የባሕር ማዶ ደብዳቤ ቁጥር ፬ | አቢቹ ነጋ

የባሕር ማዶ ደብዳቤ ቁጥር ፬ | አቢቹ ነጋ

ጉዳዩ፥ ከዳያስጶራው የተጠየቀው ትንሽ ነውና ጠ/ሚ ዓብይን እንተባበራቸው። ውድ ዳያስጶራ ወገኖቸ፥

በቅድሚያ እንኳን ለፈረንጆች ገና እና አዲስ ዓመት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ። አዲሱ ዓመት ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይን ከልብ የምንተባበርበት፤ ሃገርና ሕዝብን የምንታደግበት ዘመን ያድርግልን። በተለያየ ምክንያት ሃገርህንና ወገንህን ትተህ በባህር ማዶ ሕይወትህን ስትገፋ የኖርኸው ወገኔ ሆይ በሰው ሃገር ስትኖር ብዙ ውጣ ውረድ ደርሶብሃል። የሰው ፊት ገርፎሃል። ማንኛውንም ዓይነት ስራ ሰርተሃል። እራስህንና ልጆችህን አስተምረሃል። በረዶ፤ ብርድና ቁር ተፈራርቀው ውብ ገፁታህን አኮራምተውታል። በሙቀት ተገርፈህ ኑሮህን ለማደላደል ጥረሃል። በዚህ የምስቅልቅል ኑሮ ውስጥ ሆነህ በሃገር ቤት ያለውን ዘመድህን እረድተሃል። ቤትና ሕንፃ አየሰራህ ለወገኖችህ መጠለያና አልባሳት አቅርበሃል።

የሃገርና የወገን ናፍቆት እያስጨንቀህ ቢሆንም እጅግ ከተጨናነቀው ኑሮህ እየቀነስህ የውጪ ምንዛሬ እየላክህ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ደጉመሃል። በሁለገብ ልፋትህና ድካምህ ኑሮን አሸንፈህ ከሌላው ሃገር ዲኣስፖራ በተሻለ ደረጃ እራስህን አቋቁመህ አንቱ ተብለሃል። በህግ አክባሪነትህ የራስህን፤ የሕዝብህንና የሃገርህን መልካም ስነምግባር አሳይተሃል። ለዚህ የእንጀራ አገርህና ሌላው ዜጋ ከፍተኛ ከበሬታን ለግሰውሃል።

ውድ ዲያስጶራ ሆይ፤ በልፋትህ ዘመን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጉያህ ይዘህ ኑረሃል። ደስታዋን ደስታህ፤ ሰቆቃዋን ሰቆቃህ፤ ሕመሟን ሕመምህ አርገህ ኢትዮጵያን አስበሃል። በሰርግ አዳራሽ፤ በሃዘን ድንኳን፤ በገበያ አዳራሽ፤ በጎዳና፤ በእምነት ቤትህ፤ በሕዝብ ማመላለሻ ላይ ሆነህ ስለኢትዮጵያና ስለወገንህ ያለተወያየህበት፤ ያልሳቅህበት ወይም ያላዘንህበት ጊዜ አልነበረም። ሃገርህን ከመውደድህ የተነሳ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳ ላይ ዱላ ቀረሽ ውይይትም አድርገሃል። ተባብረህም የማይናቁ ተግባራትን ፈጽመሃል።

ለሃያ ሰባት ዓመታት ወያኔ የሚባል እርኩስ ቡድን ባራመደው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ፖለቲካ የአስር ሽህ ማይለ ርቀት ሳይገድብህ ሕገ አራዊትን ታግለሃል። አፋኙን፤ ዘረኛውንና ነፍስ ገዳዩን የሕወሃትን መንግሥት ገመና ለዓለም ህብረተሰብ አጋልጠሃል። የአሜሪካ፤ ካናዳ፤ አውሮፓ፤ አውስትራልያ፤ እስራኤል፤ መካከከለኛው ምስራቅ፤ አፍሪካ፤ አስያ፤ ወዘተ መንገዶችንና አደባባዮችን በሕዝባዊ ሰልፍ አጥለቅልቀሃል። ድምፅ ለሌለው ወገንህ ድምፅ በመሆን ሰቆቃውን ለዓለም ህብረተሰብ አሳውቀሃል። ለዴሞካራሲ፤ ለግለሰብና ሕዝቦች መብት መከበር ጥብቅና ቆመሃል።

ውድ ዲያስጶራ ሆይ፤ ያለምንም ማጋነን በመላው ዓለም ከሚገኙ ስደተኞች እንደ አንተ የሃገሩን የግፍ ፖለቲካ በዓለም መድረክ ያሳወቀ ማሕበረሰብ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። የኩባ ዲያስጶራ ከአሜሪካ በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ የካስትሮን መንግሥት ሊገዳደር የሚችል ጫና መፍጠር አልቻለም። ለዚያውም የአሜሪክ መንግሥትና መላው ምእራብ አሃጉር የቁሳቁስ፤ የገንዘብ፤ የዲፕሎማሲና የሃይል እርዳታ ለስልሳ ዓመታት እየቸሩት። በአንፃሩ የአንተ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ካለማንም ድጋፍ በራስህ ተነሳስተህ ለማመን የሚቸግር ገድል ሰርተሃል። በዚህ ልትኮራ ይገባሃል። የሃገርቤቱን ትግል በሁሉም ዘርፉ ደግፈሃል።

ኢሳትን፤ ኦኤምን፤ ዘሃበሻን፤ ዋዜማ፤ ኤስቢኤስንና ህብር ራዲዮን የመሰሉ መገናኛ ብዙሃን አቋቁመህ የሃገርቤቱን ትግል አቀጣጥለሃል፤ ሕዝብ አንቅተሃል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሃገር ቤት የተደራጁ ታጋዮችን ፋኖን ፤ ቄሮን ፤ ዘርማን በፋይናንስ፤ በሃሳብ፤ በቁሳቁስ፤ በማገዝ ታሪክ ሰርተሃል። ሕገ አራዊቱ ሕወሃት ተወግዶ ዶከተር ዓብይ ስልጣን ላይ እንዲመጣ የበኩልህን አድርገሃልና ልትኮራ ይገባሃል።

ዶር ዓብይ ሥልጣን ዶ፨ር። ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሚታነፅ ዴሞክራሲና በሕግ የበላይነት ላይ የሚቆም መስተዳድር ለማስፈን ላለፉት ስምንት ወራት ደፋ ቀና ብለዋል። የገጠማቸው ፈተና ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በዙ አንፀባራቂ ውጤቶችን በአጭር ጊዜ አስመዝግበዋል። አንገታችንን ቀና፤ ደረታችን ነፍ አርገን በኢትዮጵያዊነታችን ኮርተን እንድንሄድ አድርገውናል። ከዚህም የተነሳ በአምስቱ ክፍላተ ዓለም የምትገኘው ዲኣስጶራ ሁሉ ለክቡር ዓብይ ደጋፉህን ሰጠሃል። ዋሽንግተንና ሚኒሶታ በመጡበት ጊዜ በነቂስ ወጠህ ድጋፍህንና ፍቅርህን የገለጽህበት ሁኔታም ይታወሳል። በጥኋት ተሰባስበህ ወደ ስብሰባው አዳራሽ ለመግባት ያደርገኸው ስርዓት የተላበሰ ሰልፍ ተመልካቹን ሁሉ አስደምሟል። አዳራሹ የሚይዘው 25,000 ሆኖ እያለ 30,000 ሆነህ አዳራሹን አጨናንቀህ ከዓብይና ታማኝ ጋር ተደምረሃል። ቁጥሩ ክዚያ በላይ የሚሆን ሕዝብ ደግሞ ከውጪ ሆነህ በቴሌቪዥን ተከታትለሃል።

ጠ/ሚ ዓብይ ሲመጡ በአዳራሹ ውስጥ ሆነህ በጭብጨባ፤ በፉጨት፤ በሆታ፤ በእልልታ፤ የሳቅና ደስታ እንባ ታጅበህ ያደረግኸው አቀባበል አስለቃሽ ነበር። ያለምንም ማጋነን ሕዝብ ሲወድህ ምን ሊአደርግ እንደሚችል ግንዛቤን ሰጦናል።

ውድ ዳያስጶራ ወገኖቸ፥ከስምንት ወር በኋላ የሃገራችን ፖለቲካ ወደተፈለገው አቅጣጫ እየሄደ ለመሆኑ ፍንጮች ታይተዋል። አሁን ያለው እድል ማምለጥ እንደሌለበት ሳትገነዘብ አትቀርም። ሌላ አማራጭ ስለሌለ ጊዜ ሳታጠፋ ዓብይ ላቀረቡልህ ጥሪ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብሃል።። ድጋፍህ ከመነመነ ሕገ አራዊት ተመልሶ እንደሚጫንህ እመን። ያሲሆን ደግሞ ሰላሳ ዓመት ሙሉ የታገልህላትና የጮህላት ኢትዮጵያም አትኖርም። አንድ ዶላር በቀን ከዕለት ቡናህ ቆርሰህ መስጠት ላንት በጣም ትንሹ ነውና ዛሬውኑ እርዳ። ለገና እና ለዘመን መለወጫ የምታደርገውን ወጪ አስበው።

በቀን አንድ ምግብ ለማያገኘው፤ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በየጉድጓዱና ኩሬው የሚኳትነውን ወገንህን፤ የደብተርና እርሳስ መግዣ አጥታ ትምህርት መማር ያልቻለችውን ሕፃን አስታውስ። ለጠ/ሚ ዓብይ የገባሃውን ቃል ፈጽም። መደመርህን በተግባር አሳይ። ወቅቱ የኢትዮጵያንና የኢትዮጵዊነት ትንሳኤን ለናፈቁ ዜጎች ስለሆነ በአንድነት ተነስተህ ኢትዮጵያን ታደጋት። ዓብይ ከለውጡ ደጋፊ ዳያስጶራ የጠየቁት በጣም ትንሽ ነውና እንተባበራቸው። መልካም የፈረንጆች ዓመት ይሁንላችሁ። ኢትዮጵያ በእናንተ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር።

አቢቹ ነጋ ታሕሳስ ፪፻፩፰

LEAVE A REPLY