አቶ በረከት ‹‹ብአዴን አቅጣጫውን ስቷል/ቀይሯል›› ያለው ሐቅ/እውነት/ልክ ነው፡፡ /መላኩ አላምረው/

አቶ በረከት ‹‹ብአዴን አቅጣጫውን ስቷል/ቀይሯል›› ያለው ሐቅ/እውነት/ልክ ነው፡፡ /መላኩ አላምረው/

ባለፉት ሦስት ዐሠርት ዓመታት ብአዴን አቅጣጫ የሚሰጠው ከሕወሓትና ከእነ አቶ በረከት ነበር፡፡ አቅጣጫውም አማራን የማፈን፣ የማደድ፣ የማሰር፣ የማንኮላሸት፣ ማንነቱና ሀብቱ ሲዘረፍ ዝም ብሎ የማየት…›› ነበር፡፡ ከዚህ አቅጣጫ የሚወጣ አመራር ከኃላፊነት ከመነሳት እስከ ከሥራ መባረርና መታሰር ይደርስበት ነበር፡፡

አሁን ግን ብአዴን አቅጣጫ ቀየረ፡፡ አቅጣጫውን ከእነ አቶ በረከት ሳይሆን ከሕዝቡ መቀበል ጀመረ፡፡ ሕዝቡ ‹‹የታሰሩት ይፈቱ፣ የተሰደዱት ይመለሱ፣ የተጎዱት ይካሱ፣ የአማራ ማንነትና ክብር ይጠበቅ…›› የሚል አቅጣጫ ሰጠ፡፡ ብአዴንም ይህን አቅጣጫ ተቀብሎ መተግበር ጀመረ፡፡ አቅጣጫ ቀየረ፡፡

ድሮ ብአዴን አቅጣጫ የሚሰጠው ‹‹በሌሎች ክልሎች የሚኖረው አማራ ቢፈናቀል፣ ቢታሰር፣ ቢገደል….›› አይደለም መቃወም ቃልም ትንፍሽ እንዳይል ነበር፡፡ ይህን የሚቃወሙ ጋዜጠኞችንና የማኅበረሰብ አንቂዎችንም እንዲያስር ወይም/እና ሲታሰሩ ዝም እንዲል ነበር፡፡ ብዙ አማራ ከሚኖርበት ከኦሮሚያ ክልል አመራሮች/ከኦህዴድ ጋርም ‹የተጠፋፊነት› (ትምክህተኛነትና ጠባብነት) እንጅ መልካም ግንኙነት እንዲኖረው አይፈለግም ነበር፡፡ አሁን ብአዴን አቅጣጫውን ቀይሮ… በተለይ ከኦህዴድ አመራሮች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መሥራት ጀመረ፡፡ አቅጣጫ የሚቀበለው ከቀድሞ አመራሮቹ ሳይሆን ከቄሮን ከፋኖ እንዲሁም ከሁለቱ (ከአማራና ከኦሮሞ) ሕዝብ የጋራ ፍላጎት ሆነ፡፡ ሁለቱ ሕዝብ መቼም እንዳይስማሙ እንዲሠራ የተሰጠውን አቅጣጫ ትቶ የሁለቱን ሕዝብ አንድነትና ፍቅር መስበክ ጀመረ፡፡ ፋኖዎች ጎንደር ላይ ‹‹የኦሮሞ ደም የእኛም ደም ነው›› ያሉትን ግሩም አቅጣጫ ተቀብሎ ‹‹የኦሮሞ አመራር የእኛም አመራር ነው፤ እነርሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሁኑ›› አለ፡፡ በተግባርም ዶ/ር ዐቢይን በመምረጥ አረጋገጠ፡፡ ብአዴንማ አቅጣጫ ቀይሯል፡፡

ከእነ አቶ በረከት የሚቀበለው አቅጣጫ ‹‹የአማራ መሬቱም ማንነቱም ቢወሰድ ዝም እንዲል›› ነበር፡፡ እንኳን የሀገር ውስጥ ተስፋፊዎች ሱዳንም መጥቶ የአማራን መሬት መውሰድ ከፈለገ አይደለምና መቃወም ማጉረምረምም አይፈቀድለትም ነበር ብአዴን፡፡ አሁን አቅጣጫ ቀይሮ ‹‹የአማራ መሬቱም ማንነቱም ይከበር›› አለ፡፡ ጭራሽ የመከላከያን እገዛ ሳይጠብቅ በአርሶ አደር ነፍጠኞች ብቻ የሱዳንን መከላከያ መክቶ መሬቱን ማስጠበቅ ጀመረ፡፡ አቅጣጫ ቀየረ፡፡

ድሮ አይደለም ተቃዋሚ ፓርቲ ተቃዋሚ ግለሰብ በአማራ ምድር ከታየ… ‹‹ያዘው፣ እሰረው፣ ግረፈው…›› የሚል አቅጣጫ እየተቀበለ ብአዴን አማራውን ለውጥ እንዳያይ ይሠራ ነበር፡፡ የቁርጥ ቀን ልጆቹን እየገበረ እንዲኖር ተፈርዶበት ነበር፡፡ አሁንማ… በአዴን አቅጣጫ ቀይሮ ጭራሽ ‹‹የአማራን ማንነትና መሬት አስጠብቃለሁ›› የሚልን ‹‹አብን›› የሚባል ፓርቲ እንዲመሠረት ፈቀደ፡፡ አብን ከክልል አልፎ በአዲስ አበባ፣ በየዞኑና በየወረዳው ሁሉ ቢሮውን ከፈተ፡፡ አመራሮቹን መረጠ፡፡ እና ብአዴን አቅጣጫ አልቀየረም?

ጭራሽ እነ በረከት ያሰደዷቸውን እና በውጭ ሀገር በስደት ለአማራ ግፍና መከራ መቆም በሰላ ብዕራቸው ሲሞግቱ የነበሩትን ጋዜጠኞችና ‹አክቲቪስቶች› ተቀብሎ በፕሬዝዳንቱ ቢሮ በክብር ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› እያለ እየታየ… ለብአዴን ከዚህ በላይ አቅጣጫ መቀየር አለ እንዴ???
(ለነገሩማ እንኳን አቅጣጫ… ስም፣ አርማ፣ ሰንደቅ አላማና ርዕዮተ ዓለምስ ሊቀይር አይደለም እንዴ!!!)
—›
-›
እናም አቶ በረከት ‹‹ብአዴን አቅጣጫ ቀይሯል›› ያለው ሐቅ/እውነት/ልክ ነው፡፡
ባይሆን የዋሳ ሌሎች ነጥቦች ላይ ነው፡፡
ለምሳሌ፡- ‹‹ብአዴኖች ሊቀመንበራችን ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሲገባው አንተ ስላልደገፍኸው ሳይመረጥ ቀርቷል፡፡ እኛ አጋዥ የሌለን የሙት ልጅ ሆነናል ብለውኛል›› አለ፡፡ ቀጥሎም ‹‹የአማራን ጥቅም አላስከበርህም የተባልሁት ደመቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ባለማስደረጌ ነው›› አለ፡፡ ይህች ቅጥፈት ነች፡፡ አቶ በረከት የአማራን ጥቅም አይስጠብቅም የተባለው ገና ድሮ ነው፡፡ አማራ በአማራነቱ ብቻ ሲታሰር፣ ሲፈናቀል፣ ሲገደል… ዝም በማለቱና ምን አልባትም ይህ እንዲደረግ በማድረጉ ነው፡፡ እንጅማ… ሲጀመር የትኛው አማራ ብአዴን ጠቅላይ እንዲሆን ተመኝቶ ያውቅና ነው? የአማራ ጥቅም የሚጠበቀው አቶ ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ ነው ብሎ የሚያምንስ አለ እንዴ? የማይመስል ምክንያት ነው፡፡ ይህን እንኳን በልባችን በጆሯችንም አንቀበለውም፡፡

በመሠረቱ እነ አቶ በረከት ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ለማደረግ የፈለጉት አቶ ሽፈራውን እንጅ ዶ/ር ዐቢይን አይደለምና… ‹‹እኛ እያለን እነርሱን/ኦሮሞዎችን አስመረጥህብን›› ብለው ሊከሱት አይችሉም፡፡ ይህ (ለእኔ) ‹‹በብአዴንና ኦህዴድ መደጋገፍ ከፍ ያለውን የአማራ እና ኦሮሞ መተባበር ለመስበር የተሸረበ ሴራ›› ነው፡፡ ኦሮሞዎች ‹‹ለካንስ ብአዴን ዶ/ር ዐቢይ እንዲመረጥና ኦሮሞ እንዲመራ አይፈልጉም ነበር›› ብለው እንዲጠራጠሩ ለማድረግ የተወረወረች ቃል ነች፡፡ ሐቁ ግን… እነ ደመቀ በተግባር ኦህዴድን መርጠው ጠቅላይ አድርገዋል፡፡ አቶ በረከትማ ‹‹ዶ/ር ዐቢይ ለኢትዮጵያም ለኢህአዴግም አይመጥንም›› ብሎ እንደተናገረ ይታወቃል፡፡ አቶ ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሆን የተቃወመው ኦሮሞን ለመምረጥ ሳይሆን ከሕወሓት ጋር ተባብሮ አቶ ሽፈራውን ጠቅላይ አድርጎ የእጅ አዙር ግዛቱን ለማስቀጠል ነበር፡፡ ከወሬ ይልቅ ተግባር ምስክር ነው፡፡ ብአዴን አስቀድሞ አቶ ደመቀ እንደሚመረጥ አስወርቶ ከሆነም ለሴራ ነው፡፡ ሕወሓትንና አቶ በረከትን ለማዘናጋትና በመጨረሻ ጉድ ለመሥራት፡፡

(ደግሞ እኮ ለአቶ በረከት ምሥጢር ሆኖበት ካልሆነ በቀር ብአዴን ኦህዴድ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆን የወሰነው ጥር ላይ ነው፡፡ አልሰሜን ግባ በለው አሉ፡፡ የባሕር ዳሩ የኦሮ-ማራ ጉባኤ እኮ የተከናወነው ለስምምነታቸው ማጠናከሪያ ነው፡፡ ብቸኛው ጊዜያዊ መፍትሔ ከኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መምረጥና የሁለቱን ሕዝብ አንድነት ማጠናከር ነበርና፡፡)

በሌላ በኩል አቶ በረከት ያለው ሁሉ እውነት ነው ብንል እንኳን ወሬኛነት ነው፡፡ የድርጅት አጋሮቹን ምሥጢር እየዘረገፈ ማን ሊደግፈው ነው? ከትልቅ ሰው የማይጠበቅ አሉሽ አሉሽ ነው፡፡

የአሉሽ አሉሽ ወሬው በተለይ ‹‹ኢሳያስ ሕወሓቶችንና እነ በረከትን አስወጧቸው እንዳለ ሰምቻለሁ›› በሚለው ይቀጥላል፡፡ ይህ (ለእኔ) ተራ አሉቧልታ ነው፡፡ ሲጀመር እነ ዶ/ር ዐቢይ የቀድሞ አመራሮችን ማሰናበት የጀመሩት የኢትዮ-ኤርትራ እርቅ ከመጀመሩና ዶ/ር ዐቢይም ሆነ ኃ/ማርያም ደሳለኝ ልዑካንን ይዘው ኤርትራ ከመሄዳቸው በፊት ነው፡፡ በምን መስፈርት ነው እነ በረከትን ማስወገድ የተጀመረው በኢሳያስ ምክር ሆኖ የሚወሰደው… ወይ ይህን ምክንያት ካመጡት አይቀር… ቀድሞ ከዓመት በፊት የተደረገ ነው ቢሉ ይሻል ነበር፡፡ የማይመስል ነገር ነው፡፡ (ኢሳያስ ግን አጋጣሚውን ካገኘ አይደለም በምክር በበትርም እንደሚጥላችሁ የታወቀ ነገር ነውና መክሮም ከሆነ የሚገርም አይደለም፡፡)
ሐቁን ያስቀመጥኸው ‹‹ብአዴን አቅጣጫውን ቀይሯል›› ከሚለው ላይ ነው፡፡
=>

መውጫ፡-
አቶ በረከት አጀንዳ መፍጠሩንና በመረጃ ማወናበዱን እንደ አንድ የትግል ስልት አድርጎ መቀጠሉ አይቀርም። ብዙ ‹‹ምሥጢራ መረጃ›› የሚላቸውን ነገሮች መልቀቁም የማይቀር ነው። አላማው ወደ ብአዴን መመለስና አማራን መምራት አይሆንም፡፡ ብአዴንን በማደናበርና የሕዝብ ድጋፍ በማሳጣት ከለውጥ ጉዞው ለማደናቀፍ እንጅ፡፡ እስከአሁን የብአዴን አመራሮች በቂ መልስ ሰጥተዋል። ካሁን ወዲያ ወደ ግን ሥራ ብቻ ቢያተኩሩ ይመከራል። የታሙበትን ‹‹የአይችሉም›› ክስ ሐቅ እንዳልሆነና ብቃት እንዳላቸው ማስመስከር አለባቸው። ሕዝብ ተግባርን እንጅ ወሬን አይከተልምና፡፡

LEAVE A REPLY