እህ ዛዲያማ
በአንድ ጎጆ
እህ!
አንድ ቁርንጮ ይነጠፍና
እህ!
አዋጅ በይፋ ይታወጅና
እህ !
ሀይል ያደራጃል ደግሞ እንደገና
እህ ዛዲየማ !
እህ ዛዲያማ! ምን ትለኛለህ ?
ከየመንገዱ ሰብሰቦ ሲያስርህ
አይደለም እንዴ ገድሎ ሊጥልህ ።
ወለላዬ
እነሆ ጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ አለወትሮዋ በጸጉረ ልውጦች ከተሞላች ሰንበትበት አለች ። ሃገራችን ያለው ህዝባዊ እምቢተኝነት እንቅስቃሴ ያስፈራቸው የወያኔ ጀሌዎችና ደጋፊዎች የተነሳውን እሳት ለመሸሽ በመዘየድ ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በተራቸው መፍለስ መጀመራቸው መሆኑ ነው። ይህ ትዕይንት የወያኔ ዘመን ሊያከትም መዳረሱን ጠቋሚ ክስተት ነው። ዛሬ በመካከላችን የምንሰማው ዱካ፣ በዓይናችን የምንቃኘው ወዛም ገጽታ፣ በየሱቁ የምናስተውለው ግርግር፣ የባለስልጣን፣ የቱጃር ሚስቶችና ልጆች፣ እንዲሁም ዘመዶችና ቁባቶች መሆናቸውን አንዳች የሚያሳብቅ ነገር አለው ። እንደው በጥቅል አነጋገር በከተማው ውስጥ በሰፊው የሚታዩት እነሱ ስለመሆናቸው ብዙ ዋቢ ማቅረብ የሚያስፈልግ ከቶ አይመስለኝም ።
እነዚህ በፍራንክፈርት ከተማ ውስጥ የሚዘዋወሩትን የቱጃር ሚስቶችና ቁባቶች አተኩሮ ለተመለከተ ሰው ከቆየነው ስደተኞች በቀላሉ ይለያቸዋል። የገዥው መደብ ቅምጥሎች! ከታች እንደ አፋር ወተት በባላና ባላቸው መካካል ሲናጡ ፣ ከላይ አካላቸው የብቸና ምት እስክስታ ሲያረገርግ፣ መሬቱን ሊረግጡ ሲጠየፉት ይስተዋላሉ ። እዚህ ካሉት ሰደተኛ ሴቶች የሚለያቸው አንዱ ነገር ቢኖር ይህ አካሄዳቸው ነው ። የእኛዎቹ ሰደተኛ ሴቶች “ በሞላ ጎደለ “ አዕምሯቸው ተወጥረው፣የባቡር ሰዓት ደረሰ አልደረስ በሚል መቻኮል፣ ስፋ ሰፋ ባለ እርምጃ መንገዱን ቆረጥ ቆረጥ እያደረጉ ሲጓዙ ላየ ለካ አካሄድም ትምህርትና ቄንጥ አለው? አይ ያለው ማማሩ ፣ አረማመዱ ኩሩ ማለቱ አይቀርም።
ዘበናዮቹ ሴቶች የዛሬውን አያድርገውና ግቢያቸው በሰለጠነና በታጠቀ አሽከር፣ እልፍኛቸው በሦስትና አራት ደንገጡር፣ እግራቸው ወዲህ በሃር ስጋጃ ውዲያ በጀርመንና በጃፓን መኪናዎች ሲቀማጠሉ የኖሩ ለመሆናቸው ብዙ ባዕሪያቸው ያስረዳል።እንደው ባጋጣሚ ካገኛችኋቸው ስንት ዜጋ የሚጋፋለትንና የጀርመን ሲያጥላሉት ትታዘባላችሁ።ባቡር ላይ ተጋፍቶ፣ ለአውቶብስ ተንቀዋሎ፣ ወይ ጉድ ! ይህን ኑሮ ብላችሁ !…እንዴት ቻላችሁት? ብለው መልስው ልባችሁን ያወልቁታል። ጀርመን በሦስተኛ አለም ስትመዘን! ስትበሻቀጥ ! ይህ ብዙ የሃገራችን ሰው የሚመኘውን የጀርመን ኑሮ “ለውድ የተከበሩ” ሙሰኛ ባሎቻቸው እየደወሉ ማማረራቸው እየታማ ነው።
ለነገሩ እንዴት አያማርሩ ለዜጎቿ ገሐነም በሆነች ሃገርና አገዛዝ ውስጥ የበረሐ ገነት ኑሯቸውን ሲቀጩ ለኖሩ የሙስና ቱጃሮች አውሮፓ እንዴት ሊመጥናቸው ይችላል? ያም ሆነ ይህ ለክፉም ለደጉም መቸም መሰንበታቸው እንደማይቀር እንገምታለን። እንዲያ ከሆነ ደግሞ፣ ያውሮፓ ሕይወት ሲመራቸው ለባሎቻቸው እየደወሉ “ እነዚህን ጸረ ሰላም ሃይሎች ደምስሳችሁ መቼ ነው ወደ ሃገራችን የምንመለሰው። እኛ እዚህ ባቡር ጥበቃው ሰልችቶኛል ፣ ” ብለው ማስጨነቃቸው አይቀርም ? ለዚህ ይመስላል የጨነቃችው ባሎች ፣ የወደፊት የእነርሱም ዕጣ ፈንታ ስደት መሆኑ እየታሰባቸው፣ ትግሉን ያከሸፉ መስሏቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከማወጅ የደረሱት። መቸም የመንጥር ዘመቻ ለደርግ እንደረዳው ለኛም ይጠቅመናል ብለው ይሆናል።
ከነዚህ የሙስና ቱጃሮች ጋር ጀርመን ወለድ የሆኑ “ልማታዊ ኢንቬስተሮች “ ተመልሰው ከእኛው ጋር መጋፋት መጀመራቸውን ሌላው አዲስ ክስተት ነው። የእነዚህን “ ልማታዊ የዴያስፖራ ኢንቨስተሮች በተመለከተ ባህሪይቸውና የስብእና ልካቸው ቀደም ብሎ ብዙ ሰለተፈተሸ፣ ዛሬ በቀላሉ እነሱን እንደሌሎቹ ብረት ለበሶች ለመለየት አልተቸገርንበትም። አዲስ አበባ ውስጥ የተሰሩትን ፎቆችና ሆቴሎች ስም በመደርደር የአገሪቷን እድገት ፣ የወያኔን ዴሞክራሲያዊነት ሲሰብኩን የሰነበቱ የሚሌንየሙ ሆደ-ፈጆች፣ ዛሬ ደግሞ እንደ ልማዳቸው ተገልብጠው ተቃዋሚ ሆኖው ( “ወያኔን መክረን ፣ መክረን አልለወጥ አለን ። እነዚህ ሰዎች በፍጹም አይለወጡም”) በሚል ለሆዳቸው እንዳልሮጡ ዛሬ ተቃዋሚ ሆነው ለመታየት ደፋ ቀና ሲሉ ማየታችን የሚያስተዛዝበን እንጅ የሚያስገርመን አይደለም። ጥያቄው ግን እውነት ከልባቸው ነው ? የሚለው ይሆናል። ለነገሩ የ97 ምርጫ ጊዜም እንዲሁ አጨናንቀውን ስለነበር እናውቃቸዋለን።
ዓይን አውጥተው የተቃዋሚነት መድረክ ላይ ካፈጠጡት ሌላ ብዙዎቹ የኛዎቹ “ልማታዊ ኢንቬስተሮች” ደፍረው ከተማ ውስጥ ሲዘዋወሩ አይታዩም ። ነገሩማ ልክ ናቸው ። በየቦንዱ ሽያጭ ስብሰባ ላይ ሲፎክሩ የነበሩ አሁን ተመልስው የሕዝብን ዓይን ማየት እንዴት ይቻሉት። ለነገሩ በሃፍረት ቆፈን ተጨምድደው ከቤት እንደማይወጡ ብዙዎቻችን ታዝበናል ። እዩኝ እዩን እንዳላሉ ደብቁኝ ደብቁኝ ማለትን ይዘዋል ። እነርሱ ይደግፉት፣ ይጨፍሩለት የነበረው ወያኔ በሕዝብ ተጠልቶ ሕዝብ ወግድልኝ ማለቱን ተገንዝበው ቤታቸው ሃዘን ተቀምጠው አንዴ ኢሳትን ፣ አንዴ የአሜሪካንን ሌላ ጊዜ የጀርመንን ሬዲዮ ፣ በማክተሚያው ፋናን ዓይጋ ፎረም ድረ ገጽን ጎብኝተው የዜና ጎረድ ጎረድ እየተመገቡ፣ (እውነተኛው ጎረድ ጎረድ ሸገር ቀርቷል) ወያኔን እንዲከርምላቸው የከበረ ጾሎትና ምህላ ላይ ናቸው። ለሚወዱትና ለሚያፈቅሩት መንግስታቸው ይህም ሲያንስ ነው። ስለ ሕዝብ ስቃይማ እነርሱን አይመለከታቸውም።
ብልጣ ብልጦቹ “ ልማታዊ ኢንቬስተሮች “ ደግሞ የተቃዋሚውን መፈክር ነጥቀው በየሰልፉ ላይ ከፍ አድርጎ በመያዝ፣ የድሃውን ጩኸት ቀምተው ሲጮሁ ይታያሉ። የሚቀጥለው መንግስት ንብረታቸውን እንዳይወስድባቸው የተሳትፎ መረጃ የሚሆን ፎቶግራፍ ከወዲሁ በመሰብስብ ሳያዋጣ እንደማይቀር ሳይማሩ አልቀረም። በእውነት ከልብ ንስሀ ገብተው ተቀይረው ከሆነ በጣም ጥሩ ነው ። እንደውም አብዮት ጥፋታቸውን አውቀው ቀድመው ለሚመለሱ ልቧ ሩህሩህ ነው ። ችግሩ ገብቷቸው አስቀድመው በዘመኑ ቋንቋ ነቄ ብለው ከተመለሱ ፣ ራሳቸውን እንዳጋለጡ ተቆጥሮ ይቅር መባላቸው አይቀርም ። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሁ ይቅር ማለት አያልቅበት። ግን ሕሊና ወቃሽ ነውና ሃገራቸው ላይ የሰሩት ግፍ ከሕሊና ወቀሳ ከቶ አያድናቸውም። ዛሬ በየቦታው በአንድ ጽምጽ የተነሳው ሕዝብ ትላንት ከየደሃው እየተነጠቀ (ግራውንድ ፓላስ ቱ ቪላ) ለመስራት የተሰጣቸው መሬት ላይ በግፍ የተፈናቀለ መሆኑን ሊረዱት ይገባል።
እነዚህ ሆዳሞች ዛሬም ቢሆን አደገኛም ናቸው። የተቃዋሚውን ክፍል በተገኘው አጋጣሚ ለመከፈፈል ሲጥሩ ይገኛሉ። አንድ እኔን የገጠመኝ ጉዳይ አለ። በፍራንክፈርት ከተማ የተገነዘብኩትና በብዙ ቦታ የሚታይ ነው ። ምንአልባት እናንተም ደርሶባችሁ ይሆናል። እዚሁ ፍራንክፈርት አካባቢ የጎንደር ልጆች ተሰብስበው ትንሽ ዝግጅት አዘጋጅተው ነበር ። ይህንን ዝግጅት በሚመለከት ብዙዎቻችን ስላልሰማን አልተገኘንም ። ብዙም ገቢ የተገኘበት አይመስለኝም ። ለነገሩ እነዚህ የጎንደር ልጆች ብዙዎቻንን ወያኔ ከገባ ጀምሮ በደንብ እናውቃቸዋል። ቆራጥነታቸውን፣ ሃቀኝነታቸው እንመሰክራለን ። በአጋጣሚ እዚህ ፍራንክፈርት በተዘጋጀ የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ አንድ ልማታዊ ኢንቬስተር እንደሆነ የሚታማ አሁን “ተለወጥኩ” የሚል ለሃገር ያስበ ፣ ለሐቅ የቆመ በመምሰል “ባለፈው ለጎንደር ሕዝብ ገንዘብ ተሰብስቦ ነበር ። ለመሆኑ የተሰበሰበው ገንዘብ የት ደረሰ?” እያለ ይጠይቃል ። የሆነ ምስጢር የሚውቅ በማስመሰል ዓይኑን ካንዳችን ወደ አንዳችን እያንከባለለ እኛን ይመለከተናል። ብዙዎቻንን ነገሩ ስለገባን ዝም አልን ።(ለነገሩ የተቃውሞ ሰልፉ ላይ መገኘቱም ግራ ገንብቶን ቀደም ብለን ትንሽ አምተን ነበር ) አንድ የዋህ የሆነች እህታችን በዚህ በተጠቀሰው ስብሰባ ላይ ተገኝታ ኖሮ (ምንአልባትም እሱን በዝግጅቱ ላይ አላየችው ይሆናል) አንድ ቁልፍ ጥያቄ ጠየቀችው ። ለመሆኑ አንተ ዝግጅቱ ላይ ሄደሃል ? አይ አልሰማሁምና አልሄድኩም አላት ። ደግማም ታዲያ አንተ ያላዋጠኸውን ገንዘብ እንዴት ትጠይቃለህ ? ስትለው ሁላችንም ሳቅን። ሳቃችን አንድ ላይ ስለነበረ ማንነቱን ማማታችንን ተረዳው ። ዓላማው ሁላችንም ወያኔን መቃወማችንን ትተን የጎንደር ልጆች ጋር ጦርነት እንድንገጥም ነበር ማለት ነው ። እንደዚህ ዓይነት ነገር ወያኔ በሚያሰማራቸው ሆዳሞች በሰፊው መሞከሩ የማይቀር ነው ። በተለይ የድርጅቶችን ልዩነት በማራገብ፣ የዘር ጉዳይን በማክረር ፣ የትውልድ ልዩነትን በማጉላት ፣ ቀድሞ የተሰሩ ስህተቶችንን በማጎን ክፍፍሉን ሊፈጥሩ ይሞክራሉ።
ለማንኛውም እኛ ኢትዮጵያውያን እንግዳ ተቀባይ ነንና ክብርትና ክቡራን “እንግዶቻችን እንኳን ደህና መጣችሁ” ። የማይለመድ ነገር የለምና ቻል አርጉት። ቀስ ብላችሁ ሁሉን ትለምዱታላችሁ። እናንተም አታብዙት፣ እንደኛ ስደትን ከባዶ አትጀምሩም ። እድሜ ለባሎቻችሁ! እነሱ ሃገራችንን ይግዙ እንጂ የውጭ ሃገር ዜጎች ናቸው ። እናንተም ልጆቻችሁን አሜሪካ ስለወለዳችሁ ብዙም ችግርና እንቅፋት አየገጥማችሁም ። ስለ ገንዘብ መቸም አናነሳም እማይጭርሱትን ወግ መጀምር ወግ ማቆርፈድ ይሆንብናል ። የአውሮፓንና፣ የዐረቦችን ባንክ ያስጨነቀው የእናንተ ገንዘብ መሆኑን ካወቅን ይበቃናል ። ገንዘብ ከሌላችሁም ብዙ እንዳታስቡ እደተለመደው ባሎቻችሁ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የሠሩትን ግፍ በመጽሐፍ አሳትመው መሸጣቸው አይቀርም ። እኛም እኛ ነን። በራሳችን ላይ የተደረገን የግፍና መከራን ታሪክ ከበዳዮቻችን የደም ብዕር አንደበት ስንሰማ መቅፈፉ ቀርቶ የሚያስደምመን፣ መጠየፉ ቀርቶ የምንገዛ ተረባርበን፣ ሞታችንን፣ ደማችንንና ሰቆቃችንን መልሰን ለእናንተው ሲሳይ የምናውል የሃያ አንደኛው ማሞ ቂሉዎች እስካለን ድረስ ስጋት አይግባችሁ። እኛ እኛ ነን ። ከአዲስ ግለሰብ፣ ከአዲስ ድርጅት ብዙ የምንጠብቅ፣ ከእኛው ጋር የቆዩትን የምናሽጓጥጥ፣ ብዙዎቻንን ከወያኔ የመጡ ሁሉ አዋቂ፣ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የነገ ድል ቀዳጅ መስለው የሚታዩን፣ ለአዲሶቹ የምንሰጠውን ክብር ከኛው ጋር ለቆዩ የፖለቲካ መሪዎች ወይም ድርጅቶች የማንሰጥ፣ ይባስ ብለን ከኛው ጋር የሰነበቱትን ለማዋረድ የምንጥር !። ይህ ሊታረም ያልቻለ ቂልነታችን ነው ። ስም አልጠቅስም እንጂ በዚህ ሃያ አምስት አመት ብዙ ተዛዝበናል።
ለምሳሌ ሰሞኑን ከወያኔ “ ከዳሁ” የሚለው ሰላይ አያሌው መንገሻ የሚባለው መጽሐፍ ቢጽፍ ስንቶችንን ነን ለመግዛት የምንሮጠው፣ በየቦታው እሱን ለመጋበዝ የምንጥረው ? ይህንን ሰው የፖለቲካ መሪ ለማድረግ የምንቸኩለው? ጎበዝ እራሳችንን እንታዘብ ! እምንሰራውን እንወቅ ። ተስፋዬ ገብረ እባብን እላይ ስንሰቅለው ያደረሰብንን እናውቀዋለን ። ምክር እንስማ፣ እንደማመጥ፣ ውል አንሳት ። መረጃ አይናቅም ፤ አይደነቅም ይባላል። የሚሰጠንን መረጃ መቀበል ጥሩ ነው ። ሐቀኝነቱንም ማረጋገጥ በዛው ልክ ያሻ ይሆናል። የተሰጠን መረጃ እኛን እንደገና የሚከፋፍለን ሊሆንም ይችላል። ወይንም ራሱን ከወንጀል ለማንጻት ሌሎችን ሊወነጅል የታቀደ ሊሆን ይችላል። ግፋ ቢል የስደተኛ ጥያቄው እስከሚያልቅ ከእኛው ጋር ሊሰነብት ይችላል። ይህ ሁሉ ሳይረጋገጥ ከወያኔ በመምጣቱ ብቻ ከሰማየ ሰማያት ልንሰቅለው ስንፈልግ ነው ችግሩ የሚመጣው ። የሚወነጅላቸውስ ሰዎች ራሳቸውን ሳይከላከሉ እሱ በሰጠው መረጃ መፈረጅ ከተሳሳተ ድምዳሜ እንዳያደርሰን ማረጋገጥ ይኖርብናል።
ዘመን አልፎ ወያኔ ሊወድቅ ትንሽ ጊዜ እንደቀረው ብዙ ምልክቶች ይታያሉ። ወያኔ ከሞተ ሰንብቷል። ጥሩ እድር ጠፍቶ ነው እንጂ መቀበሪያው ጊዜ አልፏል ። የወያኔ ቡድንን አሁን ብዙ የሚክዱት ይግተለተላሉ። በንጹህም ፣ በተንኮልም ሕዝባዊ ትግሉን መቀላቀል ሊፈልጉ ይችላሉ ነገሩ ጥሩ ነው ። ግን እነርሱን ወደ አመራር ፣ የፖለቲካ ተንታኝ እያደረጉ ሁሉንም ምስጢር እንዲውቁ ማድረግ ፣ ከሚገባው በላይ መድረክ መስጠት ፣ መጽሐፎቻቸውን እያተሙ ቱጃር ማድረግ በሃገር ላይ የሚሰራ ሌላው ስውር ደባ ይመስለኛል ። መቼም ለኛ ለዘመኑ ማሞ ቂሎዎቹ አንድ ነገር መጨመር ይቻላል። ወያኔን እያካዱ ወደውም ሆነ ተገደው ሃገር ለቀው የሚመጡት ወያኔን ያዳክማልና የሚደገፍ ሊሆን ይቻላል ። ሆኖም ግን ሕዝብን ሲያስጨፈጭፍ የነበረ ሁሉ ዛሬ አቋሜን ቀይሮ ከሕዝብ ጎን ቆምኩ ስላለ ብቻ ማመንና መሪ ባጣው ትግል ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ማድረግ ትልቅ ስህተት ነው ። በተለይ በአሁኑ ወቅት ወያኔ ትግሉን ከውስጥ ለመከፋፈል በተነሳበት ወቅት ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል።
እነዚህ ወያኔን ከዳን የሚሉ የተናገሩት እውነትነቱ እስኪጣራ ድረስ በዓይነ ቁራኛ፣ በጥርጣሬ ልንመለከታቸው ይገባል። መምጣታቸው ከሚጠቅመው ጉዳቱ ሊበልጥ ይችላል ። በተቃዋሚ ድርጅቶች የፖለቲካ አለመስማማት ውስጥ ገብተው ከመፈትፈታቸው በፊት የሰጡትን መረጃ ሰጥተው ጊዜና ወቅትን እንዲጠብቁ እንጂ መሪ እንዲሆኑ መጣር ከልማቱ ጥፋቱ ይበልጣል ። በሕዝብና በሃገር ላይ ከፍተኛ ደባና ወንጀል የሠሩ ባለስልጣናት ተደላድለው በነጻነት ሲኖሩም እየተመለከትን ነው ። እነሱ በሠሩት ጥፋት ግን እነሆ ህዝብ እያለቀ፣ ተተኪ ትውልድ ዛሬም እየመከን፣ ሃገርም እየፈረሰች ነው ። እነሱም ሲያሻቸው አማካሪ፣ ሲያሻቸው የፖለቲካ ተንታኝ እንዲያም ሲል የፖልቲካ ድርጅቶች መሪዎች ናቸው ። በዚህ ዓይነት እየተመራን ትግሉን ከዳር ለማድረስ የተጓዝንበትን መንገድ መቁጠርና እድገታችንን መመዘን ፣ ከዚያም ለምን ብሎ መጠየቅ ብልህነት ነው።
ወያኔ ዛሬ እነልደቱን ሳይቀር ከተኙበት ቀስቅሶ ስደቡኝ ብሎ ልኳል ። በየተቃዋሚው ብዙ ወኪሎቹን ይልካል ። የይስሙላ ተቃዋሚም ያዘጋጃል ። ይህንን ተንኮል ተረድተን ከወያኔ የሚመጡትን ሙሉ ልብ ፣ ሙሉ ጆሮ መስጠት አይስፋልግም ። ከዛ በላይማ የማይታሰብ መሆን አለበት። ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ።
ስለ ሃገራችን በጎ የሚያስብ በሰላም ይክረም!