ዛሬ አንድ ጓደኛችን ሰርግ ላይ ለመገኜትና ለማጄብ ከጠዋቱ አራት ሰአት ላይ ተሰባስበን በቅርብ ርቀት ወደሚገኜው የሰርግ አዳራሽ እያመራን ነው።
ወደ አዳራሹ ስንቃረብ ከመሀከላችን አንዱ ድንገተኛ ጥያቂያዊ ሀሳብ አቀረበ
_ ለምን አንድ አዝማሪ አንጠራና የራሳችንን ድምቀት አንፈጥርም ?
ሀሳቡ ተቀባይነት አገኜና የባለማሲንቆ ስልክ ተፈልጎ ተደወለ ሂሳብ ተነጋገረ ተስማማ
ባልጠበቅነው ፍጥነት ደርሶ ማሲንቆውን እንዳነገተ ከባጃጂ ወርዶ ወደኛ እየተራመደ ነው
አይኑና ቀልቡ ግን በሙሉ ትኩረት በተወሰኑ ርምጃወች ቀድማ ወደሰርጉ ቦታ በምታመራ ውብና ለግላጋ ወጣት ላይ አርፏል።
ፓ !! አቤት ቁንጅና !! የእውነት ልዩ ናት ።
ሆኖም ያሳዝናል
አዝማሪያችን አይኑን እሷ ላይ እንደተከለ ከስሩ ያላየው ድንጋይ አደናቅፎት ኮብል ስቶን ላይ በቁሙ ተዘረረ ።
መቼም እንዳወዳደቁ ሰው ሆኖ የሚነሳ አይመስልም ነበር። እንደምንም ደጋግፈን አነሳነው
ተመስገን እንደፈራነው አልሆነም። ከክንዶቹ መላላጥና ከፊቱ መጫጫር በቀር የከፋ ጉዳት አልደረሰበትም። እንደነገሩ የመጄመሪያ እርዳታ አድርገንለት ስራውን ጄመረ።
ሆኖም አሁንም
ማሲንቆውን ገዝ ገዝ ከማድረጉ ከታዳሚው መሀል ያችን ቆንጆ በድጋሚ አያት
ሆኖም አሁን አልደነገጠም አልተደናቀፈም አልወደቀም።
.ማሲንቆውን ከርክሮ
ገጠመላት ገጠመባትንጂ .… … ……
እስኪ ልጠይቅሽ
እስኪ መልሽልኝ ውቢት ውባለም
አንቺ ጠይም ቆንጆ የፀዳል ሽልም
ድንገት ተከስተሽ እንደ ህልም አለም
ሰበር ሰካ ስትይ
በግሩም ቁመና በሰጎን ቅልጥም
ምን ትጠቀሚያለሽ
ከፊትሽ ወድቄ ጥርሴን ብለቅም ? … … …