39 ድርጅቶች ተፈትሸው ሁሉም በማጭበርበር እንደተሳተፉ ገቢዎች አስታወቀ

39 ድርጅቶች ተፈትሸው ሁሉም በማጭበርበር እንደተሳተፉ ገቢዎች አስታወቀ

/ኢትዮጵያነገዜና/፡- ከ55 በላይ ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን እንገነባለን በሚል ከረጥ ነፃ የግንባታ ብረታ ብረት ያስገቡ ባለሀብቶች አንዱንም አልገነቡም ፤ ኢትዮጵያ በ39 የንግድ ድርጅቶች 500 ሚሊዮን ብር ከሰረች ሲል ገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ ።

የገቢዎች ሚኒስትር ወ.ሮ አዳነች አቤቤ 39 የንግድ ድርጅቶች የቀረጥ ነፃ ሕጉን ተጠቅመው ኢትዮጵያን 500 ሚሊዮን ብር እንዳከሰሯት ተናገሩ፡፡

‹‹በሁለት አነስተኛ ከተሞች ‹ከ55 በላይ ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን እንገነባለን› በሚል ከረጥ ነፃ የግንባታ ብረታ ብረት ያስገቡ ባለሀብቶች አንዱንም አልገነቡም›› ብሏል የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ፡፡

አፋር ክልል ውስጥ በምትገኝ ‹ሀባላ› ( አብአላ?) በምትባል እና ከ2000 በላይ ነዋሪ በሌላት ከተማ 55 ኢንተርናሽናል ሆቴሎችን ለመገንባት ከቀረጥ ነፃ ብረታ ብረት ያስገቡ ባለሀብቶች አንዱንም አልገነቡም፡፡ ይልቁንም ብረቱን ለሌሎች ሽጠውታል፤ ገቢም አግኝተውበታል፡፡

ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ‹ሸኖ› ከተማ ላይም ባለአራትና አምስት ኮከብ ሆቴሎችን ለመገንባት በሚል ከቀረጥ ነፃ ብረታ ብረት በማስገባት ተመሳሳይ ማጭበርበር መፈጸሙን ነው ሚኒስትሯ ያስታወቁት፡፡

‹‹የሁለቱ ከተሞችን ጨምሮ በ39 ድርጅቶች ላይ በተደረገ ፍተሻም ኢትዮጵያን 500 ሚሊዮን ብር እንድታጣ ያደረገ ማጭበርበር ተፈጽሟል›› ነው ያሉት ወ.ሮ አዳነች አቤቤ፡፡

‹‹ለግንባታ በሚል የቀረጥ ነፃ ሕጉን ለሕገ-ወጥ ዓላማ ያዋሉ ድርጅቶችና ባለሀብቶችን የመፈተሹ ሥራ ይቀጥላል፤ ከተጭበረበረው ሀብት ውስጥ ክስ በመመሥረት 250 ሚሊዮን ብሩ ለመንግሥት እንዲመለስ ተደርጓል›› ብለዋል ሚኒስትሯ፡፡

የቀረጥ ነፃ ሕጉን መሰል ማጭበርበሮችን ለመከላከል  በሚያስችል መልኩ ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

/ከስዩም ተሾመ ገፅ/

LEAVE A REPLY