/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሶማሌ ክልል እየተፈጸመ ያለውን የሰዎች ግድያና የቤተክርስቲያን ቃጠሎ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እጅግ ማዘናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በሰጡት መግለጫ፤በሶማሌ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በደረሰው ግጭት ሳቢያ የበርካታ ሰዎች ህይወት በመጥፋቱ ማዘናቸውን ገልጸዋል። ሰባት አብያተ ክርስትያናት ተቃጥለው የካህናት ህይወትም ማለፉን ተናግረዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።
ለዘመናት አብረው በኖሩ ወንድማማች ህዝብ መካከል እየተፈጸመ ያለው ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።ቤተ ክርስቲያኒቱም የተፈጠረው ችግር እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን እንደ ወትሮው ሁሉ ድጋፏን ታደርጋለች ብለዋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለፋና ቴሌቪዥን እንደገለጹት ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመው፤ ህይዎታቸውን ላጡ ወገኖችም በሁሉም አድባራትና ገዳማት ፍትሃት ይደረጋልም ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ነገ የሚጀምረው የፍልሰታ ጾም በሁሉም አድባራትና ገዳማት በምህላ እንዲሁም በጸሎት እንደሚታሰብም ጠቁመዋል።