/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ከኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ትናንት በአስመራ ድርድር ላይ ተቀምጦ የነበረው ኦነግ(ሽኔ የሚባለው የኦነግ ክንፍ) መቋጫ ማግኘቱ ገለፀ።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ ሽኔ) ወደ ሀገር ቤት ገብቶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑን ዛሬ ባውጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኦነግ በመግለጫው “በኦነግና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል የነበረው ጦርነት ተገትቶ አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ኦነግ በሀገር ውስጥ በግልጽ ሊሰራ የሚያስችለው መሆኑ ከግንዛቤ ገብቶ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ እንዲቀጥል ከስምምነት ላይ መድረሱን ገልጿል።
ወንድማዊ መንፈስ የተንፀባረቀበት ነበር ባለው የአስመራ ውይይት፤ አቶ ዳውድ ኢብሳ፣ አቶ ኢብሳ ነገዎ፣ አቶ አቶምሳ ኩምሳ፣ አቶ ቶሌራ አደባና አቶ ገመቹ አያና ድርጅቱን ወክለው መደራደራቸውን ገልጿል።
በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ክንፍ ለበርካታ ዓመታት ዋና መቀመጫውን በአስመራ አድርጎ ሲቀሳቀስ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኦነግ ትጥቁን ፈትቶ ኤርትራ ውስጥ በጥገኝነት እንዲቀመጥ አልያም ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀስ በማለት ሁለት አማራጭ መስጠታቸው መዘገቡ ይታወሳል።