የመጀመሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ
_________
የተከበራችሁ የሀገራችን መስሊሞች
የተከበራችሁ የኢስላም ዲን ጠባቂ ዑለማዎችና ዳዒዎች
የተከበራችሁ የሀገር ሽማግሌዎችና አባቶች
የተከበራችሁ ወጣቶች
የተከበራችሁ የፌደራልና የክልል እስልምና ጉዳዮች ም/ቤቶች አመራር አባላት
ክቡራትና ክቡራን
ያለንበት ወቅት የራሳችንን ተቋማዊ ህልውና በራሳችን ለመወሰን በጋራ የምንቀሳቀስበት የታሪክ ሂደት እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ ብለን እናስባለን፡፡ ለዛሬው ማንነታችንና ዛሬ ላይ የኢስላም ሃይማኖትን ትምህርትና አቅጣጫ እንድንከተል እጅግ አስቸጋሪ የትግል መስመር ውስጥ አልፈው ሃይማኖቱ ላለፉት 1438 ዓመታት በሀገራችን ምድር እንዲቆይ ላደረጉ ኡለማዎችና ሰፊው ሙስሊም ማህበረሰብ አላህ ጀነትን እንዲለግስልን እንማጸናለን፡፡ ያለነርሱ ሁለገብ ትግል ዲነል ኢስላም ወደዚህ ትውልድ ሊተላላፍ የሚችልበት መንገድ አልነበረውም፡፡ በሀገራችን ሁለገብ የለውጥ አየር እንዲመጣና የሙስሊሞች ጉዳይም ብሔራዊ ትኩረት እንዲሰጠው መስዋእትነት ለከፈሉ ወገኖች ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡
ክቡራትና ክቡራን
እነሆ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ለበርካታ ዓመታት በሁሉም የሀገራችን ሙስሊሞች ሲነሱ የቆዩ የአስተዳደር፣ የልማትና የፍትህ ጥያቄዎች ተጨባጭና ተቋማዊ ምላሽ ያገኙ ዘንድ የማህበረሰቡ ጉልሃን እርስ በርሳቸውና ከህዝባቸው ጋር ተመካክረው ይበጃል የሚሉትን አቅጣጫና አደረጃጀት እንዲያቀርቡ መንገዱን ካሳዩ እነሆ አስራ አምስት ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ለአዲሱ መሪና መንግስታችን ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡ በርሳቸው ሸምጋይነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ም/ቤት መዋቅር፣ አደራጃጀትና አንድነት ላይ ጥናት ለማቅረብ የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ የህዝበ ሙስሊሙን መሪ ተቋም የአደራጃጀትና የሚና ውስንነት በመመርመር በቅርጽም በይዘትም ሙስሊሙን ማህበረሰብ በተገቢ መንገድ ሊያቀናጅና ሊመራ የሚችልና የሁሉም ሙስሊሞች የጋራ ቤት የሆነ ተቋም እውን እንዲሆን የሚያስችል ምክረ ሀሳብ የማቅረብ ታሪካዊ ሀላፊነት ተጥሎበታል፡፡ ኮሚቴው ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሶስት አባላት፣ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሶስት እንዲሁም የገለልተኛ ሚና ሊኖራቸው ከሚችሉ ሶስት አባላትን ያቀፈ መሆኑ ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሰረትም ተሰያሚ የኮሚቴው አባላት ለዚህ እጅግ አስፈላጊ ሚና ራሳቸውን ሲያዘጋጁ፣ ሲያደራጁና መሟላት የሚገባቸውን ቅድመ ዝግጅቶችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ኮሚቴው እርስ በርስ የሚናበብ፣ ከግልና ከቡድን ፍላጎት ለህዝባዊና ኢስላማዊ ፍላጎቶች ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ከጊዜያዊ መፍትሄዎች ይልቅ ለቋሚና ትውልድ ተሸጋሪ መፍትሄዎች የሚተጋ መሆን ያለበት በመሆኑ እነሆ ላለፉት አስራ አምስት ቀናት ለዚህ አንኳር ገጽታና ሚና ግብኣት የሚሆኑ የስነ ሥርዓት ጉዳዮችን እያሟላና እየተዘጋጀ ቆይቷል፡፡ ኮሚቴው የውስጥ አደረጃጀቱን መወሰን ስለነበረበትም በጠቅላይ ሚንስትሩ ፊት በሰብሳቢነት ከተመረጡት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ በተጨማሪ
1.የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት የሆኑትን ሐጂ ሙሐመድ አሚንን ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ፣
- ኡስታዝ አቡበክር አህመድን ምክትል ሰብሳቢ፣
- ዶ/ር እንድሪስ ሙሐመድን ዋና ጸሀፊ፣
- አስታዝ አህመዲን ጀበል ም/ ጸሀፊ፣
- ኡስታዝ ካሚል ሸምሱን የኮሚቴው ቃል አቀባይና የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ሆነው እንዲያገለግሉ በሙሉ ድምጽ መርጧል፡፡
ኮሚቴው የድርጊት መርሀ ግብሩን መሰረት ያደረገ ሥራዎቹን የጀመረ መሆኑን እያበሰርን የተጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ከግብ ለማድረስ የተለያዩ ሞያዊ እገዛዎችን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ከሚገኙ ወገኖቻችን የሚሻ በመሆኑ በጊዜአዊነት ከተከራየነው ቢሮ ድረስ በመምጣት ሃሳብን ማቅረብና መወያየት ወይም በኮሚቴው የፌስቡክ የውስጥ መስመር መላክ የምትችሉ መሆኑን ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡ ኮሚቴው በሁሉም ክልል የምክክር ጉባኤዎችን ከኡለማዎችና ከህዝበ ሙስሊሙ ጋር የሚያደርግ በመሆኑ ትኩረትና ውክልና ተነፍጎኛል የሚል ወገን እንደማይኖር እናረጋግጣለን፡፡ የተጀመረውን የተረጋጋ የለውጥና የማስተካከል ሂደት የሚያውክ ትችትና የሃላፊነት እሰጥ አገባ እንዲቆምና ሁሉም ወገን በያለበት የወንድማማችነት መንፈስ እንዲያሳይ በማክበር እንጠይቃለን፡፡ በአሻሚ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ የግንዛቤና የትርጓሜ ልዩነቶች በኡለማዎችና በዘርፉ ባለሙያዎች በጋራ እንዲታዩ የሚደረግ በመሆኑ ለዛሬ የሁከት መነሻ እንዳይሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ እናሳስባለን፡፡
በመጨረሻም መጪው ጊዜ መርህን መሰረት ያደረገ ህብረት ብሎም አንድነት የሚስተዋልበት፣ በቡድን የመከፋፈል ጥግ የሚያከትምበት፣ ሁላችንም በአንድ መድረክ ሃሳብችንን የምናካፍልበት፣ የትርጓሜና የአረዳድ ልዩነቶች መሰረታዊ የኢስላምን ምንጮች መሰረት ያደረጉ አስከሆነ ድረስ ራህመትና እዝነት እንጂ የግጭትና የሁከት መንስኤ የማይሆኑበት፣ በመንፈስም በቁስም ተደራጅተን የምንታይበት እንዲሁም ለሀገር አንድነትና ሰላም ይበልጥ የምንተጋበት እንደሚሆን ተስፋችን የላቀ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡ ለዚህ የተቀደስ ግብም ሁሉም ወገን ከጎናችን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
አላህ ለስኬት ያብቃን፡፡
ተ.ቁ ስም ሃላፊነት
1 ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ኡመር ኢድሪስ ሰብሳቢ
2 ሐጂ ሙሐመድ አሚን ጀማል ኡመር ተቀዳሚ ም/ሰብሳቢ
3 ኡስታዝ አቡበክር አህመድ ሙሐመድ ም/ሰብሳቢ
4 ዶ/ር እንድሪስ ሙሐመድ የሱፍ ዋና ፀሐፊ
5 ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ሙሐመድ ም/ፀሐፊ
6 ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ሲራጅ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ
7 ረ/ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሀቢብ ሙሐመድ አባል
8 ሐጂ ከድር ሁሴን ሀምዛ አባል
9 ኡስታዝ ሙሐመድጀማል አጎናፍር አባል
አድራሻ
ኢ-ሜይል፡- ethiomuslims9committee@gmail.com
ሐምሌ 12፣ 2010
አዲስ አበባ