ጂቡቲ ዜጓቿን ከድሬዳዋ እያስወጣች ነው ተባለ

ጂቡቲ ዜጓቿን ከድሬዳዋ እያስወጣች ነው ተባለ

ከትናንት በስቲያ በድሬዳዋ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ በአዲስ አበባ የሚገኘው የጂቡቲ ኤምባሲ “ለህይወታችን ያሰጋናል” ያሉ ዜጎቹን ማስወጣት ጀምሯል።

በኢትዮጵያ የጂቡቲ አምባሳደር መሀመድ ኢድሪስ ፋራህ አንድ ሺ የሚሆኑ ዜጓቿን በባቡር፣ በአውሮፕላንና በመኪናም የመለሰች ሲሆን ከሶስት ሺ በላይ የሚሆኑ የጂቡቲ ዜጎች በድሬዳዋ ያሉ ሲሆን እነሱም ለመዝናናት የመጡ እንደሆነ አምባሳደሩ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በቀጣዩም ቀናት መመለስ የሚፈልጉ ዜጎቿን እንደምታስወጣም ተናግረዋል።በኦሮሞዎችና በሶማሌዎች መካከል በተነሳ ግጭት በአጠቃላይ አስር ሰዎች ሲሞቱ አምስቱ የጂቡቲ ዜግነት ያላቸው ናቸውና የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውንም አምባሳደሩ ገልፀዋል። ይህ ከተሰማ በኋላ በአጠቃላይ ፍራቻ እንደተሰማ አምባሳደሩ ይናገራሉ።

“በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን በሶማሌ ክልል ያሉ ጂቡቲያውያንም በግጭቱ ምክንያት ደንግጠዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመነጋገር ሁኔታው እንደሚረጋጋ ፀጥታው እንደሚመለስ ብንነግራቸውም ስለፈሩ ወደ ጂቡቲ መልሰናቸዋል” ብለዋል።

ለአጭር ጊዜ ከመጡት በተጨማሪ ስምንት መቶ የሚሆኑ ዜጎቿም በድሬዳዋ ቢኖሩም እነሱ እንደማይወጡ ተናግረዋል። ” በድሬዳዋ ነዋሪ የሆኑትን ነዋሪዎችን አነጋግረናል። አሁን ያለውም ሁኔታ የተረጋጋ መሆኑን ከወኪሎቻችን ማረጋገጥ ችለናል” ብለዋል።

“ምንም እንኳ ሁኔታዎች የተረጋጋጉ ቢሆንም። ለጉበኝት የመጡ ሰዎች ስለፈሩ ከድሬዳዋ አስወጥተናቸዋል። ስለፈሩና በነሱ ጥያቄ መሰረት ነው እየመለስናቸው ያለው” ብለዋል።

(ምንጭ፦ቢቢሲ አማርኛ)

 

LEAVE A REPLY