[[ አብይ አህመድ እና ለማ መገርሳ ፈጣሪ ከሠማይ የጣለልን ይመሥለኛል….]]
.
ከ27 ዓመት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በጠቅላይ ሚንስትር የሰብሰባ አደራሽ የተገኙት ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፤ ዶ/ር አብይ የእለቱን የመወያያ አጀንዳ ከገለጹ በኋላ እና የስብሰባው ተሳታፊዎች አሳባቸው እየገለፁ ባሉበት ወቅት ነው፤ የኔታ ወደ መሰብሰቢያ አዳርሽ ውስጥ የገቡት። ዶ/ር አብይ ጨምሮ በአዳራሽ ውስጥ የነበሩ ተሰብሳቢ የኔታ የመቀመጫ ወንበራቸውን እስኪይዙ ድረስ የተሰብሳቢው ዓይን በፍቅርና በአክብሮት እሳቸው ላይ ነበር ያረፈው።
የተጀመረው ውይይት በተሰብሳቢዎች በሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየት ቀጥሎ ለሻይ እረፍት ስብሰባው ተቋረጠ። ሁላችንም ሻይ እና ቡና ወደተዘጋጀበት ቦታ አመራን፤ ዶ/ር አብይ ለሻይ በወጣንበት ወቅት የቱ ጋር እንዳሉ እኔ ልብ አላልኩም፤ ይልቁንም ለየኔታ ትኩስ ነገር ምን ላምጣሎት ብዬ ስጠይቃቸው? ” አንድ ሲኒ ቡና ትንሽ ስኳር ጨምረ አመጣልኝ ፣ ከዚያ በፊት የምቀመጥበት ወንበር አሉኝ ” በዚህን ጊዜ አጠገቤ የነበረው አበበ አካሉ ፈጥኖ ቡና ሊያመጣ ሄደ፣ እኔ’ም የመቀመጫ ወንበር አምጥቼ እንዲቀመጡ አደረግን ……..።
.
በዚህ መሐል ድንገት ወደኋላ በምዞርበት ወቅት ዶ/ር አብይ ቀይ መለዮ ከለበሱ ጠባቂ ወታደሮች እንዲሁም የጠቅላይ ሚ/ሩ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ ጋር በመሆን አንድ ላይ ሆኖው እኛ ወዳለንበት አቅጣጫ እየመጡ እንደሆነ አየኹኝ፤ ሁኔታው ግልጽ ነበር ዶ/ር አብይ የኔታን ለማግኘት ነው ወደኛ የመጣው፤ ቀይ መለዮ ለባሽ ጠባቂዎች እኛ የነበርንበት ቦታ ክብ ሰርተው በቅርብ እርቀት በተጠንቀቅ ቆሙ ……..።
.
ወዲያውኑ አጠገባችን የደረሰው ዶ/ር አብይ አህመድ፤ እጅግ ትህትና ፍቅር በተሞላበት ሁኔታ በጣም ዝቅ ብሎ እሳቸው ከተቀመጡበት እጁን ዘርግቶ ሰላምታውን ሰጣቸው፤ በዚህን ወቅት የኔታ ቁጭ ብዬ ሰላምታን አልቀበልም በማለት ከወንበራቸው ለመነሳት ሲሞክሩ፤ ዶ/ር አብይ ደግሞ “ፕሮፍ በፍጹም አይገባም” እያለ ሲከላከላቸው የነበረው የሰኮንድ ጊዜ ትእይንት፤ የአባትና የልጅ ፍቅርና አክብሮት በአካባቢው ለነበር ለሚመለከት ሁሉ ልዩ ሰሜት የሚሰጥ ነበር……..።
ዶ/ር አብይ “ፕሮፍ እንዴት ኖት?” በማለት በሚገርም ትህትና ሰላምታ እያቀረበ ድንገት ዞር ብሎ ስሙን አሁን የረሳውት አንድ ሰው በመጥራት “ፕ/ር በየነ’ን ጥራቸው” በማለት ፈገግታ በተሞላበት መልኩ ለመልክተኛው ነገረው፤ አንደኛው ጠባቂ ሌላ ሁለት ወንበር ይዞ መጣ፣ ዶ/ር አብይ ከየኔታ ጋር አጠገብ ተቀመጠ። ብዙም ሳይቆይ ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ አብሯቸው አንድ ላይ ተቀመጡ፤ የሻይ ብና ሰዓት አጭር ቢሆንም ጠቃሚ ነገር አንስተው አንድ ሁለት አሳብ ተለዋውዋል። ንግግራቸው በፈገግታ የታጀበ ነበር።
የጠቅላይ ሚ/ሩ የጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍጽም አረጋ በአካባቢው የነበረውን ክስተት በምስል ለመያዝ
የሞባይል ስልካቸውን በእጃቸዉ ይዘው አካባቢያቸውን በትኩረት ይቃኛሉ፤ ከእኔ’ም ጋር አጭር ቆይታ ነበረው። ከንግግሩ እና ከሁኔታው እንደተረዳሁት እሱም ከትህትናው በተጨማሪ ሌላውን ለማዳመጥ ያላው ፍላጉት ደስ የሚል ነው።
የሻይ ቡና ክፍለ ጊዜ ከተጠናቀ በኋላ ሁላችንም ወደ ስብሰባ አዳራሽ ገባን….፤ ከሻይ ቡና የእረፍት ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ ተናጋሪ የነበሩት የኔታ ነበሩ፤ ፕ/ር መስፍን ንግግራቸውን እንዲህ ሲሉ ጀመሩ “የምፈለግ ሰው አይደለሁም በብዙ ቦታ፣ ዛሬ ተፈልጌ መምጣቴ ኢትዮጵያ ምን ያህል እንደተለወጠች የሚያሣይ ነው። ” በማለት ለተደረገላችው ጥሪ አስተያየታቸውን ከገለጹ በኋላ ወደ ዋና መልክታቸው ገቡ።
እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ “……ዛሬ እዚህ ደርሰናል፣ ኢትዮጵያም እዚህ ደርሣለች፤ ጥያቄው ሁላችን የምንከበርባት በልተን የምናድርባት፣ ኮርተን ኢትዮጵያዊ ነን የምንልባት አገር እንዴት እናድርጋት በማለት ለራሳችን መጠየቅ አለብን ስግብግብነት ከውስጣችን በማውጣት የሚጠቅመን ነገር እሁን የምናደርገው እኛ ነን።…. ስግብግብነት ከመጥፎ ድህነት ወይም ከመጥፎ ጠባይ ይመጣል፤ ጥጋብ ይበልጣል ኩራት ?! ጦም ማደርም ወራዳ መሆንም ጥሩ አይደለም፣ ግን የቱ ይሻላል?! በማለት ጥያቄ ጠይቀዋል ።
.
ዶ/ር አብይ ጨምሮ ሁሉም ተሰብሳቢ በልዩ ትኩረት የየኔታ ንግግር በአጽንዖት መከተተላቸው እንደቀጠለ ነው፤ የኔታም ንግግራቸውን እንዲህ በማለት ቀጠሉ .. ” 88 ዓመቴ ነው፣ ከጣሊያን ጊዜ ጀምሮ በዚህ ዘመን ያላየሁትን አይቻለሁ ፤እግዚአብሔር ኢትዮጵያዊ ይወዳታል፣ ጥሎ አይጥላትም፣ አብይ አህመድ እና ለማ መገርሳ ፈጣሪ ከሠማይ የጣለልን ይመሥለኛል….” በማለት የኔታ በሚናገሩበት ወቅት በአዳራሹ የነበሩት ተሰብሳቢ በአድናቆት እና በድጋፍ ጭብጨባ ለንግግራቻው ምላሽ ሰጠ፤ ዶ/ር አብይም ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ ከተቀመጡበት አንገታቸውን ከፍ እና ዝቅ እያደረጉ ለጭብጨባው ምላሽ ሰጡ።
የኔታ እንዲህ በማለት ንግግራቸውን ቀጠሉ “የተጀመረው ለውጥ መቀጠል አለበት፤ እነ አብይ የያዙትን አዲስ ዓላማ ለመትከል ሲፈልጉ እንዴት እንርዳቸው? እንዴት እናግዛቸው ማለት አለብን? ትልቁ ጥያቄ ለእኔ ይሄ ነው፤ መመለስ ያለብን ይህንን ነው።…..
እኔ በቀረቺኝ እድሜ ባለኝ አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ ዜጎች ብሄሮች አይደለም በሚያደርጉት ልረዳቸው ቃል እገባለሁ።” ብለው ሲናገሩ ከፊተኛው የበለጠ በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ የጭብጨባ ድምጽ ከፍ ብሎ ተሰማ፤ የኔታ’ም ንግግራቸውን አጠቃለው ለመሄድ ፍቃድ ጠይቀው ተነስተው ሄዱ። ዶ/ር አብይ’ን ጨምሮ ሌሎቻችን ግን ስብሰባውን ቀጠልን። በነገራችን ላይ በወቅቱ በነበረን የግማሽ ቀን ስብሰባ ዶ/ር አብይ አጠቃላይ ቢደመር 30 ደቂቃ ያህል ስለመናገራቸው እርግጠኛ አይደለሁም፤ አብዛኛውን ጊዜ በማዳመጥ እና ማስታወሻ በመፃፍ ነው ያሳለፉት። የተቀረውን እና ዋና ጉዳይ በተመለከተ የግል ምልከታዬ………….ይቀጥላል………..
.