በሐዋሳው የኢህአዴግ ጉባዔ ዙሩ ከሯል!!! /ሀብታሙ አያሌው/

በሐዋሳው የኢህአዴግ ጉባዔ ዙሩ ከሯል!!! /ሀብታሙ አያሌው/

በሐዋሳ እየተካሄደ ባለው  የኢህአዴግ ጉባዔ ህወሓት የመጨረሻውን የሞት ሽረት ትግል እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።  ከዚህ ቀደም ህወሓት ያደረገው ሙከራ ዶክተር አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ እንዳይመረጥ በማድረግ የለውጥ ሂደቱን ከጅምሩ መቅጨት ነበር፤  ይህ ግን በብአዴን (አዴፓ) እና በኦህዴድ (ኦዴፓ) የጋራ ትግል በተለይም  በአቶ ደመቀ ወሳኝ ስልት እንደከሸፈ መገለፁ የሚታወቅ ነው።
ይህንን ተከትሎ በህወሓትና በአዴፓ (ብአዴን) በኩል የነበረው ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ደረጃው ከፍ ብሎ የአማራ ክልል ጥያቄ የኢትዬጵያን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የፌደራል ስርዓቱ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ጭምር እንደሚጠይቅ በመግለፅ የድንበር ማካለል ጉዳይ ከወልቃይት ጋር ብቻ እንደማይያያዝ አቋሙን ግልፅ ማድረጉንም የምናስታውሰው ነው። ከዚህም ባሻገር አዲስ አበባ የማንም ሳትሆን የአዲስ አበቤ ናት፤ ፌደራል መንግስት ከኢትዬጵያ ተቆርሶ በህወሓት አቋም በአባይ  ፀሐዬ አስፈፃሚነት ለሱዳን የተሰጠውን መሬት ያስመልስ፤ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ሊለወጥ ይገባል የሚሉ ከፍ ያሉ አቋሞች እስከማራመድ ደርሷል።
ይህንን ተከትሎ በህወሓት፤  በኦህዴድ ቤት ውስጥ ባሉ የለውጥ ቅልበሳ ኃይሎች እና  ጫፍ በረገጡ የዘር ፓለቲካ  አራማጆች መካከል በተፈጠረ ቅንጅት የለውጥ ሂደቱን ለመቀልበስ የጋራ ትግል መጀመሩም በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው።  ይህ ሁኔታ በሐዋሳው ጉባዔ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚኖረው በግሌ አስቀድሞ በተለያየ መንገድ ስገልፅ ቆይቻለሁ።  የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአቶ ደመቀን
“ከስልጣን ልልቀቅ” ጥያቄም ያለወቅቱ የተነሳ እና ለስልጣን ሽኩቻ በር በመክፈት የሐዋሳውን ጉባዔ ችግር ውስጥ የሚከት በማለት ስተችና አቋሜን ስገልፅ ቆይቻለሁ።
የፈራሁት ይህ ዛሬ በሐዋሳ የተፈጠረው ውጥረት እንዳይከሰትና ህወሓት ቀዳዳ እንዳያገኝ ነበር። ህወሓት አቶ ደመቀ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው እንዳይቀጥሉ በማድረግ በምትካቸው የደህዴኗ ወ/ሮ ሞፎርያት ካሚል እንድትመረጥ የሚችለውን ሴራ እና ቅስቀሳ እያደረገ ነው።
ይህንን ሴራ “ነፍጠኛው ጉልበት እየፈጠረ መሆኑ ለሁላችንም አደጋ ነው፤ መለስ የሰጣችሁን አዲስ አበባ የሁላችንም ናት ብሎ ሊቀማችሁ ነው፤ ፌደራል ስርዓቱ ይፍረስ ብለዋል…” ወ.ዘ.ተ በሚል የዘር ፖለቲካው ጠበቃነን በሚሉ  የነበቀለ ገርባ ፓለቲካ ተሸካሚ በሆኑ አንዳንድ የኦዴፓ (ኦህዴድ) አባላት እና እነ ሽፈራው ሽጉጤ ባሰማሯቸው የደህዴን ኃይሎች በስፋታ እየተሰራበት መሆኑን ተከትሎ ውጥረቱ አይሏል።
ይህ ሁኔታ ወደተግባር ከተለወጠ በኦህዴድ እና ብአዴን በኩል የተፈጠረውን መተማመን ስለሚቀለብሰው በማያሻማ ሁኔታ ህወሓትና ዘረኛው ቡድን የለውጥ ሂደቱን ቀልብሰው የሚያንሰራሩበት የአገሪቷም ሁኔታ ወደማያባራ ቀውስ የሚያመራበት ሁኔታ መፈጠሩ የማያሻማ ነው። ዶክተር አብይ  “የሐዋሳው ጉባኤ የኢትዬጵያን መፃዒ እድል ይወስናል” ሲሉ  ሲሉ የተናገሩት የሚሰራው እዚህ ላይ ይመስለኛል። ጉባዔው ምንም አይነት የርዕዬት ዓለም ውይይት በማያደርግበት ሁኔታ  “መፃዒ እድልይወስናል”  ማለት ትርጉሙ ምንድነው ለሚለው ጥያቄዬ ምላሽ የሰጠኝ የስልጣን ሽኩቻው ነው።
ቢያንስ ይህ በህወሓት እና በዘረኛው ቡድን ተልዕኮ ተሸካሚዎች ቡድን የተቀናጀው  ሴራ ከሽፎ የለውጥ ኃይሉ የገነባው መተማመን ገና ስድስት ወራት ሳይሻገር  አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ሁሉም አካላት በፅናት እና በንቃት ሊታገሉት የሚገባ ይመስለኛል።
 ቸር እመኛለሁ

LEAVE A REPLY