ጌታቸው አሰፋ፦ እንደ ሰው የማይታይ፣ እንደ ጭራቅ የሚፈራ “ነገር” እንዲመራን አንፈቅድም!

ስዩም ተሾመ

አንድም ሰው #ጭራቅን በአካል አይቶት አያውቅም፡፡ ነገር ግን፣ ሁሉም ሰው “ጭራቅ” የሚለውን ስም ያውቀዋል፡፡ “ጭራቅ የለም” እንዳይባል መጠሪያ ስም አለው፡፡ ነገር ግን “ጭራቅ” የሚባል ነገር በእውን ታይቶ አይታወቅም፡፡ስለዚህ ጭራቅ “አለ” ቢሉ አያዩትም፣ “የለም” ቢሉ ከምናብዎ አያጠፉትም፡፡ ጭራቅን በአካል ካዩት ያውቁታል! የሚያዉቁትን ነገር በሌለበት አይፈሩትም! በተመሣሣይ ጭራቅ የሚባል ነገር በእውን እንደሌለ ካወቁ በምናብዎ የጭራቅ አስፈሪ ምስልና ሃሳብ አይኖርም! በአጠቃላይ ጭራቅን እንዲፈሩት በእውን መኖር ሆነ አለመኖሩን በተጨባጭ ማወቅ የለብዎትም፡፡ ምክንያቱም መኖሩንም ሆነ አለመኖሩን ካወቁ አይፈሩትም፡፡

የአቶ ጌታቸው አሰፋ መሰረታዊ ዓላማ ልክ እንደ ጭራቅ መሆን ነው፡፡ “ጌታቸው አሰፋ” የሚባል ሰው “የለም” እንዳይሉት በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን ነው፡፡ ሰውዬው “አለ” እንዳይሉት ደግሞ ከተባራሪ የፎቶ ምስሎች በዘለለ በአካል ታይቶ አይታወቅም፡፡ የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ በነበረበት ወቅት ልክ እንደ ጭራቅ በዜጎች ላይ አስፈሪና ዘግናኝ ተግባራት እንዲፈፀሙ አድርጏል፡፡ ልክ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ወዳጅ-ዘመድ ይኖረዋል፣ ሀዘንና ደስታውን ይጋራል እንዳይባል ደግሞ በወንድሙ ሞት ሀዘናቸውን የገለፁ ሰዎችን ያስፈራራል፡፡ በዚህ ረገድ የዓረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሃ ደስታ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣውን ፅሁፍ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፦

“ስለ ጌታቸው አሰፋ!

በዶር ደረጀ አሰፋ (የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም) ድንገተኛ ሞት የተሰማኝን ሐዘን በገለፅኩ ግዜ “የጌታቸው አሰፋ ስም ጠቅሰሃል” በሚል ምክንያት በቀድሞ የሰላዮች ሐላፊው ተላላኪዎች በስልክም በፅሑፍም ዛቻና ማስፈራርያ ደርሶብኛል። ከሐዘኑ ይውጣና ከተወሰነ ግዜ በኋላ ስለ ሰውየው የምፅፍ ይሆናል። እስከዛው ግን (1) የመንግስት ስልጣን ይዞ ማንነቱ (ፎቶው ጭምር) በሚያገለግለው (በሚገዛው) ህዝብ እንዳይታወቅ የሚጥር ባለስልጣን ሐላፊነት የጎደለው ነው። መደበቅ የጀግና ሳይሆን የፈሪ ሰው ተግባር ነው። በመደበቁ ምክንያት “ፈሪ” ሊባል ይገባል። (2) የደሕንነት ስራ በገለልተኛ አካል ሊመራ ሲገባ በፓርቲ የማእከላይ ኮሚቴ አባል መመራቱ ምን ያህል የወረደ እንደነበር ያሳያል።
እቀጥልበታለሁ። ስም መጥቀስ ብቻ ሳይሆን ተግባራቱም ይጋለጣል።
እንኳን ከስልጣን ተባራቹ ከነ ስልጣናችሁም አታስፈራርኙም።”

ይህ በጌታቸው አሰፋ ተልከው ሊያስፈራሩኝ ለሞከሩ ተላላኪዎች የተሰጠ መልስ ነው።

አቶ ጌታቸው አሰፋ ላለፉት 17 አመታት የብሔራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ ጭራቅ ከህዝብ እይታ ተሰውሮ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀም ያደረገው ሳያንስ ከባለፈው አመት ጀምሮ የፖለቲካ ስልጣን እንዲይዝ ተደርጏል፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለፀው መሠረት፣ “እንደ እኛ ሰው ነው” እንዳይባል ሰብዓዊ ባህሪ የለውም! ወይም ደግሞ “እንደ ጭራቅ ምናባዊ ፍጡር ነው” እንዳይባል የህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነው! ስለዚህ ሰው ይሁን ጭራቅ የማናውቀው ፍጡር በሀገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ የመወሰን ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

በዚህ በሰለጠነ ዘመን፣ እንደ ሰው ለህዝብ ታይቶ የማያውቅ፣ እንደ ጭራቅ አስፈሪ የሆኑ ተግባራት በዜጎች ልጅ ላይ እንዲፈፀሙ አሊያም በራሱ የፈፀመ፤ ዜጎች እንደ ሰው የማያውቁት፣ ነገር ግን እንደ ጭራቅ የሚፈሩት፣ ምንነቱና ማንነቱ የማይታወቅ “ነገር” የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነው ማለት ምንድን ነው? በየትኛውም ሀገር የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሹም በሚመራው መስሪያ ቤት ሥራና አሰራር ጉዳይ ላይ ለሚዲያ ቀርቦ ይፋዊ መግለጫና ማብራሪያ ይሰጣል፡፡

አቶ ጌታቸው አሰፋ የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሃላፊ እያለ አንድም ግዜ ይህን አላደረገም፡፡ ይህ ሳያንስ አሁን ደግሞ የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ አቶ ጌታቸው አሰፋ እንደ አንድ ፖለቲከኛ በክልል ሆነ በፌደራል ደረጃ ባሉ ጉዳዮች ላይ ይፋዊ ማብራሪያ ሆነ መግለጫ ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ለሚወክለው ህዝብ ሃሳብና አስተያየት ሰጥቶ አያውቅም፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰው ይሁን ጭራቅ በእርግጠኝነት የሚናገር ሰው የለም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ “አቶ ጌታቸው አሰፋ”፤ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ይሁን እንደ ጭራቅ ምናባዊ ፍጡር የመጠየቅና የማወቅ መብት አለው፡፡ የህወሓቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል እና የኢህአዴግ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ፣ እንዲሁም ሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮችና አባላት የአቶ ጌታቸው አሰፋን ምንነትና ማንነት የማሳወቅ የሞራልና የህግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ሰው ይሁን ጭራቅ የማናውቀው ፍጡር በሀገርና ህዝብ ጉዳይ ላይ እንዲወስን አንፈቅድም!

LEAVE A REPLY