን ለማስከበር አጥንቱን ከስክሶ፣ ደሙን አፍስሶ የኖረ ድንቅ ሕዝብ ነው፡፡ ለዚሀም ህያው ቀደምት ታሪካችን የሚመሰክረው ይህንኑን ሃቅ ነው!! የእኛነታችን መገለጫ ከሆኑት ውስጥ አንዱና ዋንኛው ሰንደቅ ዓላማችን ነው፡፡
ሰንደቅ ዓላማችን የትናንት የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን ተጋድሎ ታሪክ ፣ባህል፣ትውፊት እና መሰል ዝክረ ታሪክ ጥልቅ የሆነ የማንነታችን ምልክት ገድል ነው፡፡መልካም ነገር ስናከናውን ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ ሲውለበለብ በኩራት አንገታችንን ቀና አድርገን እንራመዳለን ፡፡ የሚያሳፍር ሁኔታም ሲገጥመን እንዲሁ አንገታችንን እንደፋለን፡፡ሆኖም ግን፤ ታፍሮና ተከብሮ የኖረው የሕዝባችን ታሪክ ዝቅ እንዳይል ሰንደቅ አላማችን ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የትጋታችን ስንቅ ሆኖ ያገለግለናል፡፡ ምክንያቱም ሰንደቅ ዓላማችን በደም እና በአጥንት የቆመ የእኛነታችን ልዩ የብርታት እና የአሸናፊነት ምልክታችን ጭምር ነው ፡፡
የሀገራችን ሰንደቅ ዓላማ በተለያዩ የሥርዓት መፈራረቅ ውስጥ በአግድም አርንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ በመደቡ ላይ የሚቀመጡት ዓርማዎች ግን በሕዝባችን ላይ ልዩነት ፈጥረው ቆይተዋል፡፡ በንጉሣዊ አስተዳደር ዘመነ መንግሥት ፣በኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ( ኢህዲሪ )፣ እንዲሁም በኢፌዴሪ መንግሥት የተለያየ ምልዕክት ቢቀመጥም ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀደምት ታሪኩን ጠብቆ በመንግሥታቱ ውስጥ ከነበረው የሪፐብሊክ ዓርማ ውጭ ያለውን ወጥ የሆነውን አርንጓዴ፤ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ ተቀብሎ ኖሯል ፣ወደፊትም ይኖራል !!! በተለይ በንጉሣዊው አስተዳደር ዘመነ መንግሥት እና በኢትዮጵያ ህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ( ኢህዲሪ ) መንግሥት የሪፐብሊክ ዓርማ የነበረ ቢሆንም፤ ምንም አይነት ተጨማሪ ምልክት የሌለውን አርንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በክብር በመቀበል መንግስታቱ የታሪክ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡
ስለዚህም በትናንት ታሪካችን እና በተለያዩ ጊዜያት በምንመሰርተው ሪፐብሊክ ላይ የጋራ መግባባትና ይሁንታ ማግኘት ባለመቻሉ ብሎም በሕዝብ ፈቃደኝነትና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር መስፍን ባለመቻሉ የሪፐብሊኩ ዓርማ ላይ ስምምነት መድረስ አልተቻለም፡፡ መንግሥታት በተቀያየሩ ቁጥር በሰንድቅ ዓላማ ላይ የሚቀመጠው አርማም አብሮ ሲቀያየር ኖሯል ፡፡
በመሆኑም በህገመንግሥቱ ላይ የተደነገገው “የኢትትዮጵያ ህዝብ ሰንድቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ ከመሃሉ ቢጫ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀከሉ ብሔራዊ አርማ ይኖረዋል፤” በሚለው ሀርግ ስር በአዋጅ የተቀመጠ “ዓርማ ይኖረዋል” የሚለውን ተከትሎ ፤የሕዘብ ፍቃድ እና ይሁንታ ያላገኘና በአግባቡ በሕዝብ ተቀባይነት ሣይኖረው ፤አሁን ላይ የሪፐብሊኩ መንግሥት ዓርማ ነው፡፡ በሚል ኮከብ መሣይ ነገር ከሰንደቅ ዓላማው ላይ ተቀምጦ የሚገኘው አርማ እንዲነሳ ሰማያዊ ፓርቲ አጥብቆ ይጠይቃል ፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሕዝብ ፈቃድ የተመረጠ ሪፐብሊክ በሚመሰረትበት ጊዜ የሪፐብሊኩ መንግሥት ዓርማ ብቻውን በሕግ ተደንግጎ በሥራ ላይ የሚውልበት አግባብ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤አሁን ግን ሰማያዊ ፓርቲ የኢትዮጵያ ህዝብ የማንነት አሻራ የሆነውን ከላይ አረንጓዴ ከመሃሉ ቢጫ ከታች ቀይ ምንም አይነት ምልክት የሌለበት የኢትዮጵያ ሕዝብና የአገር መለያ የሆነውን ሰንድቅ ዓላማችን ፤እንደቀድሞ አሁንም እንዲቀጥል ሰማያዊ ፓርቲ በአፆንኦት ይጠይቃል ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቡም ባለፉት ሣምንታት በተለያዩ ክፍል ሃገር የቀድሞ ክብሩና ዝናው መገለጫ የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ፣በሰላማዊ መንገድ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት እዳለበት ሰማያዊ ፓርቲ ያምናል !! በመሆኑም ፓርቲያችን ህዝብ ላቀረበው ጥያቄ የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አስፈላጊውን እና ሕጋዊ መንገድ በመከተል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በመቆም፤ ሰንደቅ ዓላማው እንዲመለስለት በሚያደርገው ጥረትና ትግል ሰማያዊ ፓርቲ የበኩሉን ታሪካዊ አደራውን እና ኃለፊነቱን ይወጣል፡፡
ሰንድቅ ዓላማችን ፤ አረንጓዴ፣ቢጫ፣ቀይ ምንም አይነት ምልክት የሌለበት ነው !!!
ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር !