የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የሰባት አመራሮችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን አስታወቀ

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት የሰባት አመራሮችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን አስታወቀ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የ7 አመራሮችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን አስታወቀ።ምክር ቤቱ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አብዲ መሃመድ ኡመር(አብዲ ኢሌ)ን ጨምሮ ሌሎች ስድስት አመራሮችን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

 የጅግጅጋ ከተማ ከንቲባ የነበሩት አቶ ኢብራሂም ሙባረክ፣የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ኢብራሂም፣የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ አብዲጀማል አህመድ እና የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ራህማ መሃመድ ሀይቤ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳ ግለሰቦች መካከል እንደሚገኙበት ታውቋል።

የክልሉ ም/ቤት ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚንዳት አብዲ ኢሌ በመጨረሻዎቹ የስልጣን ወራት ያዋቀራቸው 99 ወረዳዎችና 22 የክተማ አስተዳደሮች ቀድሞ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ምክር ቤቱ መወሰኑም ተገልጿል።

 የኢሶህዴፓ ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሽዴ ትናንት ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በቀጣይም የህዝብን ተጠቃሚነትና ፍትህን ያረጋግጣሉ ተብሎ የታመነባቸው አመራሮችን በመመደብ በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ይሰራል ብለዋል፡፡

 በሌላ በኩል አዲሱ የክልሉ አስተዳደርና በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት የገባው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ርስ በርሳቸው ሳይገፋፉ በክልሉ ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። በስምምነቱ መሰረት ኦብነግ በክልሉ በነፃነት እንዲንቀሳቀስ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱ ተገልጿል።

 የኦብነግ ወታደሮች የሚደገፉበትንና ከህብረተሰቡ ጋር የሚቀላቀሉበትን ሁኔታ እንደሚመቻችና ሁለቱም ወገኖች ከጠብ አጫሪነት ተቆጥበው ለአካባቢው ሰላም ይሰራሉም ተብሏል።

ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ቅዳሜ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አብዲ ኢሌን ጨምሮ በክልሉ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አመራሮች በህግ እንደሚጠየቁ መግለጻቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY