አና ጎሜዝ፡- ይሄ ምን ጥያቄ አለው፤ አቶ በረከት ለፍርድ ነው መቅረብ ያለበት። እርግጥ ነው ብቻውን አይደለም፤ ግን ዋናው ሰው ነው፤ ለፍርድ የማይቀርበው ለምንድነው? አሁን ለውጥ ላይ ያለው መንግሥት ወደዚህ ድምዳሜ ላይ ይመጣል የሚል ተስፋ አለኝ።
ጥያቄ፡- የአቶ በረከት ስምኦንን ጉዳይ ለጊዜው ገሸሽ እናድርገውና፤ ሌላ ጥያቄ ላንሳ፤ በ2012 አቶ መለስ ዜናዊ በብራስልስ መሞታቸውን ለኢሳት መረጃ ያቀበሉት እርስዎ ኖት እንዴ?
አና ጎሜዝ፡- ሊሆን ይችላል። መረጃው ነበረኝ። ያኔ ማንም መለስ ዜናዊ መታመሙን ቀርቶ አገር ውስጥ አለመኖሩንም የሚያውቅ ብዙ ሰው አልነበረም። መሞቱንም ብዙ ሰው አያውቅም ነበር። የነበረኝ መረጃ እጅግ አስተማማኝ የሚባል ነበር። ያን መረጃ ኢሳት የተጠቀመበት ይመስለኛል። ቀደም ብሎ መሞቱን የነገረኝ ምንጭ እጅግ የምተማመንበትና አስተማማኝ ነበር።
ጥያቄ፡- ስለዚህ አቶ መለስ የሞቱት በመንግሥት ከተገለጸው ቀን ቀደም ብሎ ነው ብለው በእርግጠኝነት መናገር ይችላሉ?
አና ጎሜዝ፡- ያለምንም ጥርጥር። መጀመርያ ብራዚል ለሕክምና ተወስዶ ነበር። ከሐኪሞቹ ጋር በብራዚል ተገናኝቷል። የሕመሙ ሁኔታ የተገመገመው ብራዚል በሚገኙ ስፔሻሊስቶች ነበር። ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ተነገረው። ከዚያ በኋላ ነው ብራስልስ እንዲመጣ የተደረገው። እኔ መረጃውን ባገኘሁበት ቅጽበት ራሱ ከቀናት በፊት መሞቱ ነው የተነገረኝ። ሆኖም በምሥጢር ተይዞ ነበር።
ጥያቄ፡- ትክክለኛ ቀኑን ያስታውሱታል?
አና ጎሜዝ፡- አላስታውስም
ጥያቄ፡- የትኛው በሽታ ለሞት እንደዳረጋቸውስ ያስታውሳሉ?
አና ጎሜዝ፡- እ…አንዳች የካንሰር ዓይነት ሕመም ሳይሆን አይቀርም፤ በትክክል ምን እንደነበር እርግጠኛ አይደለሁም።
ጥያቄ፡- መንግሥት ለምን መሞታቸውን ዘለግ ላለ ጊዜ መደበቅ የፈለገ ይመስልዎታል?
አና ጎሜዝ፡- እነርሱን ነው መጠየቅ ያለብህ። ነገር ግን በአምባገነን መንግሥታት ውስጥ የጠንካራ መሪ ሞት መደበቅ የተለመደ ነው፤ የመለስን ሞት ቀደም ብዬ አውቅ ነበር እያልኩህ አይደለም። እንደሰማሁት መረጃውን ሰጠሁ። ብዙም ሳይቆይ መንግሥትም መሞታቸውን አረጋገጠ። ከዚያ በፊት ግን ስለመታመማቸው እንኳን ለኢትዯጵያ ሕዝብ አልተነገረም ነበር።
ጥያቄ፡- እርስዎ መች ነው ግን ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም የሰሙት?
አና ጎሜዝ፡- በልጅነቴ ነው። በቅኝ ግዛትና ከቅኝ ግዛትም በፊት በነበረው የአገሬ ታሪክ ወስጥ የኢትዮጵያ ስም ገናና ነው። ፖርቹጋሎች ለረዥም ዓመት ኢትዮጵያ በእግር ተጉዘው ለመድረስ ይሞክሩ ነበር። የፕሪስት ጆን አገር ተብላ ትታወቅ ነበር። የፖርቹጋል አሳሾች ትልቅ ጉጉት ነበራቸው፤ ይቺን አገር ለማየት።
እኔ አገሪቱን የረገጥኩት በ97 ምርጫ ጊዜ ነው። የያኔዋ ኮሚሽነር እኔን ወደዚያ እንድሄድ የመረጡኝ ከዚያ በፊት ምንም ዓይነት ግንኙነት ከአገሪቱ ጋር ስላልነበረኝና ገለልተኛ ስለነበርኩ ነበር፤ በቆይታዬ አገሪቱን ተዘዋውሬ ሕዝቡንና ታሪኩን ስረዳ ይህ ሕዝብ ዲሞክራሲ ይገባዋል የሚል እምነት አድሮብኛል።
እኔ በአገሬ በጭቆና መኖሬ በጭቆና የሚኖር ሕዝብን እንድረዳ ረድቶኛል። ጨቋኞች ቋንቋቸው ይገባኛል። ዲሞክራሲ የሚል ቃል ያበዛሉ፤ ሽግግር ላይ ነን ይላሉ። በዚህ ጉዳይ ከመለስ ጋር ረዥም ውይይትን አድርገናል።
ጥያቄ፡- ዘለግ ያለ ቆይታ ከአቶ መለስ ጋር ከነበርዎ አቶ መለስን ያውቋቸዋል ማለት ነው፤ አቶ መለስን እንዴት ይገልጿቸዋል?
አና ጎሜዝ፡- ብልህ አጭበርባሪ (Deviously smart) ነበር፡፡
ጥያቄ፡- ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳልዎ ይታማሉ፡፡
አና ጎሜዝ፡- (ዘለግ ካለ ሳቅ በኋላ) ይሄ ፌዝ መሆን አለበት። ብርሃኑን አውቀዋለሁ። ባለቤቱን ዶክተር ናርዶስም አውቃታለሁ። ኢትዮጵያ እያለሁ ነው የማውቃት። እሷም ታውቃለች። አሁን የምነግርህን ታሪክ እሷ ራሱ ልትነግርህ ትችላለች። በ2005፣ ጁን 7 ሌሊት ጁን 8 ሊነጋ የኾነ ታሪክ ነው፡፡
የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር የነበሩት ቲም ክላርክና ባለቤቱ ቤት ነው ያደርኩት። ያኔ የኔን የሸራተን መኝታ ለብርሃኑ ነጋ ለቅቄ ነው የሄድኩት። ለርሱ ብቻ አይደለም። ባለቤቱም ጭምር። ምክንያቱም ይህን ያደረኩት አደጋ ላይ ስለነበሩ ነው። ሌላ ቦታ ተደብቀው ነበር። የት እንደነበር አሁን አልነግርህም። የተሸሸጉበት ቦታ በመለስ ወታደሮች ሊታሰስ እንደሆነ መረጃ ለአምባሳደር ቲም ደርሶት ነበር። በአምባሳደር ቲም ክላርክና ባለቤቱ ጥያቄ መሠረት የሸራተን ክፍሌን ለብርሃኑና ባለቤቱ ለቅቄላቸዋለሁ።
ጥያቄ፡- ይህ ደርጊትዎ በራሱ በወቅቱ እርስዎ ገለልተኛ እንዳልነበሩ የሚያሳይ አይመስልዎትም?
በፍጹም! በፍጹም! ሕይወቱ በአምባገነኖች አደጋ ላይ ላለ ለማንኛወም ሰው ላደርገው የምችለውን ነገር ነው ያደረኩት። የዶ/ር ብርሃኑና ባለቤቱ ሕይወት እኮ አደጋ ላይ ነበር። ለዚያም ነው አምባሳደር ቲም ክላርክ እኔ ክፍል እንዲቆዩ የፈለገው።
ጥያቄ፡- ብርሃኑን ካነሳን ዘንዳ ወደ ኤርትራ በረሃ መውረዱን ያደንቁለታል?
አና ጎሜዝ፡- ለኔ ሊታገል አይደለም እኮ እዚያ የሄደው፤ ሰዎች ሲገፉ የት ድረስ ሊሄዱ እንደሚችሉ እረዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ አምባገነኖች ላይ ነፍጥ ማንሳት ሊያስፈልግ ይችላል። ማንዴላም አሸባሪ ሲባሉ ነበር። በሰላማዊ ትግል ነው የማምነው፤ ኾኖም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች፥ ምንም አማራጭ በሌለበት ሁኔታ ይህ ሊሆን እንደሚችልም እረዳለሁ።
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያዊ ስም እንዳልዎ ያውቁ ይኾን?
አና ጎሜዝ፡- አዎ ብዙ ሰዎች ብዙ ስም እንዳወጡልኝ አውቃለሁ። በዋናነት «ጎቤዜ» የሚባለውን ሰምቻለሁ (ሳቅ)
ጥያቄ፡- ምን ይሰማዎታል ?
አና ጎሜዝ፡- የሚያኮራ ነው። ሆኖም እኔ ከኢትዮጵያ ጋር የምጋራው ህልምና የሚያኮራኝ ነገር ካለ አንድ ነገር ነው፤ እሱም አገሪቱ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲ ተሸጋግራ ማየት።
ጥያቄ፡- አንዳንድ ቦታ ሰዎች የተቃውሞና የድጋፍ ሰልፍ ሲወጡ የርስዎን ምሥል መያዝ ጀምረዋል።
አና ጎሜዝ፡- ምን ልበልህ …አመሰግናለሁ ስለ እውቅናው፤ ግን በሆነ መልኩ ደግሞ ኃላፊነትም ጭምር ይሰጣል። ስለ ዲሞራሲ ከሚታገሉ ሰዎች ጋር የኔን ምሥል ማየቴ ኢትዮጵያዊያንን በማገዝ እንድገፋበት ነው የሚያደርገኝ፤ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዬ ጥሩ ጅምር ላይ ያለ ይመስላል፤ ነገር ግን አስተማማኝ መሠረት ላይ ገና አልተቀመጠም።
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያዊ ዜግነት የመጠየቅ እቅድ ይኖርዎ ይሆን? ወይም ደግሞ የጡረታ ዘመንዎ በኢትዮጵያ የማድረግ ሐሳብ…
ሳቅ- የኢትዮጵያ ወዳጅ ነኝ። ኾኖም የምትለው ዕቅድ የለኝም፤ ራሴን የማየው እንደዚያ ነው። እኔ ራሴን አንድ የዓለም ዜጋ አድርጌ ነው የምቆጥረው
ጥያቄ፡- በግልዎ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ጀግና እንደሆኑ ይሰማዎት ይሆን?
አና ጎሜዝ፡- እንደዚያ እንደማላስብ ነግሬሀለሁ፤ አሁን የታየውን ተስፋ እንዲለመልም በጣም ተስፋ በማድረግ ላይ ነው ያለሁት።
ጥያቄ፡- ሳስበው ቤትዎ በኢትዮጵያዊ ቁሳቁሶች የተሞላ ይመስለኛል።
እውነትህን ነው፤ አሁን የማወራህ በብራስልስ ቢሮዬ ሆኜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ባንዲራ አለ። በአንድ አርቲስት የተሳለ ቆንጆ የአዲስ አበባ ሥዕልም ይታየኛል፡፡ ቤቴም ቢሆን ኢትዮጵያዊያን ወዳጆቼ የሰጡኝ ማስታወሻዎች ይገኛሉ። በ97 ምርጫ የለበስኩት የምርጫ ታዛቢነት የደንብ ልብስም በማስታወሻነት አለ። በርካታ መስቀሎችም አሉኝ፡፡ ከመርካቶ የገዛኋቸው።
ጥያቄ፡- ወደ አቶ በረከት ጉዳይ አንድ አፍታ ልመስልዎ። ሰሞኑን በአማርኛ መጽሐፍ ጽፈዋል። የሚተርጉምልዎ በጎ ፈቃደኛ ቢያገኙ የማንበብ ፍላጎት አለዎ?
አና ጎሜዝ፡- ብዙ የምሰራቸው ቁምነገሮች አሉ። ብዙ ማንበብ ያለብኝ መጽሐፍት አሉኝ። ለምን ብዬ ነው ዋሾ ነው ብዬ የማምነው ሰው የጻፈውን መጽሐፍ የማነበው። የፕሮፓጋንዳ ፋብሪካ ነው እኮ እሱ። ምናልባት ወደፊት ሥራ ፈት ብሆን ላነበው እችል ይሆናል።
ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በሚያደርጉት የበዛ ተሳትፎ…
አና ጎሜዝ፡- የበዛ አትበል። የበዛ ነው ብዬ አላምንም።
ጥያቄ፡- …… በዚህ ተሳትፎዎ የሚበሳጩ ሰዎች የሉም?
አና ጎሜዝ፡- ኦ! ብዙ ስድቦችንና ማንቋሸሾች በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል ይደርሱኛል። ከመንግስት ሰዎች ግን እንዲያ ያለ ነገር ዐይቼ አላውቅም። እዚህ ብራሰልስ የማገኛቸው ዲፕሎማቶች በመከባበር ነው የሚያወሩኝ። በ2013 አዲስ አበባ ሄጄ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለምሳ ጋብዘውኛል። ሌሎችንም አግኝቻለሁ። የተለየ ነገር አላየሁም። ግለሰቦች ግን ይሳደባሉ። መለስ ዜናዊም ‹‹በኢትዮጵያን ሄራልድ›› ጋዜጣ ያን ሁሉ ገጽ ከተቃዋሚ ብር ትቀበላለች ብሎ ሰድቦኛል፡፡
ጥያቄ፡- ወደ አዲስ አበባ የመምጣት ፍላጎት አለዎት?
ብዙ ወዳጆቼ ለውጡን ተከትሎ እንድመጣ ይጠይቁኛል። ለመሔድ ብዬ አልሄድም። የማግዘው ነገር ሲኖር ያን አደርጋለሁ፤ ሰሞኑን ለምሳሌ ስቶክሆልም ባሉ ኢትዮጵያዊያን ለውይይት ተጋብዣለሁ። እሄዳለሁ።
ጥያቄ፡- ዐብይ አህመድን አግኝተዋቸዋል?
አና ጎሜዝ፡- አላገኘሁትም። እስክንድር ነጋን ግን አግኝቼዋለሁ። በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡
ጥያቄ፦ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል?
አና ጎሜዝ፡- መገምገም የምችለው በማገኛቸው ሰዎች ዐይን ነው። ለምሳሌ አንዳርጋቸው ጽጌ እዚህ አውሮፓ ኅብረት ምስክርነት ለመስጠት መጥቶ አግኝቼዋለሁ። ከዐብይ አሕመድ ጋር ቆይታ እንዳደረገ ነግሮኛል። አሱ በዐብይ ላይ ባሳደረው ተስፋ ተደንቂያለሁ። ለዲሞክራሲ ሕይወታቸውን የሰጡ ሰዎች ዐብይ ላይ ተስፋ ካሳደሩ እኔ ተስፋ የማላደርግበት ምክንያት የለም።
ጥያቄ፡- ተቃዋሚዎች ሥልጣን ቢይዙም ድምጾትን ማሰማቱን ይቀጥሉበታል?
አና ጎሜዝ፦ አዳምጠኝ፤ እኔ በኢትዖጵያ ጉዳይ ኤክስፐርት አይደለሁም። ባየሁት በደል ነው የተነሳሳሁት፥ የዓለማቀፉ ማኀበረሰብ ለኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉጉት ያሳየውን ንቀት ነው እዚህ ውሰጥ የከተተኝ። ያ ነው አጋርነቴን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳደርግ የሚያደርገኝ፡፡እኔ ማንም ይሁን ማን ለኢትዮጵያ ደሞክራሲን የሚያመጣ ልቤን ያሸንፈዋል፡፡ በ97 ያየሁትን የማውቀው እኔ ነኝ።
ጥያቄ፦ከኢትዮጵያ ፖለቲከኞች እጅግ የሚያደንቁትን አንድ ሰው ይጥቀሱ ቢባሉ ያ ሰው ማን ነው?
ብዙ አሉ እኮ! ለምሳሌ የኦሮሞ ወጣቶች ይሄን አመጽ የጀመሩት ጀግኖች ናቸው። ብዙ ድንቅ ኢትዮጵያዊያን አጋጥመውኛል፤ እነ መረራ፣ እነ እስክንድር…
ጥያቄ፡- አንድ ነበር ያልክዎት?
አና ጎሜዝ፦ አንድ ጀግና የለም። ዲሞክራሲ በአንድ ሰው አይገነባም። ብዙ ሰዎች ናቸው የሚገነቡት። እነ አንዳርጋቸው፣ ደግሞ ብርቱካን ሚደቅሳ ድንቅ ሴት ናት። የማይታወቁ ስንት ወጣቶች አሉ። ዐብይ የሚባለውን ሰው መቼ አውቀው ነበር? ሥልጣን ከያዘ በኋላ ነው ስለርሱ የሰማሁት፡፡
ጥያቄ፦ከፖርቱጋል ውጭ በዓለም ላይ ካሉ አገሮች በአንዱ የመኖር ዕድል ቢሰጥዎ የት ይመርጣሉ?
አና ጎሜዝ፦ ተመልከት! አሜሪካ እንደ ዲፕሎማት ስኖር ይህ ዓይነቱ ነገር (ግሪንካርድ) ይቀርብልኝ ነበር። እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር ደስ አይለኝም። ፖርቹጋላዊት ሆኜ ኖሬ መሞት ነው የምፈልገው። ያ ግን ለሌሎችን አገሮች ከመቆርቆር አይከለክለኝም።
/ከቢቢሲ አማርኛ/