የብርቱው ጋዜጠኛ ተመስገን የአመክሮ መነፈግ!
* ለተመስገን አመክሮ መታገድ ፣ መከልከል ምንም ማለት አይደለም
* አሳሪዎች ግን ያላዩት እውነት አላቸው!
ልክ የዛሬ ሁለት አመት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ” በሚጽፋቸው ጽሁፎች አመጽን ቀሰቀሰ ” ተባለና 3 ዓመት ተፈረዶበት ታሰረ ፣ ዛሬ ሁለተኛ አመቱን ገፍቶ በአመክሮ በሚፈታበት ጊዜ ላይ ብንገኝም ጉምቱው ወጣት ደፋር ብዕረኛ ተሜ ግን አልተፈታም !… ጋዜጠኛ ተመስገን በእስር ቤት የህግ ታሳሪ በህገ መንግስት የተደነገገ ህግ የተሻረበት ፣ ተደጋግሞ ጠያቂ የተከለከለ ፣ በጨለማ ቤት የታጎረ ፣ በህመም እየተሰቃዬ ህክምና የተነፈገ ፣ የተገፈፈ መብቱን ለማስመለስ በሽንፈት የማይንብከክ ልበ ሙሉ ሩቅ አሳቢ ጋዜጠኛ ላይ የሆነው የምጠብቀው ነበርና አልደነቀኝም … !
አሳሪዎች አመክሮ ሲነፍገየት … !
ጋዜጠኛ ተመስገን እንደማናቸውም ታሳሪ በአመክሮ የመፈታት መብቱን ሲነፍጉት የሰጡትን ምክንት ወንደሙ ታሪኩ ደሳለኝ አጋርቶናል ። የአመክሮ ነፋጊ አሳሪዎች ምክንያት ነው ያለው በአመክሮ መከልከያ ቢጫ ወረቀት አንዱ ” የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጽሁፎች አሁን ሀገሪቷ ላለችበት ነገር ዋናውን አስተዋፆ ይወስዳል ” ማለቱ ይጠቀሳል ! ሌላው ምክንያት አጃቢ እንጅ ውሃ የሚያነሳ ምክንያት አይደለምና ልተወው …
አሳሪዎች ግን ያላዩት እውነት አላቸው !
እርግጥ ነው የእስር ቤቱ ” ማረሚያ ቤቱ” ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ” የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጽሁፎች አሁን ሀገሪቷ ላለችበት ነገር ዋናውን አስተዋፆ ይወስዳል ” ማለታቸው እውነት አላት ፣ አሳሪዎች ያላዩት እውነት !!! እነሱ እንዳሉት ጋዜጠኛ ተመስገንን ከዛሬው ህዝባዊ እምቢተኝነት ጋር የሚገናኝ ” አስተዋጽኦ ” መንፈስ አለው ፣ ትክክል ብለዋል !
እውነቱም ጋዜጠኛው ትናንት ሆኖ ዛሬን ማየቱ ነበር … ተመስገን ስለ ኢትዮጵያውያን ፍትህ ፣ ነጻነትና የዲሞክራሲያዊ መብት መከበር ሰብኳል ፣ ስለ ጠገበው ሳይሆን ስለተገፋው ወገኑ ምሬትና የፍትህ ፍላጎትና ጥቃቄ ጽፏል ፣ የሃገሬ ወጣት ፍርሃትን እንዳይፈራ ለሚወዳት ሀገሩ ቀናኢ እንዲሆን ወትውቶ በማይነጥበው ብዕሩ ጽፏል … ግፍ ሲበዛ ፣ ህዝብ እና መንግስት ፣ የህዝብን ድምጽ በኃይል መመከት ሲጀመር ስላለው አደጋ ቀድሞ ተናግሯል ፣ ጽፏል ! … የሰማው ግን አልነበረም !
እናም ህዝብ ተማርሮ በሰላማዊ መንገድ እጆቹን እያመሳቀለ ጥያቄ ሲያቀርብ ” ጥያቄ እውነት ነው !” እያልን ሹም እየቀያየርን ለጥያቄው መልስ ኃይልን የመረጥንበት የታሪክ መባቻም ተሜ ” የፈራ ይመለስ! ” መጽሐፉን ወህኒን ሆኖ ሳይታክት አቅርቧል ፣ የተኛውን ያነቃ ትጉህ ሰላማዊ ታጋይ ኢትዮጵያዊ ወንድማችን ነው ጋዜጠኛ ነው ተመስገን !
…ጋዜጠኛ ተመስገን ህዝብ በመንግስት ላይ እምነት ሲያጣ ፣ ህዝብና መንግስት ሲለያዩ ስለሚከተለው ምዕራፍ ” በመለስ አምልኮ ” ድንቅ መጽሐፉ የነገረን እሱ ተመስገን ነው ፣ በመናገር በመጻፉ ብቻ በወንጀለኛነት ተጠርጥሮ ለመቁጠር የሚታክቱ ክሶችን እያስተናገደ አንዱ በር ሲዘጋ በሌላ በር ሾልኮ ማስተማር የሚያውቀው ብርሩ ሰው መሳሪያው ብዕር እንጅ ጠመንጃ አልነበረም !
የተሜ መንገዱ ሁሉ ፍጹም ሰላማዊ ነበር ፣ ከሁለት አመት በፊት ህገ መንግስታዊ የመጻፍ መናገር መብቱን ተጠቅሞ በማጻፍ በመናገሩ ከተደረደረበት ክስ በአንዱ ለ3 ዓመት ተፈርዶበት ወህኒ ወረደ ፣ በወህኒ ያሳለፈው መከራ ብዙ ነው ! በልጃቸው መጠወር የሚገናቸው እናት ስንቅ ይዘው መጎብኘትና ማቀበል እንዳይችሉ እስከደረሰ የጭካኔ መብት ገፈፋ ግን ተመስገንን አላንበረከከውም ! ይልቁንም አይታክቴው ብዕረኛ ከተቸነከረበት ወህኒም ሆኖ ” የፈራ ይለመስ ” ወልዶ በመከራው ውስጥ እያለፈ ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ስንል ፍርሃትን እንዳንፈራ ተምሳሌት ሆኖ በጻፈው መጽሐፍ አነቃቅቶናል ! ተሜ ብርቱዎች ብርቱ ትንታግ ብዕረኛ ነው ፣ ተሜ ያለውን አካፍሎ መብላት የሚያውቅ ፣ ሰብአዊና ሃገር ወዳድ ወንድም ነው፣ ተሜ መከራውን በጸጋ የሚገፍት ራሱንና የእናት ፍቅሩን ለሀገሩ መስዋዕት ያደረገ ወንድም ነው ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እንዲህ ነው!
ለእሱ መታገድ ፣ መከልከል ምንም ማለት አይደለም !
ዛሬ ተመስገን የአመክሮ መታገዱ ሰምቶ ይሆናል ፣ እኔ ግን የእሱን መልድ ሳልሰማ ከማውቀው ብርቱ ሰው አንደበት ይወጣ ይሆናል የምለውን ምላሹን እኔ ልንገራችሁ ፣ ለእሱ አመክሮ መታገድ ፣ መከልከል ምንም ማለት እንደማይሆን ያልገባችሁ ካላችሁ እወቁት ፣ እኛም ቤተስብ ወዳጆቹ ” በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ የሀገሪቱ ህገ መንግስት አልተከበረም !” ለማለት ያህል አመክሮ መከልከሉን አወሳነው እንጅ ተመስገን የእነሱ አመክሮ ፈላጊ ፣ እሱ አሳሪዎቹን ” ፍቱኝ ” ብሎ የሚንከላወስ ሰብዕና እንደሌለው በጽናት ላመመነበት አላማ ፈቀቅ የማይል ዘረኛነትን የሚጠየፍ የኢትዮጵያ ልጅ መሆኑን አውቃለሁና እነግጋችኋለሁ!
ዛሬ ላይ ህዝባዊ እንቢተኝነቱን አመጹ ከጫፍ እስከጫፍ ባየንበትና መንግስት አመጹና ለማረጋጋት አስቸኳይ አዋጁ ባወጀበት የታሪክ አጋጣሚ ሆነን ፣ ጥቂት የማይባል የሀገሬ ሰው ፣ አዋቂው አላዋቂ የዘር መንፈስ ተጠናውቶት የዘር ግጭትን ወደ ሚገፋ ክፉኛ የማይበጀን መንገድ ሲተም ፣ ጋዜጠኛ ተመስግን ” ኢትዮጵያዬ ” እንዳለ በወህኒ የመከራ ጊዜውን በጽናት በመገፈት ላይ ያለ ብርቱ ሀገር ወዳድ ነው ። ተመስገን የሚጽፍ የሚናገረውን እውነት ዛሬ ከወረቀት ባለፈ በህዝብ በሀገሩ ፣ በመንግስትባ በሹማምንቱ ላይ ሰፍሮ እያየነው መሆኑም ደረቅ እውነት ነው!…
ትንሳኤው እስኪደርስ …
ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት አልፋ ከትንሳኤው እስኪደረስ ባለው የስቃይና የመከራ መንገድ ባንዱ በዚህ ወቅት ለጋዜጠኛው ለተሜና ለጽኑ ቤተሰቦቹ መከራው ሳያንስ እንደ ህክምናና ጎብኝ ፣ አመክሮም መከልከሉ ምንም ማለት አይሆንም! …. ትናንትም ዛሬም በተመስገን ላይ የሆነው ከዚህ መንግስት የሚጠበቀው ነው ፣ አልደነቀኝም ተሜና ቤተሰቦቹም ይህን አታውቁም አልልም ፣ በልጅ ወንድማችሁ በጋዜጠኛ ተመስገን ላይ ግፍ ተደራርቦባችሁ ህግና ሥርዓትና ደንቡ ተከብሮላችሁ አላየሁም አልሰማሁም! ዛሬም ይህን በደል ከፈጸመባችሁ የመንግስት አስተዳደር አመክሮ መጠበቅ ሰዎቹን አለማወቅ ነው አልልም ፣ ብቻ ህግ እንዲህ መሸራረፉን ሳይሆን መዘንነሉን ማሳያ ነውና መረጃው ተገቢ ነው! ለተሜ የኢትዮጵያ አምላክ ጊዜ አለው!!!!
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ማግኘት የሚገባውን አመክሮ በማግኘት ባይፈታም እሱ ነጻና ከፍርሃት እስር በመንፈስ የተፈታ ብርቱ ብዕረኛ ነው! መታሰር ሞት አይደለም ፣ ሞትም ቢሆን ስለኢትዮጵያ የሚል ትልቅ አላማ ላለው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ” ጉዞዬ እስከ ቀራንዮ ነው ” ሲል ፣ የቀራንዮው የመስዋዕትነት ጉዞ ፍጻሜው ትንሳኤ ቢሆምም ሞት ግን የሚጠበቅ ነው!
”ሁሉን ማስደሰት አይቻልም ፣ በተለይ ለተገፉት ከተናገርኩ በቂ ነው!” ሲል በአንድ ወቅት እምነቱን ሳያወላዳ የገለጸም ጉምቱ ወጣት ብዕረኛ በጽናት ለሚያደርገው የቀራንዮ ጉዞ ትንሳኤ ሩቅ አይሆንም ፣የትንሳኤው ቀን እስኪደርስ የጋዜጠኛ ተመስገንና የቤተሰቡ አበሳ ከባድ ነው ፣ እሱና ቤተሰቦቹ እየከፈሉት ላለው የከበደ መስዋዕትነት ግን ሁሌም ታላቅ ክብር አለኝ፣ ብዙዎች እናመሰግነዋለን፣ እናመሰግናቸዋለን!
ቸር ያሰማን !
ነቢዩ ሲራክ
ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓም