ከጋምቤላ የተገኘው መረጃ

ከጋምቤላ የተገኘው መረጃ

ከጋምቤላ የተገኘው መረጃ እንደሚመለክተው ርዕሰ መስተዳድሩ ጋትሉዋክ ቱት ክሆት ቅዳሜ ቀን ሰባት የክልል መስተዳደሩን የቢሮ ኃላፊዎችን ከሥልጣናቸው ለማስወገድ ደብዳቤ ወጪ እንዲሆን አዝዘው ነበር። እነዚህ ኃላፊዎች እንዲባረሩ የተደረጉበት በደብዳቤው ላይ ባይገለጽም ዋንኛው ምክንያት የርዕሰ መስተዳድሩን ሥልጣን የሚገዳደሩ ናቸው ተብለው እንደሆነ ከዚያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ከሰባቱ ውስጥ አራቱ የአኙዋክ ተወላጆች ሲሆኑ ሁለቱ የኑዌር አንደኛው ደግሞ የመጀንጊር ተወላጅ ናቸው። ደብዳቤው ለባለሥልጣናቱ በእጃቸው እንዲደርስ ባይደረግም መረጃው ግን እንደደረሳቸው ታውቋል።

የኑዌር ተወላጅ የሆኑት የክልሉ ርዕሰመስተዳድር “ወገኖቼ” ከሚሏቸው ኑዌሮች ለእርሳቸው የሚሰጠው ድጋፍ እየተመናመነ መሄዱን በመመልከታቸው “አልተደመርንም፤ አንደመርም” የሚሉ ኑዌሮች ለእርሳቸው ድጋፍ እንዲሰጡ ሲያስተባብሩ እንደነበር ካካባቢው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በዚህም ምክንያት ርዕሰ መስተዳደሩ የማደግፏቸው ሁሉ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ባዘዙት መሠረት ስድስት ኑዌሮች እሁድ ዕለት ተይዘው ታሥረዋል። ይህንን የተመለከቱ የአኙዋክ ወጣቶች (ዳልዲሞች) ከኑዌር የለውጥ ሐዋሪያ የሆኑት በመታሰራቸው አግባብ የለውም በማለት ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ አስፈትተዋቸዋል። ይህ በተከሰተ ዕለት ማምሻው ላይ በአጋጣሚ ወደ ኑዌር መንደር ሄዶ የነበረ የአኙዋክ ወጣት በኑዌሮች ተወግቶ ሞቷል። የእርሱን መሞት ለመበቀል የወጡ አኙዋክ ተወላጆች ሦስት ኑዌሮችን ገድለዋል።

ሰኞ ዕለት የአኙዋክ ተወላጆች ተወግቶ የሞተውን ወገናቸውን ለመቅበር ከወጡ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍም አድርገው ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ “አንደመርም” የሚሉ የኑዌር ተወላጆች የተገደሉባቸውን ወገኖች ለመበቀል የፈለጉ ሲሆን በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከአኙዋኮች ጋር ግጭት ለመፍጠር አስበው ነበር። በወቅቱ በመስተዳድሩ ብዙ ግፍ ተፈጽሞብናል የሚሉት አኙዋኮች ጎማ እያቃጠሉ ወደፊት እየገፉ ሲመጡ በቦታው የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ከመተኮሳቸው በፊት “እባካችሁ ተዉ” እያለ ሲለምናቸው እንደነበር በቦታው ተገኝተው የነበሩ የዓይን እማኝ ቃላቸውን ሰጥተዋል። ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ወደመሄድ ላይ ሲደርስ የመከላከያ ሠራዊት ተኩስ ከፍቶ አምስት አኙዋኮች ሲገደሉ 22 ደግሞ ቆስለዋል። ከቆሰሉት መካከል አንድ ሴት እንደምትገኝ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ ሰልፈኞቹ ላይ ጥይት እንዲተኮስ ትዕዛዝ የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው በማለት ዳልዲሞች አቶ ጋትሉዋክን ይወነጅላሉ። ምክንያቱም ሰላማዊ ሰልፉ ርዕሰመስተዳደሩ ቢሮ አካባቢ ስለነበር እና ከቢሮዋቸው ሲወጡ ይህንን በመመልከታቸው የመከላከያ ሠራዊት በሰልፈኛው ላይ እንዲተኩስ አዘዋል በማለት የዳልዲም ተወካዮች ይናገራሉ።

ለጋራ ንቅናቄያችን ከአካባቢው የሚደርሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ ከተማዋ ላይ እንቅስቃሴ የተገታ ቢሆንም ውጥረት ግን እንደነገሠ ነው። ነዋሪዎች ሳይመሽ ወደመኖሪያቸው የገቡ ሲሆን በአጠቃላይ በከተማዋ ውስጥ ነገ ምን ይሆናል የሚል ስጋት እንዳለ ይነገራል።

በጋምቤላ የመደመር፣ የለውጥና የተሃድሶ እንቅስቃሴ እንዳይካሄድ በሙስና ተዘፍቀዋል የሚባልላቸው የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚችሉትን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ ይነገራል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዳልዲሞች ለውጥና መደመር ወደ ጋምቤላ እንዲመጣ ተግተው እየሠሩ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ርዕሰ መስተዳድሩ ሥልጣናቸውን ላለማጣት በንግድ ከተሳሰሩባቸው ግለሰቦች ጋር በመተባበር በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኙ ይሰማል። ከበፊቱ ይልቅ የሚተማመኑባቸው ኑዌሮች፤ በለውጡ የመደመር ሃሳብ ማንገባቸውና ከአኙዋኮች ጋር በጣምራነት መሥራት መጀመራቸው ሥልጣናቸው እንዲሸረሸር እያደረገው መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። በንግድ የተሳሰሯው ደግሞ ሥልጣናቸውን እንዳይለቁ የሚያደርጉባቸው ጫና ርዕሰ መስተዳድሩን በሌላው ጽንፍ ውጥረት ውስጥ ከቷቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ አቶ ጋትሉዋክ ብሔራቸውን ኑዌርን መከለያ በማድረግ በጋምቤላ የሚደረገው ግጭት ብሔር ተኮር ቀለም እንዲይዝ ተግተው እየሠሩ ይገኛል በሚል በርካታ ክስ ይቀርብባቸዋል።

በጋምቤላ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን አኙዋኮችም ሆነ ኑዌሮች ጥሪ እያሰሙ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ በመግባት ሁኔታውን እንዲያረግብ እየጠየቁ ነው። ሥልጣናቸውን ላለማጣት ተግተው የሚሠሩት የክልሉ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ሁኔታውን ሌላ መልክ በተለይም የብሔር ግጭት እንዲመስል ከማድረጋቸውና ክልሉ በከፍተኛ አለመረጋጋት ውስጥ ገብቶ የህወሓት ማነቆ እየከረረ እንዳይመጣ መደመር በክልላቸው እንዲገባ ሁሉም የጋምቤላ ወገኖች ጥሪያቸውን ያሰማሉ።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በጋምቤላ እየተከሰተ ያለውን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል ሲሆን የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ ሁሉም ወገኖች በአንድነት እንዲሠሩና ኅብረታቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ ያቀርባሉ። ኑዌር፣ አኙዋክ፣ መጀንጊርና ሌሎችም በአንድነት ሆነው ሙስናን፣ የሰብዓዊ መብት ረገጣን፣ ግፍን በመቃወም ለክልሉ የወደፊት ዕድል ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ ያስተላልፋሉ፤ ሰከን በማለት በኅብረት እንዲሠሩ ይመክራሉ። የፌዴራል መንግሥትም ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ክልሉ ወደከፍተኛ አለመረጋጋት ከመግባቱ በፊት አስፈላጊውን በማድረግ ክልሉ በፍጥነት ወደ መደመር እንዲመጣና የጥላቻ ግድግዳ ፈርሶ የፍቅር ግንብ እንዲገነባ በቶሎ እጁን እንዲያስገባ በጋራ ንቅናቄው ስም ጥሪ ያስተላልፋሉ።

ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ክፍል

LEAVE A REPLY