/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ) ን ጨምሮ የክልሉ የቀድሞ ከፍተኛ አመራር የነበሩ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ምድብ ችሎት ለሁለተኛ ጊዜ ዛሬ ቀርበዋል። ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፍ/ቤቱን ጠይቆ የተፈቀደለት ሲሆን ለመስከረም 18/2011ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
አቶ አብዲ ኢሌን ጨምሮ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ለችሎት አቤቱታ ያሰሙ ሲሆን ቤተሰብም ሆነ ጓደኛ እንዲጠይቃቸው አለመፈቀዱን፤ ምግብና ህክምናም በአግባቡ እያገኙ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አሰምተዋል ተብሏል።
የጊዜ ቀጠሮ መዝገቡ ሁሉንም ተጠርጣሪዎች በአንድ መያዙ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው እንደየሃላፊነታቸው መጠን እንዲለያይ እንዲሁም የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ የተጠረጠሩበት ወንጀል የዋስትና መብት አያሰጥም በማለት ፍ/ቤቱ ጥያቄውን ውድቅ አድርጓል።
አቶ አብዲ መሃመድን ጨምሮ የሶማሌ ክልል ሰባት የቀድሞው ከፍተኛ ዓመራሮች ሐምሌ 21 እና 22/2010ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።