አርበኞች ግንቦት 7 በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመታገል ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ነው!
ባለፉት አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገራችን አፈና እንዲያበቃ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍሏል። ውሎ አድሮ በኢህአዴግም ውስጥ ከዚህ መስዋእትነት ከፋይ ህዝብ ጋር የወገኑ የለውጥ ሃይሎች ተነስተዋል። የእነዚህ ሁለት ኩነቶች ድምር የሃገራችንንን ፖለቲካ ከነበረበት አስፈሪ ሁኔታ ወደ ተሰፋ ሰጭ ሁኔታ መርቶታል። ይህን ያጤነው ድርጅታችን አርበኞች ግንቦት 7 አመጽን ጨምሮ ሲያደርግ የነበረውን የነጻነትና የመብት ማስክበር ትግል ያለምንም ማቅማማት ወደ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ቀይሮታል።
አርበኞች ግንቦት 7 ይህን ውሳኔ ሲወስን በሃገራችን ውስጥ ሁሉ ነገር ተስተካክሏል የወደፊቱ ትግል አልጋ ባልጋ ይሆናል ከሚል እሳቤ አልነበረም። ገብተንበት የነበረውን አመጽን ያካተተ ትግል ቀድሞውኑ ተገፍተን እንጂ ወደን የገባንበት አለመሆኑና በተለይ ከገባንበት በኋላ ይህ አመጽን ያካተተ የትግል ስልት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሊያስከትል የሚችለው መዘዝ ክፉኛ ያሳስበ ስለነበር ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 ለነጻነትና ለፍትህ መከበር የአመጽ ትግልን ያካተተ ትግል የጀመረው ለተመሳሳይ ዓላማ ተመሳሳይ ትግል በበርካታ የአረብ ሃገራት መደረግ ከመጀመሩ በፊት እንደነበር ያስታውሷል። በነጻነት ስም የተጀመረ የአመጽ ትግል ሶሪያን፣ የመንን ሊቢያንና ሌሎችንም የአረብ ሃገራት የጨመረበትን ሲኦል የመሰለ ሁኔታ ለተመለከተ የኛም ተመሳሳይ ትግል በተለይ በኢትዮጵያ የተወሳበበ ሁኔታ ምን ሊያስከትል ይችል ይሆን ብሎ መጨነቁ አይቀርም። አመጽ፣ አንድ እምነት አንድ ቋንቋ የሚናገሩ የአረብ ሃገራት ህዝቦችን ወደ ሲኦል ከወሰደ እንደኛ የቋንቋ፣ የባህልና የእምነት አይነት በበዛባት ሃገር የት ሊወስደን እንደሚችል ለመተንበይ ጠንቋይ መቀለብ የሚያስፈልግ አይሆንም።
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ለሰላማዊና ህጋዊ ትግል የተሻለ እድል ከፍቷልና የአመጽ ትግል እናቁም የሚለው ውሳኔ የመነጨው ሃገርንና ወገንና ከሚያሰቀድም ጭንቀት እንጂ ከድርጅቱና ከአባላቱ ጠባብ ጥቅምና ፍላጎት አይደለም። በዚህ ጽኑ እምነትና ምክንያት ላይ በመመስረት ንቅናቂያችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም አድርጎ ሃገሪቱን የሚመራው የለውጥ ሃይል ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመንቀሳቀስ በቅቷል።
ንቅናቄያችን በመሳሪያ ሃይል ይንቀሳቅሱ የነበሩ አባላቱን ከመንግስት ጋር ባደረገው ስምምነት ወደ ካምፕ ያስገባ ሲሆን፣ እስከአሁን ካምፕ ያልገቡትንም መንግስት ወደ ካምፕ እንዲያስገባ በጋራ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ንቅናቄያችን በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ታጣቂዎቹ በምንም አይነት የአመጽ እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ መመሪያ ከሰጠበት እለት አንስቶ እሰከ አለንበት ወቅት ምንም አይነት ችግር ያልተፈጠረ ሲሆን አባላቶቻችን ለሰላም መስፈንና ለህግ የበላይነት መከበር ካላቸው ቀናዒነት የተነሳ ወደፊትም ምንም አይነት ችግር እንደማይፈጠር እርግጠኞች ነን።
አመጽ ከሃገራችን ፖለቲካ ተወግዶ ፖለቲካ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ የሚደርግበት ሁኔታ ሲናፍቅ የኖረው ንቅናቄያችን ዛሬ በሃገራችን የተፈጠረውን ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ለማድረግ የተመቻቸ ሁኔታ እንዳይበላሽ ወይም እንዳይቀለበስ በመንግስት ውስጥ ካሉት የለውጥ ሃይሎች፣ ለሰላምና ለህግ መከበር ከቆሙ ከተለያዩ ተፎካካሪ ድርጅቶች ጋር በጋራና በጽናት እንድሚቆም ያሳውቃል።
ሁሉም ለሰላም ዘብ ይቁም !
አርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ