/Ethiopia Nege news/፡- ከመንግስት ጋር ትጥቅ ለመፍታት አልተስማማንም የሚለው የአቶ ዳውድ ኢብሳ መግለጫ ትክክል እንዳልሆነ እና መንግስት የታጠቀ ሃይል ኢትዮጵያ ውስጥ አስገብቶ ሁለት መንግስት እንዲኖር የማይፈቅድና ቀይ መስመር ያለፈ ጉዳይ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ አስታወቁ።
ዛሬ የኮሚኒኬሽን መሳሪያ ቤቱ ሃላፊ አቶ ካሳሁን ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል ኦነግ 1300 የሚደርሱ ወታደሮቹ ትጥቃቸውን ለኤርትራ መንግስት አስረክበው በዛላምበሳ ግምባር በኩል መግባታቸውንና በአሁኑ ሰዓት አርዳይታ በተባለ ቦታ በመንግስት እጅ የተሃድሶ ስልጠና በመውሰድ ላይ እንዳሉ ይፋ አድርገዋል።
በማያያዝም አቶ ካሳሁን ጎፌ አሁንም በኦሮሚያ እና አካባቢው በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እንዳሉ በማስታወስ ኦነግ አሁንም አቋሙን እንደገና እንዲፈትሽ እና እንዲያጤን በመምከር አሁንም ኦነግ አባላቶቹን ትጥቅ የማያስፈታ ከሆነ መንግስት የሀገርንና የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታውን እንደሚወጣ አሳስበዋል።
የኦነግ መሪ የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ሲገቡ ትጥቃቸውን ፈተው መሆኑን ያስታወሱት የኮሚኒኬሽን መሳሪያ ቤቱ ሀላፊ አቶ ካሳሁን በኦነግ በኩል የተሰጠው የትጥቅ መፈታት አለመፈታት ጥያቄ ተስማምተው ከገቡበት የሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ጋር የሚጣረስ መሆኑን አስምረውበታል።
አቶ ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው ኦነግ ትጥቅ መፈታቱን አስመልክተው ለዋልታ ኢንፎርሜሽን በሰጡት አወዛጋቢ መግለጫ ትጥቅ ፈቺና አሰፋች የለም ሲሉ መናገራቸውን ተከትሎ በርካታ አስተያየቶች ሲስተናገዱ መሰንበታቸው የሚታወቅ ሲሆን መንግስት ዛሬ ዘግይቶ በሰጠው መግለጫ ቀይ መስመር የተላለፉ ሃይሎች ላይ ምንም አይነት ምህረት እንደማያደርግ አቋሙን ይፋ አድርጓል።

























