ዶ/ር አብይ ሊቀመንበር ሆነዋል፤ የህወሃትንም ድምፅ አግኝተዋል

ዶ/ር አብይ ሊቀመንበር ሆነዋል፤ የህወሃትንም ድምፅ አግኝተዋል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- 11ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ የሚገኘው ኢህአዴግ ዶ/ር አብይ አሕመድን በከፍተኛ ድምጽ ሊቀመንበር አድርጎ ሾሟል።

ከእያንዳንዱ አራት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች 45 ሰዎች የሚወጡበትና በድምሩ 180 አባላት ያቀፈው ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ውሳኔ መሰረት ዶ/ር አብይ አህመድ 176 ከ177 ጠቅላላ መራጭ ድምጽ ለሊቀመንበርነት ሲመረጡ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ በምክትል  ሊቀመንበርነት ፓርቲውን እንዲያገለግሉ ከ177 ጠቅላላ ድምጽ 149  በመገኘት ተመርጠዋል ለምክትል ሊቀመንበርነት የተወዳደሩት ዶ/ር ደብረፂዮን ከ177 ጠቅላላ መራጭ የ15 ሰዎችን ድምጽ  አግኝተዋል።

በዚህም መሰረት በቀጣይ ዶ/ር አብይ አህመድ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት የሚመሩ ሲሆን አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ ምክትላቸው ሆነው ያገለግላሉ።

ይህ በእንዲህ እያለ የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ኢንጂነር አወቀ ሀይለማርያም ከአዴፖ የተመረጡ ሲሆን የዚሁ የቁጥጥር ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት አቶ ጀማል ረዲ ከደህዴን ሲሆኑ በጸሐፊነት አቶ ብርሃኑ ፈይሳ ከኢዴፓ መመረጣቸው ተመልክቷል።

ምርጫው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ህወሀትን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ተወካዮች የመረጣቸው መሆኑን ያሳያል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች ዶ/ር አብይ በህውሃት ውስጥ የ’ተደመሩ’ ሰዎችን አበርክተዋል ማለት ይቻላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ከነኚህ የድርጅቱ ወሳኝ ቦታዎች ውስጥ የህውሀት አንበሳ ድርሻ ሙሉ በሙሉ የተቀማ ሲሆን አብዛኞቹ አባላት ከዶ/ር አብይ ጋር ለውጡን ለማስቀጠል መወሰናቸውንና የህወሀት ጽንፈኞች ባዷቸውን የቀሩበት ሂደት መሆኑን አብዛኞች ይስማማሉ።

በቀጣይ የሚጠበቀው የድርጅቱ ቀጣይ እቅድ በሊቀመንበሩ ይፋ የሚደረግበት ሂደት ሲሆን አገሪቱ በኢህአዴግ እንዴት እንደምትመራ አቅጣጫዎችን የሚያመላክት ፍኖተ ካርታ የድርጅቱን መጻኢ እድል ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY