በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ውስጥ ሆነን ሁለተኛ ሣምንታችንን ያዝን፡፡ ዕድሜ ለዐዋጁ ገንዘቤም አፌም ዐረፉ፡፡ አሁን አፌን ሰብስቤ በጊዜ ወደቤቴ ከማምራቴ በፊት በየመሸታ ቤቱ እንደጣቃ ስቀደድ አመሽ ነበር፡፡ አንዱ ጆሮ ጠቢ ጠልፎ ቢወስደኝና ድራሼን ቢያጠፋው ለምግብ ያላነሱ ለሥራ ያልደረሱ ልጆቼ ወደ በረንዳ መበተናቸው አይቀርም፡፡ በሌላም በኩል ዐዋጁን ቀድሞ በተዘጋው ኢንተርኔት ሰበብ ብዙ ገንዘብ በቴሌ እበላ ነበር፤ አሁን ግልግል ነው፡፡ ሣር አልበላም እንጂ በዚያም ላይ “እምቧ!” እያልኩ እንደከብቶቹ አልጮህም እንጂ ዕድሜ ለሕወሓት የለዬልኝ የቤትና የዱር እንስሳ ሆኛለሁ – በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ አይሉ ሁለት ዲፕሎማ ይዤ የማልናገር የማልጋገር የወያኔ ጥፍጥፍ ባሪያ ሆኜ መገኘቴ የሰው ልጅ የደረሰበትን ኢትዮጵያዊ የዕድገት ደረጃ ያመለክታል፡፡ ግሩም ዕድገት! ግሩም እንከን የለሽ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያዊ ሩህሩህ መንግሥት!
ይህ ዐዋጅ በዓለማችን በቅርቡ እንደሚፈነዳ በጉጉት የሚጠበቀውን የሦስኛውን ኒኩሌራዊ የዓለም ጦርነት አስቀድሞ በኢትዮጵያ በለዬለት ባርነት መልክ ያፈነዳ ፈር ቀዳጅ ዐዋጅ መሆኑን ውስጥ ዐዋቂዎች እየተናገሩ ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ደግሞ ዐዋጁ የሕወሓትን ማይማዊ ዕብሪትና ለሕዝብ ያለውን ከፍተኛ ንቀት አጉልቶ ከማሳየቱም በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሚባለው በምዕራባውያን በተለይም በአሜሪካና በአውሮፓ የሚመራው ወያኔን በሁሉም ረገድ ዕቅፍ ድግፍ አድርጎ የያዘው የበላይ ተቆጣጣሪ ለዚህ ቀበጥ ልጁ ምን ያህል እንደሚንሰፈሰፍለትና የፈለገውን ሁሉ እንዲያደርግ የፈቀደለት መሆኑንም አመላካች ነው፡፡ ወያኔዎች በዓለም ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ይህን መሰል “ዐዋጅ” ‹ባገር ሰላም‹ ማወጃቸው ሊቃወማቸው የሚችል ዓለም አቀፍ አካል እንደሌለ በማመን ነው፡፡ ለሁሉም ፍጡራን መብት እንቆረቆራለን ብለው የእንስሳት መብት አስጠባቂ ድርጅት የሚያቋቁሙት ምዕራባውያን እኛ እንዲህ በግልጽ እሥር ቤት ስንታጎር ለኛ ለ“ሰዎች” የሚሆን እርባና ያለው የተቃውሞ ድምፅ ማሰማት አለመቻላቸው የሚገርም ነው፡፡ ይህን ዓይነቱን ግልጽ አድልዖና ወደር-የለሽ ፍርደ-ገምድልነት የሚታይበትን ክስተት double standard ይሉታል እነሱ ራሳቸው፤ እጅጉን ይደንቃል፡፡
ለማንኛውም ይህ ዓለምንና እኛን ተጎጂዎቹን ብቻ ሣይሆን የመንግሥተ ሰማይንና የገሀነመ እሳትን ማኅበረሰባት ሣይቀር በሥላቅ የሚያስፈግግ ዐዋጅ የተሟላ ለማድረግ የሚከተሉትን አንቀጾች መጨመር አስፈላጊ ሆኖ በማግኘቴ ቀጣዩ ማስተካከያ እንዲጨመርበት በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ከፀሐይ በታች ከወያኔ በስተቀር አዲስ ነገር የለምና እየተዝናናችሁ እንድታነቡ ልባዊ ግብዣየ ነው፡፡ (ዋናው ዐዋጅ 31 አንቀጾች አሉት፡፡)
አንቀጽ 32.
የሕዝቡን ደኅንነትና ፀጥታ ለመጠበቅ ሲባል ማንኛውም ዜጋ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ውስጥ ስለምንም ነገር ማሰብ፣ ህልም ማለም፣ መቀባዠር፣ መቃዠትና በዕንቅፍ ልብ ማውራት የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 33.
ህገ መንግሥታችንን ከመጥፎ የመኪና አነዳድ ለመከላከል ሲባል ማንኛውም አሽከርካሪ መኪና ውስጥ ገብቶ ሲያሽከረክር ወደግራም ሆነ ወደ ቀኝ መታጠፍ፣ ወደቀኝም ሆነ ወደግራ ፍሬቻ ማሣየት፣ በኋላ ማርሽ የኋሊት መሄድ ወይም በፊት ማርሽ ወደፊት መንዳት፣ እስፖኪዮ መመልከት፣ ነዳጅ መቅዳት፣ ዘይት መለወጥ፣ መኪናን ላባጆ ማስገባት፣ ለሰው ሊፍት መስጠት፣ ቤተሰብ መጫን ወዘተ፣ ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 34.
ሀገርንና ትውልድን ከሽብር ጥቃት ለመከላከል ሲባል ይህ ዐዋጅ ተግባራዊ ሆኖ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ አራስ ሕጻናትም ጭምር ማንኛውም ለአቅመ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የደረሰ ዜጋ ፀሐይ መሞቅ፣ አየር መተንፈስ፣ ውኃ መጠጣት፣ መፀዳጃ ቤት መሄድ፣ ሰውነቱን ማከክ፣ ንፍጡን መናፈጥ፣ ምግብ ጠግቦ መብላት፣ ሰላምታ መለዋወጥ፣ የሕወሓታውያንን ህንጻና መኪና ማየት፣ ወደነሱም ማፍጠጥ፣ ከሣሎን ወደ ጓዳ ወይም ከመኝታ ቤት ወደ ሣሎን መንቀሳቀስና ከኮማድ ፖስት ኃላፊዎች ፈቃድ ሳያገኙ ከቤተዘመድም ሆነ ከጓደኛ ገንዘብ መበደር ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ እነዚህን ሲያደርግ የሚገኝ ተሃድሶ ተሰጥቶት ለስድስት ወር ከርቸሌ ይወርዳል፡፡
አንቀጽ 35.
ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታማሚን ለመጠየቅ ወይም የሞተን ለመቅበር ሲሰባሰቡ ህገ መንግሥታቸውንና በመቶ ፐርሰንት የመረጡትን ዴሞክራሲያዊ መንግሥት እንዳያሙ ሲባል በነዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ማንኛውም ዜጋ በተፈጥሮ በሽታም ሆነ በድንገተኛ አደጋ መታመምም ሆነ መሞት የተከለከለ ነው፡፡ ነገር ግን የዜጎች መሞት በግድ አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ከሕወሓቶች በስተቀር ማንኛውም ዜጋ አጋዚና የመከላከያ ሠራዊት በሚገኙባቸው አካባቢዎች በቡድንም ይሁን በግል በመቅረብ በጅምላም ሆነ በችርቻሮ የተፈለገውን ያህል የሞት መጠን መቀበል እንደሚቻል ኮማንድ ፖስቱ በደስታ ይገልጻል፡፡(የጥይት ግን ይከፈላል)
አንቀጽ 36.
አካባቢን ከሁከት ለመታደግና ህገ መንግሥቱን በኃይል ከሚንዱ አሸባሪዎች ለመከላል ሲባል በዐዋጁ ጊዜ ውስጥ ማንም ዜጋ በምንም ምክንያት ጮክ ብሎም ይሁን በለኆሳስ መሣቅም ይሁን ማልቀስ፣ “እሰይ!” በማለትም ይሁን ”ውይ!”፣ “ኡፍ” በሚልም ይሁን “ኣ!ኣ!” የውስጥ ስሜቱን በገሃድና በኅቡዕ መግለጽ የተከለከለ ነው፡፡ የቤት አከራዮችም የተከራዮችን ሣቅና ልቅሶ መጠን በመቆጣጠር ከጣራ በላይ የሚስቁትንና ስቅስቅ ብለው የሚያለቅሱትን በመለየት ለሚቀርባቸው የቀበሌ አስተዳደር ጠቁሞ እርምጃ አለማስወሰድ የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 36.
በለጋሽና አበዳሪ ሀገሮች ሕዝባዊ የእምቢተኝነት ዐመፅ ምክንያት መንግሥት ያጋጠመውን የገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ሲባል በነዚህ ስድስት ወራት ውስጥ ሚስት ከባል ወይም ባል ከሚስት ለሚያገኙት ለእያንዳንዱ ፆታዊ እርካታ ብር አንድ መቶ ለመንግሥት ገቢ ማስገባት የሚኖርባቸው ሲሆን በዚህ ግንኙነታቸው ውስጥ ግን ጽንስ መቋጠር ወይም ማስቋጠር በጥብቅ የተከለከለ ነው፤ ለእርግዝና ቁጥጥሩ ቤተሰብ መምሪያ፣ ጤና ጥበቃና መከላከያ ሚኒስቴር በትብብር እንዲሠሩ በኮማንድ ፖስቱ ታዘዋል – ለትውልድ ማምከኛም በጀት ተይዞላቸዋል፡፡ ባገራችን ያለው የመንግሥትና የሕዝብ መተማመን ክፉኛ እየቀነሰ በመምጣቱ ሳቢያ ሕዝቮችና ብሔር ብሔረ ሰቮች መንግሥትን እንዳይሸውዱ ሲባል ይህን መሰሉን የግንኙነት መጠን መቆጣጠር የሚያስችል ባልቦላ(ቆጣሪ) ከፈረንሣይና ከጣሊያን በዕርዳታ በማስመጣት በያንዳንዱ ዜጋ ጭን ውስጥ ለመግጠም መንግሥት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ኮማንድ ፖስቱ ቁጭትና እልህ በተሞላት ደስታ ይገልጻል፡፡ ይህ መመሪያ የማይመለከታቸው ከ10 ዓመት ዕድሜ በታችና ከ110 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ዜጎችን ብቻ ነው፡፡ (ስለዚህ የቀድሞውን “ፕሬዝደንት” አቶ መቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዮርጊስን አይመለከትም ማለት ነው?)
አንቀጽ 37.
ሰሜን ሸዋ አካባቢ ግዳጅ ላይ እያለ የተሰዋው ሃምሣ አለቃ ደሳለኝ የተባለ የሕወሓት ዕቃ ተሸካሚ አህያ “ስም አስጠሪ ልጅ ሳይተካ ተሰዋ!” ብሎ በዚህ ሰማዕት ላይ ማላገጥ የተከለከለ ነው፡፡ እሱን የሚያስከነዳ አንድ ዐይና ጠብደል ስናር አህያ ተክቶ አልፏልና ዘሩ ባለመቋረጡ የመለስ ራዕይ የተመሰገነ ይሁን፡፡ (አብረን ይቺን መፈክር እንበል – “የመለስ ራዕይ በአህዮቻችን ግቡን ይመታል!” – “ይመታል!”)….
አንቀጽ 38.
የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ ሲባል በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ማንም ዜጋ የፈለገውን መልበስ የተከለከለ ነው – ሞቀኝ በረደኝ ሳይባል መንግሥት በዝርዝር መመሪያዎች በቀጣይ የሚያወጣቸውን የልብስ ዓይነቶችና የአለባበስ ፋሽኖች አለመከተል የተከለከለ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ለምሣሌ ቀይ ፓንት ወይም ቢጫ ካናቴራ ወይም አረንጓዴ ኮፍያ ማድረግ መንግሥትን ስለሚያስደነብር በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 39.
ህገ መንግሥታችንን በኃይል ሊንድ ስለሚችል በዐዋጁ ጊዜ ውስጥ ዕቁብና ፅዋ ማኅበር መጠጣት፣ በዕድር ቤቶች መሰባሰብ፣ ከሦስት ወር ያለፈው የተረገዘን ጽንስ ጨምሮ ከአንድ ሰው በላይ ከቤት ውጭ መሰብሰብ ወይም ቆሞ መገኘት፣ መጠጥ ቤት መግባት፣ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ወይም በሌላ ቦታ የሆቴል ቤትን የምግብ ዝርዝር ጠቋሚ ሜኑ ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ጽፍሑ/መጽሐፍ ማንበብ … የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 40.
“በደህና እንዳዋልከኝ በደህና አሳድረኝ” ከሚል የግል ጸሎት ውጪ የዘወትር ጸሎትንና ውዳሤ ማርያምን ጨምሮ ማንም ዜጋ ምንም ዓይነት የምህላና የምልጃ ጸሎት በዚህ የዐዋጅ ጊዜ ውስጥ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡ ሀገር ሰላም ስለሆነች “ሀገረ ኢትዮጵያን ሰላም አድርግልን፤ የቀድሞ አንድነቷን መልስልን” የሚለውን የጠባቦችና የትምክህተኞች ጸሎት ማድረስና በቅዳሤም ይሁን በሌላ ጸሎት ላይ “እግዚኦ መሓረነ…” ብሎ በዜማም ይሁን በዕዝል ማመልጠን ወይ መጸለይ በጥብቅ የተከለከለ ነው – (ዋልሽ! እዚያ የሾምናቸው ልጆቻችን አሣርሽን ያበሉሻል)፡፡
አንቀጽ 41.
በኢ.ኦ.ቤ/ክርስቲያን የማሣረጊያ ጸሎቶች ውስጥ የጠቅላይ ሚንስትራችንን የአቶ መለስ ዜናዊንና የዶክተር አባ ጳውሎስን ስም ከብፁዕ አባታችን ከአቡነ ማትያስ ስም ጋር አለማንሣት በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
አንቀጽ 42.
የህዳሴያችንንና የህገ መንግሥታችንን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ማንኛውም ዜጋ ኢቢሲን ጨምሮ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሚዲያዎች መመልከት፣ ማዳመጥና ማንበብ አለበት፤ ከዚህ በተያያዘ ቢቢሲንና ቪኦኤን ጨምሮ ምንም ዓይነት የውጭ ማስሚዲያ መከታተል በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡
ጥቅምት 9 ቀን 2009ዓ.ም፣ አዲስ አበባ