‹‹ዶክተሮች ስህተታቸዉን ይቀብራሉ፡፡ ዳኞች ስህተታቸዉን ወህኒ ቤት ይቁልፉበታል፡፡ ወይም ሞት ይፈርዱበታል፡፡ ጋዜጠኞች ግን ስህተታቸዉን በፊት ለፊት ገፅ ላይ ያወጣሉ፤ ያትማሉ፡፡›› የሚል የሰነበተ አባባል አለ፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ ምን ያህል ከባድ የኃላፊነት ቀንበር እንደታጨነበት ማሳያ ሀቅ ነዉ፡፡ የዛሬን አያድርገዉና ጋዜጠኛ ነጋሪ እንጂ ፈራጅ አይደለም፡፡ አድማጩ፣ ተመልካቹ ወይም አንባቢዉ ነዉ ዳኛዉ፡፡ ‹‹ እኛ እንነግራችኋለን፤ እናንተ ዳኙ›› ነዉ መርሆዉ፡፡
ዛሬ በስም ጋዜጠኝነት ዘገባዎቻችን የግልና አባል የሆንባቸዉ ቡድኖች ፍላጎት አቅራሪዎች ሆነዋል፡፡ ዛሬ በ‹‹ጋዜጠኛዉ›› እና በፖለቲካ ካድሬዉ እንዲሁም በ‹‹ጋዜጠኛዉ›› እና በአክቲቪስቱ መሐከል ያለዉን ድንበር መለየት ያዳግታል፡፡
ዛሬ በስም ጋዜጠኛ ትንታኔዎቻችን አንድን በጠላትነት የተፈረጀን ኢላማ መደብደብ ሆኗል፡፡ አብዛኛዉ መረጃችን ከምንጩ የምንቀዳዉ ሳይሆን አሉባልታ ያደራበት ነዉ፡፡ አየሩን Militant Journalism ሞልቶታል፡፡ ነዉጠኝነት፣ ፅንፈኝነት፣ አድሏዊነት፣ አሉባልተኝነት…የተከበረዉን ሙያ በክሎታል፡፡ ዛሬ እዉነት አስቀድሞና አሳምሮ በመጮህ ልክ እየተመዘነ የእዉነተኛ ዘገባን ሚዛን ጨርሶ አዛብቶታል፡፡ የጋዜጠኛዉን ተዓማኒነት አፈር ከመሬት ቀላቅሎታል፡፡ አመድ አልብሶታል፡፡
በሕዝብ መዋጮ በሚተዳደሩ የሚዲያ ተቋማት፣ ‹‹ የሕዝብ አንደበት ነን›› የሚሉ ግለሰዎች ማዶ ለማዶ የሚወራወሩት መርዝ ለእነርሱ ሠላም ቢሰጥም፣ በሚስኪኑ ሕዝብ ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ ግን ያለ ገደብ እየተረጨ ብክለትን፣ ብክነትን… እያስከተለ ይገኛል፡፡ የማይሽር ቁስል እየፈጠረ ነዉ፡፡
የ‹‹ አወቀናል፤ ተምረናል፤ በሰለጠነዉ ዓለም ኖረን ስልጥነናል…›› ባዮች፣ ‹‹ አንድ አለብህ፣ አንድ አለብሽ …›› የመሸታ ቤት ዓይነት ብሽሽቅ እየዘራ ያለዉን የጥላቻ አዝመራ አንድ ትዉልድ አጭዶ መጨረስ መቻሉ ያጠራጥራል፡፡
እባካችን በጊዜና ሁኔታ ግድ ባይነት በየማኅበራዊ ሚዲያዉና ‹‹ሜይን ስትሪም›› በሚባለዉም ሚዲያ ላይ ማይክ ወይም ብዕር ይዘን ያለን ሰዎች ቢያንስ፣ ቢያንስ ለኅሊናችን (ካለ)፣ ለሰብዓዊ ሞራል፣ ለሰማያዊዉ ቃልም ተገዥ ለመሆን እንፀልይ፡፡ እንደየእምነታችን፡፡
ያንን ማድረግ ካልቻልን ማይኩንም ሆነ ብዕሩን ትተን፣ ሌላ እንጀራ መብያ ብንፈልግ ምንም አይደለም፡፡ ባለን ሌላ ሙያ ወገኛችንንና ዘረሰዉን እናገልግል፡፡ የሕግ ሰዉ በፍትህ ረገድ፣ የታሪክ ሰዉ በታሪክ ዘርፍ፤ ዲያቆኑም በድቁና፣ ደላላዉም በድለላ ይሰማራ፡፡
ይህም የማይሆንልን ከሆነ ደግሞ ያለቦታችን ገብተን፣ ይሁነን ብለን ወይም በየዋህነት ከምንፈፅመዉ ወንጀል አይብስምና ማይኩን አስቀምጠን ገሃነብ እንግባ፡፡
ጨዋዎች፣ ‹‹ልቀርልህ ነዉ?›› ብትሉኝ ደስ ይለኛል፡፡ የባለጌዎች አፀፋ ስድብም ያዝናናኛል፡፡ ይኼዉ እንግዲህ፡፡