አርበኛ ሲበዛ አገር ምን ይሆናል?! | በጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ

አርበኛ ሲበዛ አገር ምን ይሆናል?! | በጋዜጠኛ ደረጀ ደስታ

ጀብደኛውን መንገድ ትመርጥና አልምተህ ሳይሆን አጥፍተህ፣ ሠርተህ ሳይሆን አውርተህ፣ አሳስበህ ሳይሆን አሳምጸህ፣ ገንብተህ ሳይሆን አውደመህ፣ ሰብስበህ ሳይሆን በትነህ፣ አሳምነህ ሳይሆን አስፈራርተህ ተከታይህን ታበዛና… አገርን ለይውደም ይውደም እየጠራህ፣ ወይ ከወህኒው ወይ ከበረሃው እየገባህ ያለቀው አልቆ አንተም ታልቃለህ።… ወይም ካቴናው ከጅህ ጠልቆ ወልቆ ሲወጣ ወይም ድል ቀንቶህ ከሥልጣን ስትወጣ አርበኛና ጀግና ትባላለህ። አንተም በተራህ ሌላውን አስረህ እየገረፍክ ሌላ አርበኛ ሌላ ጀግና ትፈጥራለህ። እና አርበኛ ለአርበኛ ፈረቃ ገብተህ አንድህ ለአንድህ ሰበብና ጦስ ሆነህ ባደረስከው ሳይሆን በደረሰብህ ግፍ መልሰህ ትጀግናለህ። ከዚያ በኋላማ አለቀ፣ ሰማዕትና ጀግና እንደቻይና እቃ በየሳምንቱ በሚመረትባት ኢትዮጵያ ከገበያው አደባባይ ትወጣለህ።

ዛሬ ጀግናው በዝቶ ተርመስምሶ አስተዋዩ አንሶ ያለውም አጎንብሶ፣ ቀጣፊውና ዘራፊው ነግሶ እዚህም እዚያም ብቻውን ሲያወራ ራዕይ ሲያድል፣ ሁሉን ነገር ሲንቅ ሲያናንቅ ሲያስጠነቅቅ ይታያል። ወዲህ የሰረቀውን ወዲያ ደግሞ ሰው ገርፎ ያነቀውን፣ ከትናንት ታጋይና አርበኝነት፣ ወደ ዛሬው ቀማኛና ወንበዴነት የተሸጋገረውን ታያለህ። የገዛ መስዋዕትነትና ቃሉን ቀርጥፎ የበላውን እየነቀለች፣ በምትኩ ተረኛውን፣ የዛሬ አርበኛ የነገ ሙጃውን እየተከለች እምትጓዝ አገርህን እያየህም ታዝናለህ። እስኪ ቤት ያፈራውን ለዝና ካዝናው እሚተጋውን እንደ መንግሥት ወንበዴ እንደ አርበኛ መደዴ ሆኖ እሚተውነውን ተዋናይ ሁሉ ዝምብለህ ተመልከት! ገዳይ ለመግደሉ ብቻ ሳይሆን ሟችም ለመሞቱ ኃላፊነት አለበት…እሚለው የካህሊል ጅብራን ፍልስፍና ትዝ አይልህም! ንግግሩ ሁሉ ዝም ብሎ “በለው በለው!” ብቻ የሆነውን ሰው፣ አንተም መልሰህ እሱን ራሱ “በለው በለው” እሚል ቁጣ አይመጣብህም? ወዳጄ ሆይ ያን ጊዜ ፍራ! አንተም እንደ መንግሥት አንተም እንደ ገልቱዎች ያገርህ ድርጅቶች ሆንክ ማለት ነው። ምክንያቱም መንግሥትም ተበሳጭቶ፣ አንዳንዴም መንገድ አጥቶ፣ መረን የወጣውን እየለቀመ፣ አናት አናቱን ቢለው የበለጠ አበሳጭቶ ያሳዝነሃል።

ስለዚህ ወዳጄ፣ አይዞህ መልሰህ አትቆጣ፣ ተረጋጋ፣ ግፍ ሠሪው ግፍ ጠሪውን ሲጎዳ እያየህ አትበሳጭ። ይልቁንስ አመጽ ለአመጽ እሚሽከረክርበት ቆሞ፣ አገር ከአመጽ ወደ ውይይትና ስክነት እሚሸጋገርበትን ትናፍቅ ዘንድ፣ ይህን የችግግርና የሽግግር ዘመን በርጋታና በጥበብ እለፈው። ዘመኑ በአንተ ዝምታና ገለልተኝነት ጭምር ቤት ያፈራቸው አርበኞችና አዋቂዎች ብቻ የሚውረገረጉበት ዘመን ነው። እነሱም በዝተው እየተባዙ፣ ብዕር ትቶ ዱላ አንስቶ እሚሮጠው ተማሪ ሳይቀር በዝቷል እየተባለ ነው። አገሪቱ አዋቂዎችዋን ሳይሆን አርበኞችዋን እንዴት አድርጋ በማዕረግ እንደምትቀበል ስለሚያውቅ ይሆናል። ትምህርት ምን ያደጋል? ትምህርት ቤቱስ ቢሆን!- እነሱንም ማውደምና ማፍረስ ነው። ዘንድሮም ትምህርት ከድል በኋላ እየተባለ ነው። አንዳንዱም ምጽድቅ ዘራፍ ሺገዳይ ብሎ እየፎከረ የሥልጣኔና የለውጥ አባት ነኝ ብሎ አመጣሁት ያለውን፣ የገዛ ፍሬዬ ነው ብሎ እሚመጸዳቅበትን ድል ሳይቀር መልሶ እየዋጠ፣ ሌባ ሌባውን ጎሰኛ ጎሰኛውን ናፍቆ መልሶ እያደነቀ ሰልፍ ሲወጣ ይገርምሃል። እንግዲህ እዚህም እዚያም በየጎጡ እየተነሳ እሚሄድ አመጸኛና አርበኛ እየበዛ ሲሄድ፣ የትግል መነሻውና መድረሻው ይጠፋል። ፍቅሩ ከግብ ሳይሆን ከአመጽና ትግል ብቻ ከሆነ፣ ከዚህ አርበኛ መንጋ እግዜር ይጠብቀን! ለአገሬ ጥቂት ጥበበኞች ትዕግስቱን ይስጣችሁ። እዚህም እዚያም ባለው ነውጥ አትረበሹ። ለሚያልፍ ቀን ክፉ እየተነጋገራችሁ አትገማመቱ። ይህን የቀውጥና የነውጥ ቀን በተስፋው ብልጭታ እናሳልፋለን በሉ እንጂ- እናሸንፋለን አትበሉ። ሰው ራሱን እንጂ ማንንም አያሸነፍም! እንዲህ ያለው የአገር ውስጥ ድል እኮ ያለ ጠላት አይመጣም። ጠላትህ ማነው ብትባል ማን ልትል ነው?

LEAVE A REPLY