ስለ ዜግነት ፖለቲካ ኦባንግ ይናገር! | ጌታቸው ሽፈራው

ስለ ዜግነት ፖለቲካ ኦባንግ ይናገር! | ጌታቸው ሽፈራው

ዜጋን የሚያውቀው ኦባንግ ነው። ስለ ዜግነት ፖለቲካ ኦባንግ ሜቶ ይናገር! ጋምቤላ ስለሆኑ አይደለም። ጎንደር የሚገኙትን ከወልቃይት የተፈናቀሉ አማራዎች ሄዶ አይቷል። በወልቃይት አማራ ሕዝብ ላይ የተፈፀመውን ሰቆቃ እንዲህ ፍዝዝ ብሎ አዳምጧል። የቡድኑ አባላት ስቃዩን ሲሰሙ እንባቸው ለመቆጣጠር ሲታገሉ ታዝቤያለሁ። ይህ ለዜጋ ከመጨነቅ የሚመጣ ስሜት ነው።

ራያ ላይ ስለሚፈፀመው ጭካኔ አውርተነው አዝኗል። ሄዶ እንደሚያያቸው፣ ይህን ባይችል ከወኪሎቻቸው ጋር ሆኖ የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግን ቃል ገብቶልን ነበር። በእርግጠኝነት ያደርገዋል! የአማራ ገበሬዎች ጋር ቁጭ ብሎ አውርቷል። የአፋሮችን ስቃይና መከራ አይቷል። አዝኖ ነግሮናል!

በዜግነት ፖለቲካ ስም ብዙው ስንፍና ውጦታል። ኦባንግ ጎንደር ሄዶ የጎበኛቸው ተፈናቃዮች አዲስ አበባ ድረስ መጥተው እንኳ ብቅ ብሎ ማየት አልፈለገም። እንደ ዜጋ ባይቆጥራቸው ነው፣ የዜግነት ፖለቲካ የተባለውን ሩቅ መንገድ ባይደርስበት ነው። የዜግነት ፖለቲካ አቀነቅናለሁ እያለ በዛ ጥሩ ስም ላይ የተወዘፈበት ሁሉ ልክ እንደ ኦባንግ ከልቡ ቢይዘው የ”ብሔር” ፓርቲ እያሉ የሚጮሁበት ባልተፈጠረ ነበር።

ከኦባንግ ጋር ስለተበደሉት ስታወራ “አማራ አማራ አትበል፣ የኦሮሞን ስም አትጥራ፣ ጉራጌ ምን ሆን?” አይልህም። ስለ ስቃያቸው ስታወራ “ጎጠኛ” አይልህም። “ጎሰኛ” ብሎ አይፈርጅህም። በቁስላቸው ላይ በርበሬ ነስንሶ አያሳዝንህም። ህመማቸውን፣ ህመምክን ይጋራሃል። የሚፈለገውኮ ይሄ ነበር።

በዜግነት ፖለቲካ ስም የሚነግደው ሁሉ ግን ስለመከረኛ ሕዝብ ስታወራው “ቁስል እየቀሰቀስክ አታብስ” ይልሃል። ህመሙ የሚያስጮኸው ሰው ላይ “አፍክን ዝጋ” ብሎ ማንባረቅ ምን አይነት ኢ ሰብአዊነት ነው? የፈለገ ይበድሉህ ለሀገር ስትል ዝም በል ማለት ምን አይነት ጨካኝነት ነው? የዜጎችን ጩኸት አልሰማም እያሉ የዜግነት ፖለቲካን አራምዳለሁ ማለት ምን አይነት ድንቁርና ነው?

የዜግነት ፖለቲካ አራምዳለሁ የሚለው ሁሉ ልክ እንደ ኦባንግ ከልቡ ቢሆን ኖሮ ያን የላቀ የፖለቲካ መስመር ባላቆሸሸው ነበር። ለሰልፍና ስብሰባ ሲሆን ህፃናትን ይዞ አደራሽና ጎዳና የሚወጣው፣ ሰንደቅ አላማ ያዙ ብሎ የሚያስቸግረው ሁሉ ህፃናትና እናቶች ሲገደሉ እንደ ዜጋ ቆጥሮ፣ አዝኖላቸው በተግባር ቢያሳይ የምር የዜግነት ፖለቲካ ባሸነፈ ነበር። አሁን ግን የዜግነት ፖለቲካን በቀረርቶና ሽለላ ብቻ አደረጉት። እነ ኦባንግን የመሰሉ ጥቂቶች ብቻ ከልባቸው ይዘውታል!

ስለ ዜግነት ፖለቲካስ ኦባንግ ይናገር! ሌላው ውሸቱን ነው! ሌላውስ የዜጎችን ቁስል የሚያመረቅዝ ነው። “ዝም በል፣ አትናገር” እያለ ለገዥዎች፣ ለበዳዮች ጠበቃ የሚሆን ነው። ስሙ እየተጠራ የተበደለን ሕዝብ ቁስል ስቃይ ስትናገር “ጎጠኛ፣ ጎሰኛ” እያለ የራሱን ውዝፍነት፣ ስንፍና፣ ግድ የለሽነት፣ ነጋዴነት ለመሸፋፈን የሚጥር ነው።

ኦባንግ ለዜጎች የምር ስሜቱን ስለገለፀ፣ ዜጎችን ስላልካደ ፕሮፖጋንዳ ሳያበዛ፣ ቅስቀሳና አቀባበል ሳያደርግ በዜጎች ልብ እየነገሰ ነው። በተቃራኒው የዜግነት ፖለቲካ እያለ ሲጮህ እየዋለ በተግባር በዜጎች መከራና ስቃይ የሚቀልደው ግን የፖለቲካ ግብአተ መሬቱን እያፋጠነ ነው! የውድቀት አፋፍ ሲሆን ደግሞ ይብስበታል! ብሶበታልም!

ስለ ዜግነት ፖለቲካስ ኦባንግ ይናገር!

LEAVE A REPLY