የተጋመድንበት ፈትል /ከፋሲካ መለሠ ተሾመ/

የተጋመድንበት ፈትል /ከፋሲካ መለሠ ተሾመ/

መስከረም 2011 .

አባታችን ወደ አስራ ሶስት ልጆች ነበሩት፡፡ ከተለያዩ ሴቶች፡፡  ዘርቆጠራ ባልችልበትም፣ የአባቴ ሚስቶች ስብጥር  ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ከጉራጌ፣ ከትግራይ እና ከኤርትራ ነው፡፡ እድለኛ ስለኾንኩ ከአንዷበስተቀር ከኹሉም ከአባቴ ሚስቶቼ ጋር አብሬ ኖሬአለኹ፡፡ እናቴከአማርኛ ተናጋሪ ቤተሰብ ነው የመጣችው፡፡ ኾኖም በህጻንነቷወለጋ እና ኢሉባቦር አድጋለች፤ ስለዚህ ኦሮምኛ አቀላጥፋትናገራለች፡፡ በጣም ተናዳ ሰው መገሰጽ ስትፈልግ ወይም ንግግሯንበተረት ማሳለጥ ሲያሰኛት የምትጠቀመው በኦሮምኛ ነው፡፡ አኹንሳስበው ኦሮምኛ የሚናፍቃት ይመስለኛል፡፡ አማራኛ እና ኦሮምኛየሚናገር ሰው ካገኘች ኦሮምኛውን ትመርጣለች፡፡ በአኹኑ ዘመንአራዳዎች አነጋገር ኦሮምኛ ውስጧ ነው፡፡ ልጆቿን ያሳደገችንየአማራን ባህልና ስነልቦና ከኦሮሞው ጋር አጋምዳ እና ፈትላ ነው፡፡

ሌላዋ ያባቴ ሚስት ጉራግኛ ተናጋሪ የሆነችው ነጋዴዋ እትየ ዘነቡነች፡፡ ካባቴ ጋር ከተፈታችም በኋላ ቢኾን ከቤቷ አልጠፋም ነበር፡፡በኹለት ምክንያት፤ በመጀመሪያ ኹለት ወንድሞቼን እና አንዷንእህቴን የወለደችው ካባቴ ስለሆነ፣ ኹለተኛው ደሞ የምንኖረውባንድ ቀበሌ ነበርየመርካቶው መሳለሚያ እና ኳስ ሜዳ፡፡  አባቴያንን ሰፈር እስከለቀቀ ድረስ በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ የምውለውእና የማድረው እዛው እሷ ቤት ነበር፡፡ የጉራጌዎችን ባህል እናስነልቦና እስኪበቃኝ ያላበሰችኝ እትዬ ዘነቡ ናት፡፡

 ሌላዋ እናቴ ትእግስት ናት፡፡ ትውልዷ ትግራይ ስለነበረ አማርኛአትችልም ነበር፡፡ አባቴ ትግርኛ ቋንቋ ስለሚችል ችግርአልነበረበተም፡፡ ኾኖም ከኔ ጋር ስታወራ፣ እሷ በትግርኛ እኔበአማርኛ እየተነጋገርን እናወራለን፣ እንግባባለን፡፡ ገበያ ይዣትየምሄደው እኔ ነኝ፡፡ ያን ግዜ እድሜዋ ካስራ ስምንት አይበልጥም፡፡ትእግስት የትግራዋይን ባህል እና ስነልቦና አስተዋውቃኝለኤርትራዊቷ እናቴ አስረክባኝ ሄደች፡፡

ሸዋዬ ኤርትራ ተወልዳ ያደገች የዘመናዊ የሹራብ መስሪያ ባለቤትእና ባለሙያም ነበረች፡፡ ያን ግዜ የአስመራ ሹራብ ከኢትዮጽያአልፎ በጎረቤት ሀገሮችም የታወቀ ነበር፡፡ ሸዋዬ አማርኛ ብትችልምበእናት ቋንቋዋ ትግርኛ መናገር ይቀላታል፡፡ እሷ በትግርኛ እኔበአማርኛ፡፡ ዘግየት ብሎ ከአስመራ የመጣው ታናሽ ወንድሟ ሙሴእና የወንድሟ ልጆች እነ አማኑኤል ወንድሞቼም ጓደኞቼም ናቸው፣አንድ ላይ ነው የኖርነው፡፡ እናም የአዲስ አበባ ስብእናየከኤርትራውያን ስብእና ጋር ተጋምዶ አደግኹ፡፡

አንዲት የነገሌ ቦረና ሴት ካባቴ አንድ ልጅ ወልዳለች፡፡ ከርሷ ጋር አልኖርኩም፡፡ 1968 . መጨረሻ አባቴ ለስራ ነገሌ ሲሄድ ይዞኝይሄዳል፡፡ ሴትዮዋ በወቅቱ ነገሌ ቦረና ከተማ ውስጥ ከነበሩትጥቂት ምግብ ቤቶች የአንደኛው ባለቤት ነበረች፡፡  እዚያ ስንደርስወንድ ልጅ ወልዳ አራስ ቤት ነበረች፡፡ ወንድምህ ነው አለኝ አባቴ፡፡ነገሌ ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻ ቆይተን ወደ አዲስ አበባችንተመለስን፡፡  ያችን ያባቴን ወዳጅ ብቻ ሳይኾን ያንን ጨቅላወንድሜን ከዚያ ጊዜ በኋላ አይቻቸው አላውቅም፡፡ ከጊዜ ብዛትየተነሳ የሴትዮዋን ስም ረስቼዋለኹ፡፡  የኢጆሌቦረና ወንድሜበህይወት ካለ አኹን አርባ አመት አካባቢ ይሆነዋል፡፡ ስሙንምስለማላውቀው አብቹ ብዬ ልጥራው፡፡ አደራህን አብቹ! የኦሮሚፋተናጋሪ ማህበረሰብን ለመገንጠል ከሚጥሩ ቡድኖች ጋርእንዳትገጥም፡፡ ያባት ሀገር ግንድ ነው አይገነጠልም፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለኹ የነበሩኝ የጓደኞቼ የብሄርስብጥር ብዙም ትዝ አይለኝ፡፡ ኾኖም ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪቤተሰቦች ሊመጡ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፡፡  በወጣትነቴየኢሕአፓ አባል የኾንኩት ገና የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለኹ ነው፡፡ኢሕአፓ ደግሞ በዘር የሚሸነሽን ፓርቲ አልነበረም፡፡ ኢሕአፓከምስራቅ እስከ ምእራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን  የምንገኘውንየኢትዮጵያን ልጆች በአንድ ድስት ውስጥ ከታ ነበር ክሽን አድርጋየሰራችን፡፡ ኢሕአፓ ከነስሙም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊፓርቲ ስለነበር እና የሀገራችን ዋነኘው ችግር የመደብ እንጅ የብሄርአይደለም ብሎ የተነሳ ፓርቲ ስለነበር ኹላችንም በጊዜያዊ ሕዝባዊመንግስት  ገመድ ገምዶ አታገለን፡፡ በጣም ትዝ የሚሉኝ፣ በኢሕአፓውስጥ አብሬአቸው የሰራኹት፣ እኒያ ልጆችን ልጥቀስ፡፡ ሀጎስ እናቴዎድሮስ ጸጋዬ ከትግራይ እና ከኤርትራ ቤተሰቦች፤ ጌታነህ ታደሰ፣አበበ ማሞ እና አባይነሕ ኹነኛው ከአማራ፤ መሰረት ድሪባ፣ በቀለቶላ እና የትናየት ደቻሳ ከኦሮሞ ቤተሰቦች፤ መሀመድ ኢድሪስከጉራጌ፤ በኮድ ስሙ ሙላቱ እና ነጋሽ በቀለ ከደቡብ ቤተሰቦችነበሩ፡፡ እስር ቤት ውስጥ የነበረንበትማ የሚደንቅ ነው፡፡ ወደሰማንያ ከሚደርሰው ብሄር በሉት ብሄረሰብ ልጆች ጋር አብረንመታሰር ብቻ  ሳይኾን አንድ ላይ ኖርን፤ ከጎረቤቶቻችን ከሱዳን እናሶማሌዎች ጋር ሳይቀር፡፡

o ኦሮምኛ ተናጋሪ ኦነግ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢሕአፓ፣  ኦሮምኛተናጋሪ መኢሶን፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤

o ትግርኛ ተናጋሪ ሻእቢያ፣ ትግርኛ ተናጋሪ ህውሀት፣ ትግርኛተናጋሪ ኢሕአፓ፣ ትግርኛ ተናጋሪ መኢሶን፣  ትግርኛ ተናጋሪየኢሰፓ አባል፤
o አማርኛ ተናጋሪ   ኢሕአፓ፣ አማርኛ ተናጋሪ መኢሶን፣  አማርኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤  
o ጉራግኛ ተናጋሪ ኢሕአፓ፣  ጉራግኛ ተናጋሪ መኢሶን፣ ጉራግኛተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤  
o ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪ  ኢሕአፓ፣ ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪመኢሶን፣ ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፣ ወዘተ ወዘተ፤

እስር ቤት ውስጥ የኖርኩት ከላይ ከጠቀስኳቸው ከተለያየ ቋንቋተናጋሪ ቤተሰብ ከመጡ የኢትዮጵያ ዜጎች  ጋር ነው፡፡ ብንኳረፍወደን በመረጥነው የአላማ ልዩነት፤ ብንታኮስ ወደን በመረጥነውየአላማ ልዩነት ነው፤ ደሞ ያባት ነው፣ የሚጠበቅም ነበር፡፡ሳንፈልግ በተወለድንበት ብሄራችን ሳቢያ አልተኳረፍንም፣አልተቧቀስንም፣ አልተታኮስንም፡፡ አብዛኛው የዚያ ትውልድ አባላትበዋነኝነት ያቀነቅኑ የነበረው በመሬት፣ በዴሞክራሲ እና በህዝባዊመንግስት ጥያቄ ላይ ነበር፡፡ ያን ተመርኩዞ ኹሉ ወጣትመጀመሪያ የንጉሱን ስርአት፣ ቀጥሎም የወታደራዊውን ስርአትበሕዝባዊ መንግስት ለመተካት ተናነቀ፡፡

የዚያ ትውልድ ልጆች  የተሰባሰቡት  በዋነኝነት በኢሕአፓ፣አንዲያም ካለ ደሞ በመኢሶን ውስጥ ነበር፡፡ የኹለቱም ፓርቲዎችቁልፍ የስትራቴጂክ ጥያቄ ደግሞ የመሬት፣ የዲሞክራሲ እና ከፍሲልም የመደብ ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥ የብሄር ጥያቄ አንዱየሀገራችን ችግር ነው ብለው በፕሮግራማቸው ላይ አስፍረውታግለውለታል፡፡ ኾኖም ጥያቄው የሚፈታው በሀገር ደረጃበሚፈጠር የዴሞክራሲ ስርአት ነው የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ስለዚህ ትውልድ በነዚህ ኹለት ፓርቲዎች ውስጥ ኾኖ የታገለውለሕዝባዊ መንግስት ነበር፡፡ አብዛኛው የዚያ ትውልድ አባላትምበቀይሽብር ያለቀው የህዝባዊ መንግስት ምስረታን ቀዳሚበማድረግ በመታገሉ ብቻ ነበር፡፡

የቀይ ሽብር እልቂት ለጥቂቶቹ ጎጠኞች ተመቻቸው፡፡ የጎሳ ፖለቲካአራማጆች የኾኑት የዚያ ትውልድ አባላት አንድ፣ ኹለት፣ ሶስትተብለው የሚቆጠሩ ብቻ ሳይኾኑ፣ ቁጥራቸው ከአርባ እና ከሃምሳየማይዘል፣ በስም የሚታወቁ የትውልዱ ቅራሪዎች ናቸው፡፡ እኒያየትውልዱ እሪያዎች፣ የኤርትራን ማህበረሰብ እንወክላለን በማለትሰባት እና ስምንት ኾነው ቀደም ብለው ድርጅት መሰረቱ፡፡ ሌሎችሰባት እና ስምንት የሚኾኑ ወጣቶች ደሞ የትግራይን ህዝብእንወክላለን ብለው ነፍጥ አነሱ፡፡ ኦሮሞ ነን የሚሉ በተመሳሳይሰባት እና ስምንት ኾነው ነጻ ሀገር እንመስርት ብለው ትግል ጀመሩ፡፡ፋሽን ይመስል ሌሎች ሰባትስምንት የሚሆኑ የሶማሌ ወጣቶችምሶማሌን/ኦጋዴን ለመገንጠል አመጹ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሰባትስምንቶች የኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር  የብሄር ጥያቄ ነው በማለትበየአቅጣጫው በረሃ ገቡ፡፡የኛን ቋንቋ ይናገራሉየሚሏቸውንበሺ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ሰብስበውደሀ እንድትኾን ያደረገኽየአማራ ቋንቋ  ተናጋሪ ነውአሉት (የሻእቢያን፣ የህወሀትን እናየኦነግን የድርጅቶቻቸውን መመስረቻ ሰነድ ይመለከቷል)፡፡ ስንኩልእና ጎዶሎ ታሪክ እያጣቀሱ  የገበሬውን ጦር ጋቱት፤ በኢትዮጵያዊዜግነት ላይ እንዲዘምትም አደረጉት፡፡ ያሰቡት የጦር ሜዳ ድልለሁሉም ባይኾን ለኹለቱ ድርጅቶች ተሳካላቸው፤ ኤርትራምተገነጠለች፣ ህወሀትም ቀሪውን የሀገራችንን አገር ገዛ፡፡

ከዚያ በኋላ እዳው ገብስ ነው እንዲሉ፣ ኢትዮጵያ የተጋመደችበትንቋጠሮ ለመፍታት፣ 1983 ዓ፣ም በኋላ የነበረውን ትውልድ በዚያስንኩል እና ጎዶሎ ታሪክ ለሃያ ሰባት አመት ጠመቁት፡፡ነጻየወጡትም፣ ነጻ ያወጡትም፣ ነጻ ያልወጡትምአንድ ላይ ኾነውየኢትዮጵያዊነትን ፈትል በደነዘ ቢላ ገዘገዙት፡፡ ኢትዮጵያዊነትንያቆራኙ እሴቶች  የሉም ብለው ካዱ፡፡ የጎጥ ክልል አስምረው፣ የጎጥፓስፖርት አደሉ፡፡ አማራ የሚሉትን ከኦሮሞ፤ ኦሮሞ የሚሉትንከሶማሌ፤ ወላይታ የሚሉትን ከሲዳማ፤ ጉራጌ የሚሉትን ከጉራጌወዘተ ወዘተ መጤሰፋሪ ብለው አፈናቀሉ፣ አዘረፉ፣ አሰገደሉ፡፡በግልብ ትንታኔአቸውም ኢትዮጵያውያን የተጋመዱበትን ፈትልበጣጠስነው ብለው ፎከሩ፡፡ ቢሆንም፣ ቢኾንምተቻችላችኹ ኑሩእያሉ አሾፉብን፡፡

ያም ኾኖ፣ እኛ ኢትዮያውያን የተጋመድንበት የስነልቦና ቋጠሮውሉን ስላላገኙት ገዘገዙት እንጅ አልበጠሱትም፡፡ ኢትዮጵያዊነትአንደ ቀስተደመና ህብረቀለማት የተሰናሳለ አልባሳት ይመስላልባለቀለማት ጥለት፡፡ ቀዩን ሲመዙት አረንጓዴው ይጠነክራል፤አረንጓዴውን ሲስቡት ቢጫው ይበረታል፡፡ ከንቱ ድካም፡፡ ኢትዮጵያየተቋጠረችበትን ውል እንፈታለን ብለው ደክመው አደከሙን፣ቧጠው አስቧጠጡን፣ ጠልሽተው አጠለሹን፡፡ የጋራ አገር ብቻሳይኾን የጋራ ከተማ እና የጋራ ባንዲራ እንኳን እንዳይኖረን ዳከሩ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የተሳሰረ ነው ሲባል፣ ለማለት ብቻየሚነገር ይመስላል፡፡ ብዙዎቻችን ከምናስበው በላይ የኢትዮጵያዜጎች የተጋመድንበት ውሉ እጅግ ውስብስብ ከመኾኑም በላይቋጠሮው የትላይ እንደኾነ መለየት  ያስቸግራል፡፡ ለዚህም ነውኢትዮጵያን ለመበታተን የተደረገው ተከታታይ ሙከራ ሲከሽፍየምናየው፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተፈለገ ኢትዮጵያያውያንተጋምደው የተቋጠሩበትን ውል ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የዚያንየቋጠሮ  ውል ማንም አያውቀውም፡፡

አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣  ትግሬው፣ ሶማሌው፣ ወላታ፣ሲዳማው፣ አፋሩ፣  ቤንሻንጉሉ ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ የተጋመደነው፡፡ ይህ መጋመድ ግን በተለያዩ ብሄሮች መሀከል ያለውን የቋንቋእና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን ደምስሶ እንደ ኮንዶሚኒየምፎቆች አንድ ወጥ አላደረጋቸውም፡፡ ኢትዮያዊነት ልክ በሀበሻቀሚስ ላይ እንደምናየው  ባለ ቀለማት ጥበብ አንድ መደብ ላይየተጠለፈ ነው፡፡ ጥበቡን ጥበብ የሚያደርገው የሁሉም ቀለማትሰበዞች ተዋህደው ሲገኙ ብቻ ነው፤ አንዷን  ክር ከመዘዝናትጥልፉ ይበተናል፡፡ኢትዮጵያዊነትም እንዲኹአንዱን ብሄርከኢትዮጵያዊነት ስናወጣው ምስቅልቅላችን ይወጣል፡፡ የኤርትራ30 አመት ጦርነት፣ የህወሀት እና የኦነግ የማይገነጠለውንለመገንጠል እና ከኢትዮጵያ ተለይቶ መኖር የተደረገ ትግል ያስከተለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለዚህምስክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የተጋመደበትን ፈትል ለመግለጽ የራሴን ታሪክእንደምሳሌ ወስጃለኹ፡፡ ኾኖም ይኽ በቂ አይደለም፡፡ ምናልባትየኢትዮጵያን ብሄሮች እንዴት እንደተጋመዱ ባክልበት ምሉእያደርገው ይኾናል፡፡ በዚህ አጭር ጽኹፍ የኹሉንም ብሄሮች ታሪክመግለጽ አይቻልም፡፡ ልክ እንደሎተሪ እጣ ኹለት ብሄረሰቦችን ብቻአንስቼ በጣም ባጭሩ ልግለጽወላይታ እና ጉራጌ፡፡ መጀመሪያከወላይታ ልጀምር፡፡

ማጣቀሻዬ የወላይታው ተወላጅ፣ ዋና ዋጌሾ፣ -1990 .. በጻፉትየወላይታ ህዝብ ታሪክ ከሚለው መጽሀፍ ነው፡፡     እስከቅርብ ግዜድረስ በወላይታ አካባቢ በየዋሻው ውስጥ ተደብቀው የሚገኙትጥንታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት መቼእና እንዴት እንደመጡ በትክክል አይታወቅም፡፡ እንዳንድ ጸሀፊዎች በግራኝ ወረራ ወቅት ንዋየ ቅድሳቱ ወደ ተለያዩ የሀገራችንክፍሎች ሄደዋል፤ አንዱ እና ዋነኛው ወላይታ ነበር የሚሉ አሉ፡፡  ይህግምት እውነት የመኾን እድል ቢኖረውም፣ እኔ ግን ከዚያም በላይበነበረ የኢትዮጵያውያን የመጋመድ ምክንያት ነው እላለኹ፡፡ ለዚህደግሞ ማስረጃ የሚኾነን  የሚከተለው ነው፡፡

የወላይታ ህዝብ 110 ከሚደርሱ የተለያዩ ጎሳዎች በመጡ ሰዎችየተመሰረተ ብሄረሰብ ነው፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች ለረጅምክፍለዘመን አብረው ከኖሩ በኋላ ማላ እና ዶጋላ በመባል ሁለትትላልቅ የወላይታ ነገዶችን ፈጥረዋል፡፡ የጥንቱ የወላይታ ንጉስመቶሎሜ የአኹኑን ሰላሌ እና ፍቼን አልፎ ሰሜን ሸዋን ጭምርያስተዳደር ነበር፡፡ እንደውም አንደኛዋ የሞቶሎሜ ሚስት፣ ከቡልጋየማረካት (እግዚእሐርያ በመባል የምትጠራ የአቡነ ተክለኃይማኖትእናት) እንደነበረች ይታወቃል፡፡ እግዚእሐርያን ተከትለው የመጡበርካታ አማሮች በወላይታ ሰፍረው ቀርተዋል፡፡ ዳሞቴዎች ከጎጃምቡሬ የመጡ ጎጃሜዎች ናቸው፡፡ ካህናቱ ደግሞ የክህነት ስራቸውንያለማቋረጥ በመስራት ከወላይታ ህዝብ ጋር ተቀላቅለው ኖረዋል፡፡ቃልቻዎች  ከወሎ፣ ቡቡላ የሚባሉ ከቡልጋ፣ ጎንደሬዎች ከጎንደር፣ ኦሮሞዎች ከአርሲ እና ከጅማ፣ ትገሬዎች ከትግራይ፣ ሀዲያዎችከሀዲያ፣ ማረቆ ተብለው የሚጠሩት እና ከወንጂ እና ከአካባቢውወደ ወላይታ በብዛት ኼደዋል፡፡ አንዳንዶቹ የራሳቸውን እምነትንይዘው ቢኖሩም ቀሪዎቹ የወላይታን ባህልና እምነት ሙሉ በሙሉወስደዋል፡፡ ያም አለ ኹሉም  ወላይታነታቸውን ተቀብለው ነውየሚኖሩት፡፡

ታላቁ የወላይታ ንጉስ ካዎ ጦና፣ የትግሬ ዝርያ ቢኖርበትም፣ህዝቡም ኾነ የታሪክ ጸሀፊዎች የሚያውቁት በወላይታነቱ ነው፡፡ጋይም ሚካኤል የሚባለው የትግሬ ባላባት እህቱን ለወላይታውንጉስ ለሊቼ ከዳረ በኋላ እዚያው ወላይታ ውስጥ ከነሰራዊቱእስከመጨረሻው ኖሯል፡፡ የትገሬ ሰራዊት ከወለይታዎች ጋርተደባልቆ የወላይታን ጦር እስከ አስራሁለት ትውልድ ድረስመርቷል፡፡ የካዎ ጦና መሰረትም ከዚያ ይመዘዛል፡፡  ካዎ ጎቤተብለው  የሚጠሩት ዝነኛው  የወላይታ መሪ በወቅቱ የጂማ ኦሮሞንጉስ የነበሩትን ሴት ልጅ (አቤንቶ ዲጊቲ) አግብተዋል፡፡ በዚያን ጊዜየንጉሱን ልጅ ተከትለው በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ወላይታ ውስጥየመጡ ሲኾን፣  እስከመጨረሻው  ከወላይታ ህዝብ ጋርበመጋባታቸው እና በመዋለዳቸው ወላይታ ኾነው ቀርተዋል፡፡ እንግዲህ ይህን መጋመድ ነው፣ ሰሚ ካገኘን፣ ኢትዮጵያዊነትየምንለው፡፡

ሌላው ብሄር ጉራጌ ነው፡፡ የጉራጌዎች ምንጭ ደግሞከወላይታውም የበለጠ የሚገርም ነው፡፡ ስለ ጉራጌ ህዝብ ታሪካዊምንጭ የተለያዩ ጸሀፍት የተለያየ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ፖል ሔንዝእንደሚለው የጉራጌ ህዝብ በአክሱም ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያአካል የነበረ ሲኾን የአክሱማውያን ሀይል እየተዳከመ ሲመጣየጉራጌ ህዝብ ተነጥሎ በመቅረቱ ከግዜ ብዛት ቋንቋውና ባህሉእየተለየ መጣ ይለዋል፡፡ ብራውክ ሃመፕር የተባለው የታሪክ ሰውደሞ ክርሰቲያን የኾኑት የጉራጌ ማህበረሰብ አባላት የኢትዮጵያውንጉስ የአምደጽዮን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ምንጫቸውም  በዋነኝነትጉራእ ከሚባለው የኤርትራ ክፍል ሲኾን፣ በኋላም በግራኝ ወረራወቅት ከጎጃም እና ጎንደር አካባቢ በመነሳት ወደ አኹኑ የጉራጌግዛት ለተወሰነ ወታደራዊ ተልእኮ ሄደው በዚያው ሰፍረው የቀሩናቸው፡፡  የሙስሊሞቹ ጉራጌዎች ምንጭ ደግሞ ከሃረር አካባቢ እናማህበረሰብ (ሃርላ)   ተነስተው  በአኹኑ የምስራቅ ጉራጌ ክልልየኖሩ ናቸው በማለት ጽፏል፡፡  እንግዲህ የጉራጌ ህዝብ ምንጭከኤርትራ ይሁን ከጎጃም፣ ወይም ከጎንደር ወይም ደግሞ ከሀረር የዚህ ጽኹፍ የመከራከሪያ ነጥብ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ የጉራጌማህበረሰብ ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዴት አድርጎ እንደተጋመደለማሳየት ብቻ ነው፡፡

የኦሮሞ እና የአማራ ማህበረሰብ ቁርኝት ደግሞ ልክ እንደወላይታው እና ጉራጌው ፍጹም አንድ አይነት እና ተመሳሳይ ነው፡፡ጎጃሜዎች ከኦሮሞዎች ጋር፣ ጎንደሬዎች ከኤርትራ እና ከትግራይሰዎች ጋር፤ ሰሜን ሸዋዎች ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ  ከሀዲያ እና ከሌሎችብሄረሰቦች ጋር ተዋህደው እና ሊለዩ በማይቻልበት ደረጃ ተጋምደውነው ኢትዮጵያን የሰሯት፡፡ በየትኛውም ዘመን የነበረ  የኢትዮጵያንጉስ ንፁህ ብሄር የለውም፡፡  ከመቶ አመታት በፊት ኢትዮጵያንከገዙት ከንጉስ ሱስንዮስ እንኳን ብንጀምር፣ ንጉሱ የአንድ ብሄርተወላጅ አልነበሩም፡፡ ጎንደርን ማእከል አድርገው በተከታታይ ከሰባአመታት በላይ ኢትዮጵያን የመሩት  ኦሮሞች ምን ያህልከጎንደሬዎች፣ ከኤርትራውያን  ከትግራውያን እና ከጎጃሜዎች ጋርእንደተጋመዱ ማን ይኾን የሚያውቀው?  እውን አጼ ቴዎድሮስጥርት ያሉ ጎንደሬ ናቸው? ቢያንስ ስልጣን ከመያዛቸው በፊትጀምሮ ያገቧቸው ሴት የኦሮሞው የታላቁ ራስ አሊ ልጅአልነበሩምን? እኝህስ ሴት ከባለቤታቸው ከአጼ ቴዎድሮስ ጋርበመኾን የኦሮሞውን ያባታቸውን ዙፋን ነጥቀው እራሳቸውንእቴጌ አላደረጉም?

ለመኾኑ ኢትዮጵያውያን የተቋጠሩበት ውሉ ያለው የት ላይ ይኾን? የፈረደበት የአማርኛ ቋንቋ ለበርካታ አመታት የቤተመንግስት ቋንቋሆነና (በጎንደር ቤተመንግሰት የኦሮሞ እና የትግሪኛ ቋንቋ መነገሩተረስቶ)  አማራ ገዛን የሚል ድቤ ይጎስማል፡፡ የኔ ቢጤ ተላላ አማራነኝ ባይ ደግሞ ኢትዮጽያን የሰራት አማራ ብቻ ነው ለማለትይዳዳዋልሚስኪን፡፡ ሌላው ሚስኪንያልተቀላቀልኩ ንጹህኦሮሞነኝ ባይ ደግሞ፣ ሶስት አራተኛው የኢትዮጵያ ግዛት በአማራየተወረረ የኦሮሞ ግዛት ነው ይለናል፡፡ እነዚኹ ወገኖች በመላውደቡብ፣ ምስራቅ ምእራብና ሰሜን በመስፋፋት ሌላው ብሄርአግብቶ፣ ወልዶ፣ ተዋልዶ እና ሰፍሮ እንዲያም ሲል ቋንቋውንአሰተምሮ የኖረውን የኦሮሞን ህዝብ፣ የቀይ መስመር ድንበርአበጅተው ስፍራ የኦሮሞ ክልል ብቻ ነው  ይሉናል፡፡ ሌላው ተላላትግሬ ደሞ አማራው ሚኒሊክ ስልጣናችንን ነጥቆ ገዛን ይላል፡፡የሚያወሩት በሬ ወለደ ውሸት እውነት እንኳን ቢኾን ለእኛ 21ኛውክፍለዘመን ኢትዮጵያውያን የሚመጥን መረጃ  አይደለም፡ ይህችጎንበስ ጎንበስ እንዲሉየብሄር ጥጋጥግ ፍለጋ ዋነኛ መነሻዋየኢኮኖሚ የበላይነትን ለማግኘት እንደኾነበቀደም እለትየተጠናቀቀው የህወሀት 27 አመት የግዛት ታሪክ ምስክር ነው::

ለመኾኑ የአማርኛ ቋንቋ እና ባህልን ለአማራ ብቻ፣ የኦሮምኛን ቋንቋ እና ባህልን ለኦሮሞ ብቻ፣ የሲዳማን ቋንቋ እና ባህልንለሲዳማ ብቻ፣ የወላይታን ቋንቋ እና ባህልን ለወላይታ ብቻ፣የትግርኛን ቋንቋ እና ባህልን ለትግሬ ብቻ፣ የአፋርን ቋንቋ እናባህልን ለአፋር ብቻ፣ የጉራጌን ቋንቋ እና ባህልን ለጉራጌ ብቻ ወዘተማን ነው የሰጠው? አንዱ የአንዱን ብሄር ተወላጅ (በጋብቻ፣በጉዲፈቻ፣ በምርኮ፣ በሰፈራ እና በመስፋፋት) ከቀላቀለ እናቋንቋውን ካስለመደ በኋላ ስለራሱ ጎጥ ብቻ የሚሰብክ የየትኛውምየብሄር አባል የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ኹሉም  ቋንቋዎች እናባህሎች የኹሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሰማንያ ይኹኑዘጠና ቋንቋዎቻችን እና ባህሎቻችን የኹላችንም ቅርሶችናቸውቅርሶቻችንን ደሞ እንጠብቃለን እንጅ አናጠፋም፡፡

ለመኾኑ የወሎው ንጉስ ሚካኤል፣ የጎጃሙ ንጉስ ተክለይማኖት፣የሸዋው ልጅ እያሱ እና የወላታው ንጉስ ጦና የአንድ ብሄር ሰዎችናቸው? ሚኒሊክ እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴንስ ማነው ያንድ ብሄርሰዎች ናቸው የሚለው?  መንግስቱ ይለማርያምን፣ መለስን፣ኃይለማርያምን እና አብይን ማን ነው ያንድ ብሄር ሰዎችያደረጋቸው?  አዳሜ ስነ ልቦናው እና ባህሉ ተጋምዶ እና በጋብቻተዋልዶ የብሄርደሙከተበረዘ በኋላ፣የዚህ ወርቅ እና ጀግናብሄር ተወላጅ በመኾኔ እኮራለኹእያለ ሊያጃጅለን ይሞክራል፡፡ይኼንን የመቀላቀል ነገር እንደገና ወደ ራሴ በመውሰድ ምሳሌልስጥ፡፡ ነፍሱን ይማረውና የስጋ ዘመዴ ጋሽ አርጋው አንድ ቀንአበበ ቢቂላ እኮ የኛ ዘመድ ነውአለኝ፡፡

ጋሽ አርጋው አንዳንዴ ስለሚቀለድ የምሩን ነው ብዬ አላሰብኩም፡፡እናንተ የጅሩ ሰዎች ነን ትላላችኹ፣ እንዴት ኾኖ የቢቂላ ልጅ የስጋዘመዳችን ሊኾን ይችላል;›› ብዬ ጠየቅኹት፡፡

ቢቂላ እና ሚስቱ፣ አበበን ገና ከህጻንነቱ ጀምሮ በጉዲፈቻ ያሳደጉትቤተሰቦች እንጅ በስጋ አይወልዱትም፡፡ ወላጆቹ የኛ የስጋ ዘመዶችየጅሩ ሰዎች ናቸውአለኝ፡፡ ጋሽ አርጋውን አልተከራከርኩትም፡፡ ያምኾኖ በፍጹም አላመንኩትም፡፡ ይሄንን ወሬ ነው ብዬም ለማንምአልተናገርኩም፡፡ ያም ኾኖ ውሸት እንዳይኾንብኝ፣ አንድ ቀን፣የቅርብ ጓደኛዬ እና የስራ ባልደረባዬ የነበረው ኦሮሞው ዘካርያስ፣ምርጥ የሆኑት የኢትዮጵያ ሯጮች በሙሉ ኦሮሞዎች ናቸውካለኝ በኋላ፣ ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ መቁጠር ጀመረ፡፡ ይኄን ጊዜ፣ጣልቃ ገባኹናእዚህ ላይ ታቆማለኽ፣ አበበ ቢቂላ አማራ እንጅኦሮሞ አይደለምብዬ ላበሽቀው ሞክሪያለኹ፡፡  ያን ቀን ጓደኛዬዘካርያስ፣ የቢቂላን ልጅ አማራ በማድረጌ፣ ከት ብሎ የሳቀብኝንእስከአኹን አልረሳውም፡፡

ወደ ነጥቤ ስመለስ፣ ከብዙ አመት በኋላ ነው፤ ሬዲዮ ሳዳምጥየአበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ድል መታሰቢያ ፕሮግራም ሲተረክ ሰማኹ፡፡ ጋዜጠኛው፣  አበበ ቢቂላ ከሮምእንደተመለሰ አየር መንገድ ላይ የሰጠውን ቃለመጠይቅ  አሰማ፡፡ቀጥሎም በቦታው ተገኝተው የነበሩት የአበበ ወላጆች ሰጥተውትየነበረውን የድምጽ ቅጅ አስከተለ፡፡ የአበበ ወላጅ አባት ናቸውተብለው ቃለምልልስ ያደረጉት አቶ ቢቂላ ሳይኾኑ፣ የሰሜን ሸዋየአማርኛ ቋንቋ ቅላጼ ያረበበባቸው ሌላ ሰው ነበሩ፡፡ እናቱ የተባሉት ወይዘሮ ውድነሽም እንዲኹ፡፡  በጣም ገረመኝ፤ ጋሽአርጋው ያጫወተኝ እውነት መኾኑ ገባኝ፡፡ ያም አለያ፣ የአበበቢቂላን ኦሮሞነት ማንም ሊነጥቀው አይችልም፡፡ አበበ ማለትማንም ይውለደው ማን፣ ቢቂላ ያሳደገው ኦሮሞ ነው፤ ከዚያ በላይግን አበበ ቢቂላ ኢትዮጵያዊ ነው፤ አራት ነጥብ፡፡  ይህን እውነተኛታሪክ እንደምሳሌ ያነሳኹት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የተጋመደበት ውሉእና ቁርኝቱ እጅግ ውስብስብ መኾኑን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡

ያለመታደል ኾኖ የኛን ቋንቋ የማይናገር ጀግናን ጥላሸት መቀባትእንወዳለን፡፡ የሚገርመው የሌላ ብሄር ጀግና የተባለ ሰው ታሪኩሲጠና የራሳችን ኾኖ ያርፈዋል፡፡ የጋራ ጀግና እና አርበኛ ሞልቶንእና ተትረፍርፎን በጋራ እንዳንዘክረው የተደረገበት መንገድናኹኔታ እርግማን ነው ያሰኛል፡፡ በመዲናችን በአዲስ አበባሀውልት የሰራንላቸውን ሰማእቱን አቡነጴጥሮስን አማራአይደሉም፤ የጎጃሙ ንጉስ፣ ንጉስ ተክለኃይማኖት አማራ አይደሉም፣የወላታው ንጉስ ጦና ወላይታ ብቻ አይደሉም ወዘተ ወዘተ ብዬበመከራከሬ ስንቱ ጎጠኛ በዚያ 27 አመት ተቀይሞኛል!!!! ለነገሩእኔ፣ ያኔም ኾነ አኹን አልተቀየምኩም፡፡

ከምእራብ፣ ከምስራቅ፣ ከደቡብ እና ከሰሜን በመነሳት አንዱ ብሄርሌላውን፣ በንግድ፣ በጦርነት፣ በምርኮ፣ በጋብቻ፣ በጉዲፈቻ በሰፈራእና በመሳሰሉት ምክንያቶች ለብዙ ክፍለዘመን ተቀላቅለን እናተጋምደን ኢትዮጵያን ከመሰረትን በኋላ፣ የብሄርን ጥግ ለመታከክመሞከር (ያውም 21ኛው ክፍለዘመን) የጤና አይመስለኝም፡፡ለማንኛውም አኹን ብርሃን ይታየኛል፡፡ ብርሃንን ካየኽ ተከተለውእንዲል የጥንቱ ፈላስፋ፤ እኔም እንደ መላው የሃገራችን ዜጎችብርሃን እየተከተልኩ በተስፋ ተሞልቻለኹ፡፡

በቃኝ!!!!!!

LEAVE A REPLY