የሀዋሳ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባንና የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ ጨምሮ...

የሀዋሳ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባንና የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ ጨምሮ 100 ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የቀድሞውን የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ፣ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ቴዎድሮስ ገቢባን ጨምሮ በ100 ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቱን የፌዴራል አቃቢ ህግ ገለጸ። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ችሎት በሀዋሳ ከተማ የተከሳሾቹን የክስ ሂደት እየተመለከተ እንደሚገኝ ፋና ዘግቧል።

በግለሰቦቹ  ላይ የተመሰረተው ክስም በሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ በአንዳንድ የሲዳማና የወላይታ ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር በማድረግ፤ የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው መሆኑ ታውቋል።

በዛሬው እለት ችሎት ከቀረቡት መካከል የሀዋሳ ከተማ ማረሚያ ቤት ሃላፊን ጨምሮ ስድስት የማረሚያ ቤቱ ሰራተኞች ይገኙበታል ተብሏል። ችሎቱም በማረሚያ ቤት ውስጥና በሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ ለረጅም ዓመታት በአብሮነት የኖሩትን የሲዳማና ወላይታ ብሄረሰብን በማጋጨት ለሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም እጃቸው አለበት የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ እየተመለከተ ይገኛል።

ባለፈው ሰኔ ወር በሀዋሳ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ወላይታ ሶዶ፣ ቀቤና ሌሎች በርካታ ቦታዎች ተዛምቶ የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ሲያልፍ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎችም ከቀያቸው በግፍ መፈናቀላቸው ይታወሳል።

LEAVE A REPLY