/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ አባቶች መካከል ባለፉት 27 ዓመታት ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ለመፍታትና እርቅ ለመፍጠር ከአዲስ አበባ የተነሳውን ልዑክ በትዕግስትና በአስተዋይነት እንዲሰራ ሲሉ ዛሬ በጽ/ቤታቸው ጠርተው መክረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ሳምንት፣ በአሜሪካ በሚኖራቸው ቆይታ ለሰላም የሚከፈልን ማንኛውንም ዋጋ በመክፈል የቤ/ክርስቲያንቷን ሰላም እንዲመለስ ጥረት እንዲያደርጉ አስራ አንድ አባላት ያለውን አሸማጋይ ኮሚቴ አደራ ብለዋል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በእርቀ-ሰላም በመፍታት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት የሆነችውን ቤተክርስቲያን ጠንካራ ተቋም ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠ/ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
የእርቀ ሰላሙ ጉዞ ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደደረሰና በሁለቱም በኩል ያሉትን አባቶች በማስማማት በቅርቡ የሰላምና የፍቅር ብስራት በኢትዮጵያ እንደሚሆን የአስታራቂ ኮሚቴው አባላት ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ አባቶች መካከል እርቀ ሰላም ለማምጣት መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ለመጣት ዘግጁ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ከኮሚቴው ጋር በጽ/ቤታቸው በነበራቸው ቆይታ ማረጋገጣቸው ታውቋል።
ለአመታት የዘለቀው የእርቅ ሂደት በህውሃት ጣልቃገብነት ሲስተጓጎል እንደሰነበተ የሚታወቅ ሲሆን በተለይም አቡነ ጳውሎስ ባረፉበት ወቅት ቅድስት ቤተክርስቲያን ወደ አንድ ተሰብስባ በሕጋዊው ቅዱስ ፓትርያርክ ስር ትሆናለች ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።
ከ70 አመት በላይ የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በተመሳሳይ መልኩ ተከፍሎ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን የኮሙኒስት ስርአት በተጠናቀቀ ጊዜ መፍትሄ ማግኘት መቻሉ ከስርአት ጋር በተያያዘ ክፍፍል የሚጠናቀቀው ከስርአቱ ውድቀት ጋር መሆኑን ማሳያ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሚቀጥለው ሳምንት በአሜሪካን ሀገር የሚያደርጉትን ጉብኝት ሲያጠናቅቁ ህጋዊውን ቅዱስ ፓትርያርክ አጅበው ወደ ሃገርቤት እንደሚመለሱ ውስጥ አዋቂዎች በተለይ ለኢትዮጵያ ነገ ድረገጽ ጠቁመዋል።