ክቡርነትዎ እንዴት ከርመዋል?
ወዳጁንም፣ ጠላቱንም፣ ሚናው ያልለየውንም በማቀፍ የዛሉት እጆችዎስ በረቱ?
እኔ ደኅና ነኝ ባይ ነኝ። ዘላቂ ደኅንነቴ በርስዎ መንግስት እና በፈጣሪ እጅ ነው።
ክቡርነትዎ በእንዲህ ያለ በኩራፊያ የደነዘዘ ፣ በደስታ የሠከረ እና በሹመት ተስፋ የመረቀነ ስሜታዊ በሚበዛበት የለውጥ ሠሞን በአካልም በአዕምሮም በዕጅጉ እንደሚደክሙ ግልፅ ነው ። ታዲያ ድካም ና ግርግር ከጠቢብ ሊሠውሯቸው የሚችሉትን አንዳንድ እንከኖች ወረድ ብለው እንደኔ ካለ ማይም ሊያገኙ ይችላሉ ና ፤ ከርስዎ የትምህርት ዝግጅት ፣ ፈጣሪ-ሠጠሽ የማስተዋል ጥበብም ሆነ ከፍተኛ የመንግስት ስራ ልምድ አንፃር ሲታይ ጃሂል የምባል እኔ ያለኝን ስጋት ልጠቁምዎ ወደድኩ ።
ፅሁፌን ቁምነገር አግኝተውበት ስጋቴ ስጋትዎ ከሆነ የመራኄ መንግስት መላ ያበጁላታል ፤ መናኛ ሆኖ ከታይዎ ደግሞ ‘የጃሂል ነገር’ ብለው ይለፉት ፤ እኔ ግን ልቀጥል
እርስዎ ክስተት ሆነው ይኼ ህዝብ ጓዳ ለጓዳ ብቻ እንዲያንጎራጉረው ተፈርዶበት የነበረውን የፍቅርና የህብረት ዜማ ላንቃው እስኪሰነጠቅ ድረስ ባደባባይ እንዲያቅራራበት ከፈቀዱ ወዲህ እርሰዎ በኩርፊያ ለንቦጩን የጣለን በማባበል እና የተገፋን በመለማመጥ በተጠመዱበት ወቅት ፤ ዜማውን መልመድ ያልቻሉ እና መልመድ እንዳይችሉ ሞገድ የሚለቀቅባቸው ወገኖች ከነአካቴው መሠረቱን ለውጠው የሀዘን እንጉርጉሮ በማድረግ ማላዘን ከጀመሩ ሠንብተዋል ።
ዳሩ ግን ይኼ በየትኛውም ከግለኝነት ወደ ህብራዊነት በሚደረግ የለውጥ ጉዞ የተለመደ በመሆኑ እርስዎ እንደነሡ ሥጋት ሌላ ዜማ ይዘው እስካልመጡ ድረስ በጊዜና ርስዎ በያዙት የሚታይ ዕውነት እየታረቀ ዜማው እየተለመደ መጥቶ ምሉዕና ስሙር የሆነ የገነት መዝሙር እንደሚሆን እምነቴ ነው ። እስከወዲያኛው ሊለምደው ያልቻለውም ወይ በብዙሀኑ ጣዕመ ዝማሬ ጎርናና ድምፁ ተውጦ ይቀራል ፤ አልያም ከብዙሀኑ በላይ አቅራራለሁ ሲል ላንቃው ተዘግቶ እንገላገላለን ።
የኔ ስጋት ወዲያ ነው ። አዎን ወዲያ….
የኔ ስጋት ሠርክ የእያንዳንዱ አገር ስርዓት ወደ አለም አቀፍ ስርዓት የሚደመር ሳይሆን ፥ የእያንዳንዱ ሉዓላዊ ሀገር ስርዓት የነሡ ( ቀድመው የነቁት? ፥ የበቁት?) አገራት ስርዓት ንዑሣን ክፍላት አድርገው የሚመለከቱ “ባለከባድ ሚዛን” መንግስታት ናቸው ።
በየትኛውም የታሪካችን ገፆች ላይ ለሚታዩ ሥርዝ ድልዞች ንቁ ተሣታፊ የሆኑት እኚህ መንግሥታት እንደ ትናንቱ ዛሬም እርስዎ የሚፅፉትን ታሪክ ለመደለዝ ላጲሳቸውን አሹለው እደጃችን ተገትረዋል ብዬ ለማመን ምክንያት አለኝ ።
ለዚህ ደግሞ ከመቸውም ጊዜ የበለጠ አመቺ ሆኖ ያገኙት ይኽ ሃሣብን በነፃነት ለማንሸራሸር የተፈቀደበት የርስዎ አመራር ወቅት ነው ። (ጅምሩ ከርስዎ በፊት በነበሩ አመራሮች እንደሆነም ሳልክድ ፥ እርስዎም የነሡ ውጤት በመሆንዎ )
ነፃነት አገርን ለማዳን ቁልፍ የሆነውን ያህል ደካማ ጎንን ጥጉን ይዞ ለሚከታተል ጠላትም ወሣኝ መሣሪያ ነው ። ለናሙና ያህል የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ቢታፈን ኖሮ የሩዋንዳ ሰቆቃ የሠማነውን ያህል ላይሆን ይችል እንደነበር ይታመናል።
ይኸንን ሁናቴ በአገራችን ያለፈው ስርዓት ና አሁን በቅርቡ በከፊል ያለፈው ስርዓት የመጀመሪያ ዓመታት የነበሩትን አንፃራዊ ሃሣብን በነፃነት የማቀንቀን ዕድሎች እንደክፍተት ተጠቅመው አገርን ያህል ቁምነገር የተሸከሙ የአገር ልጆች በተራ ቃላት ስንጠቃና በግላዊ ምስል ፍላጎት ከፋፍለው ማባላታቸው አሁን ድረስ ምስሉና ጠረኑ ያልተዘነጋ ትዝታችን ነው ። ይኽ መርዝ አሁንም ድረስ ከደማቸው ያልወጣ ሠዎች እንዳሉ በሠሜን አሜሪካ ቆይታዎ የታዘቡ ይመስለኛል ።
የነዚህን ሠዎች መርዝ ምንያህል አንጠፍጥፈው ካልተመረዘውና መርዙን ከተፋው ህዝብ ጋ እንደደመሯቸው እርስዎ ያውቃሉ ። ለመራዦቹ ግን የተተፋውን መርዝ መልሶ አቀናብሮ በማስቋጠር ያዲያቆኗቸውን ማቀሰስ ቀላል መሆኑን እንዳይዘነጉብኝ ።
ክቡርነትዎ
እነዚህ ሠዎች በአሁኑ ወቅት በጃቸው ያለው ካርታ
እንደአብዮቱ ዘመን ‘ሸ’ ፍላወር እና ‘ቸ’ ጦር አይደለም። ወይንም ደግሞ እንደ አንቀፅ 39 ያለ ፋራ ትሪስ አይደለም።
አሁን በጃቸው ያለው ፉንጥ ‘ዘ-ረ-ኝ-ነ-ት’ ነው። ይኼ ደግሞ ለነሡ የተጋጣሚንና የሚሣቡትን ካርዶች አውቀው እንደመጫወት ቀላል መሆኑን ተዝካሯ በቅጡ እንኳን ሳይወጣላት ‘እኚህ ነበሩ’ የመባል ወግ የደረሳት ዩጎዝላቪያ እማኝ ነች። ከጎረፈው ደም እና ከተከሰከሰው አጥንት ጀርባ ያገኙት የተበላለተች አገርና ጥርሱን ያገጠጠ ችጋር ነው ።
ወደኛ ስመልስዎ ሁሌም ለለውጥ አዲስ ልብስ ስንቀይር ካርዳችንን እንዲያዩ የሚላኩት እንደ ኸርማን ኮኽን (ይኽ ሠው ቀደም ብሎ የለካከፈውን አገር የማመስ ተልዕኮ በሽግግሩ ወቅት ተመልሶ ኤርትራን በማስገንጠል ላይ ጉልህ ሚና ተጫውቶ ነጥብ አስይዞ መሄዱ ከርስዎ ንቁ ዐይን የሚሠወር አይመስለኝም) ያሉ ሰዎች ብቅ ብለዋል ። ብቅ ማለት ብቻም ሳይሆን ስስ ብልቶቻችንን የወላጅ ያህል ስለሚያውቁ በቀላሉ ሊፈረካክሱን የሚችሉበት ዕድል አግኝተዋል ።
እነዚህ ሰዎችና የሚወክሏቸው መንግስታት እርስዎ ወደ ስልጣን ሲመጡ አለኝታነታቸውን በማሣየት መተማመንዎትን
ከፍ አድርገውልዎ ከሆነ መልካም፤ ነገር ግን ሙሉ ልብዎን
ሠጥተው በነሡ በመተማመን የአገርዎን ላት ከደጅ እንዳያሣድሩ ከታሪክ ተሞክሯችን የሚያውቁትን ላስታውስዎ
. በHewitt treaty አጤ ዮሐንስ አራተኛን እንግሊዞች የራሳቸውን ጠላት ለንጉሡ አስታቅፈው በምላሹ በጥቁርና ነጭ የተቀመጠውን ያልደረቀ ውል ሸምጥጠው የሚጠበቀውን ወዳጅነት በመንፈግ የሣቸውን አናት ለድርቡሽ፤ የአገሪቱን አናት (ኤርትራን)ለጣልያን መስጠታቸው፤
.ጣሊያኖች ሚኒልክን ‘የወዳጅነት..’ የሚል ጣፋጭ ርዕስ ባለው “ስምምነት” ውስጥ ሻጥ ባረጓት አንዲት አባይ አንቀፅ ሉዐላዊነታችንን ሊገፍፉን ከጫፍ ደርሰው እንደነበርና በዚህም መዘዝ አያቶቻችንን በደምና በአጥንት ከባድ ዋጋ ማስከፈላቸው እና ኤርትራን እስከወዲያኛው ያቆራረጡበትን መንገድ አደላድለው መሄዳቸው፤
.ሶቭየቶች ኢትዮጽያንም ሶማሊያንም ትጥቅ እያቀበሉ በሁለቱ አገሮች ልጆች ደም ጢባጢቢ መጫወታቸውን ፤
.በኅብረተሰባዊነት የመጨረሻ ዘመናት ባገኟት ቀዳዳ ራሳቸው ወጥነው ራሳቸው ባከሸፉት የይምሠል መፈንቅለ መንግስት ለአገሪቷ ለራሷ የከበዱ ምርጥ ‘ጥቂት’ ጄነራሎች
አስጨርሰው በውድም ይሁን በግድ የተገኘውን በቋፍ የነበረ ብሔራዊ አንድነት ለአደጋ ጥለው መዞራቸውን
.ከዚያም የኤርትራን “ነፃነት” ከስር ከስር አካልበው ዋናዉን እና የግጭት መነሻ የሚሆነውንና የሆነዉን የድንበር ማካለል ቸል አስብለው “ጥይት አይጮህም ” ያለውን መሪ የሚያሸማቅቅ ዕልቂት እንዲፈጠር በር መክፈታቸውንና በበሩም ዘው ብለው ገብተው በገሀድም በስውርም እዚህ ግባ ከዚህ ውጣ፤ እዚህ ድረስ እዚያ እንዳትደርስ እያሉ ከወጭ ቀሪ የደም ጭቃና ጥላቻ አስቀርተው በጓሮ በር ዞረው ዳኛ በመሆን ያሻቸውን መወሠናቸውን በማስታወስ
ከዚህ በኋላ አይሞክሩትም ብለው እንዳይዘናጉብኝ ደጋግሜ እማጠንዎታለሁ።
ክቡርነትዎ
እኚህ ኃያላን ወደ አገራችን የፖለቲክ ሜዳ ብቅ የሚሉት በአገራችን ወሣኝ የታሪክ ምዕራፎች ሠሞን ሲሆን ፥ በተለይ ደግሞ ብሔራዊ አንድነት በሚቀነቀንባቸው ንጋጋት ላይ ደማቸው ይሞቃል ፤ እንዳሁኑ ህዝብ በአምስት በስድስት ሃሣብ ሲከፋፈልላቸው ደግሞ ነገሮች ፍራሽ በፍራሽ ይሆንላቸዋል ። በነፃነት ትንፋሽ መሀል የመርዝ ሽቷቸውን ለማርከፍከፍ ከቢሯቸው እንኳ መንቀሳቀስ አይጠበቅባቸውም ።
ክቡርነትዎ
ነገሬን ለመሰተር ስጋቴ ያልኳቸው አካላት ሁለት ወሣኝ ካርዶችን ይዘው እደጃችን ቆመዋል ፤
ከብዝሀነታችን የተመነዘረ አድፍጠው ሲያለማምዱን የከረሙት ዘረኝነት እና ነገርን በፈለጉት መጠን ወደፈለጉበት የሚያነፍሡበት የማህበራዊ ሚዲያ ቴክኖሎጂ።
እኚህ ሁለቱ የኃይል ሚዛኑን ለእነሡ እንዲያደላ የሚያደርጉት ቢሆንም ክቡርነትዎ በአገርኛ ጉዳይ ተጠምደው ካልተዘናጉ አሊያም በአይዞህ ባይነታቸው ና በአጉል ቃልኪዳኖቻቸው በተለመደው ኢትየጵያዊ የዋኅነት ካልተታለሉ በኃይል ሚዛን ተበልጦ ድል መንሣት ዕንጀራችን ስለሆነ ትኩረት ሰጥተው እንዲንቀሳቀሱና የተደገሠልንን የመበጣበጥ ፅዋ ከኛ እንዲያርቁ አሁንም ደግሜ እለምንዎታለሁ። በተለይ በአገራችን የገበያ ግርግር ወቅት የማይጠፉና አፍሪካ ላይ ሡማቸውን ለዘመናት የተከሉ ሠው ከዚህ ሁሉ የፍቅርና የምህረት ድግስ ይልቅ ቀልባቸውን የሣበው የኦጋዴን ጉዳይ መሆኑ በዕጅጉ ሊያሳስብዎት ይገባል ብዬ አምናለሁ ።
መለስንና ኢሳያስን በማንቆለጳጰስ ጀምረው በንፁሃን ደም አጨማልቀው የተለዯቸው እኚህ ሠው እርስዎንም በማሞካሸት ሠንብተው ሠሞኑን ደግሞ በሶማሊላንድ መነጠል የተገኘው “በረከት” እንዴት ለኦጋዴን ዋስትና እንደሆነ በትዊተር ገፃቸው ሹክ በማለት የመጨረሻው መጀመሪያ የመሠለኝን መርዝ እንደዋዛ በተን አድርገዋል ።
(መልዕክቱ በተለጠፈ በ3 ወራት ዉስጥ በኦጋዴን የመገንጠል ወሬ ና ተያይዞም ሁከት መፈጠሩ በፅሁፉ ቅንፍ ውስጥ የተዶለት ነገር ይጠፋ ይሆን? ወይስ አጋጣሚ?)
ክቡርነትዎ
ይኼን የማይደርስዎ የኤሌክትሮኒክ ደብዳቤ አየር ጥሎት ካነበቡት በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀቴ ፣ በወግ ማንዛዛቴ ና ቃላት አሳመርኩ ብዬ ነገር አበላሽቼ ከሆነ ለጦር ሠባቂ ና ሜንጫ ነቅናቂ የሠጡትን ይቅርታ አይነፍጉኝም ብዬ እተማመናለሁ።
ስጋቴ በክቡርነትዎ ዘንድ ሚዛን ደፍቶ እንደሆነ ግን የሚወዷትንና የምወዳትን አገር ከማያንቀላፉ ጠላቶቿ ይጠብቋት ዘንድ ይንቀሳቀሱ።
መንግስታዊ መላው የርስዎ ቢሆንም እንደ መነሻ ግን ግለሠቡ ወይም የሚወክሉት አካል ማብራሪያ እንዲሠጥዎት በመጠየቅ ቢጀምሩ መልካም ነው ባይ ነኝ።
የመጣጥፉን ሙገሣውንም ትንኮሳውንም ምናልባት ካላዩት ብዬ ከትዊተር ገፃቸው መንትፌ አባሪ አድርጌ ሠድጀልዎታለሁ።
በጭብጨባና በቅርቡ እንደሚግተለተልለዎ በማምነው ሽልማቶች ሳይዘናጉ ፈጥነው ይመክቱ። መሪን አስጊጠው ሸልመው አገር መቀማት እንጀራቸው መሆኑን ከማዲባ አገር ሳይስተማሩ የሚቀሩ አይመስለኝም።
ለጤናዎና ለአስተዳደር ብልሀትዎ ፈጣሪ ከጎንዎ እንዲሆን እፀልያለሁ ።
/አክባሪዎ አንተንሳይ መስፍን
ከሳማ መንደር-ደሴ/