በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለሚቴክ ሲባል የተዋቀረ የትምህርት ክፍል እያወዛገበ ነው

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ለሚቴክ ሲባል የተዋቀረ የትምህርት ክፍል እያወዛገበ ነው

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ፕሮዳክሽን ኢንጂነሪንግ በሚባል ትምህርት ክፍል ውስጥ እስከ አምስተኛ ዓመት የደረሱ ተማሪዎችን እያስተማረ የቆየው የአርባምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዛሬው ዕለት ከዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት በተሰማው ወሬ ይህንን ትምህርት ክፍል እሳቸውም ሆኑ ሌሎች የዩኒቨርስቲው የበላይ አመራሮች እንደማያውቁት ተገልጿል፡፡

በዚህም መነሻነት የትምህርት ክፍሉ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ዓመት ያሉ ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን ከተማሪዎቹ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ ስለ ትምህርት ክፍሉ የጠራ መረጃ ስጡን አለበለዚያ በማይታወቅ ዲፓርትመንት አንማርም በማለት በተለያዩ ጊዜያቶች አቤቱታቸውን ለዩኒቨርስቲው አመራሮች እያቀረቡ የቆዩ ቢሆንም የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑት አቶ አታክልቲ ትምህርት ክፍሉ ከሌሎች ትምህርት ክፍሎች የተሻለ እንደሆነና ሲመረቁም ሜቴክ እንደሚቀጥራቸው በመናገር ሲያታልሏቸው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ተማሪዎቹ በዚህ ዓመት ወደ ተለያዩ ተቋማት ለተግባር ልምምድ ወጥተን ለመስራት የተመደብን ብንሆንም የሄድንባቸው ተቋማት በሙሉ ፕሮዳክሽን ኢንጂኔሪንግ የሚባል ትምህርት ክፍል አናውቅም በማለት እንደመለሷቸው ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ይህ ዲፓርትመንት ሲከፈት ጀምሮ አሻጥር ያለበትና ላልተገባ ጥቅም ተብሎ የተከፈተ መሆኑን ዘግይተው ማወቃቸውን ተማሪዎቹ አክለው ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በዛሬው እለት ሰልፍ የወጡ የትምህርት ክፍሉን ተማሪዎችን በመሰብሰብ ያነጋገሩ ሲሆን ይህ ዲፓርትመንት በዩኒቨርስቲው ውስጥ እንዳለ እንደማያውቁ አመራሮቹ ለተማሪዎች በድጋሚ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ የሆኑትን አቶ አታክልቲን ‘ትምህርት ክፍሉን ከየትኛው አካል ፈቃድ አግኝተው እንደከፈቱት መረጃ እንዲያቀርቡና ይህ ካልሆነ ግን በህግ እንደሚጠየቁ’ ተናግረዋል። በማያያዝም ዶ/ር ዳምጠው አንደኛና ሁለተኛ ዓመት የሆኑት የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች ወደ ሌላ ትምህርት ክፍል እንደሚዘዋወሩ ገልጸው ለ4ኛ እና 5ኛ ዓመቶች ተማሪዎች ግን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረው ምላሽ እንደሚሠጡ ቃል ገብተዋል ።

LEAVE A REPLY