ከቀናት በፊት በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኘው የእነጋትራ ሃና ገዳም አስተዳዳሪ የነገሩኝን የድረሱልን ጥሪ ፌስቡክ ላይ ለጥፌ ነበር።
ለዚህ መልስ የሚሆን ፅሁፍ /ከዳናዊትአበበ/ ደርሶኛል። ዝርዝሩ ይኸው:
“የገዳሙ አስተዳዳሪ ያነሱት ጉዳይ እንዲህ በጥቂት ጊዜ የተፈጠረ ሳይሆን ምናልባት ከሁለት አስርት አመታት በላይ ያስቆጠረ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎችና እነጋትራ አንደኛ ደረጃ በተለያየ ወቅት ያስተማሩ መምህራን ስለ ጉዳዮ የሚከተለውን ብለውኛል( አካባቢው ገጠር እንደመሆኑና ተመላልሶ ማስተማር ከባድ እንደመሆኑ ት/ቤቱ ውስጥ እንደነገሩ ሆና የተሰራች ቤት በሸንበቆ ተከፋፍላ ለመምህራን ተሰጥታ እዛው ት/ቤቱ ውስጥ ይኖሩ ስለነበር ጉዳዮንና ችግሩን በደንብ ያውቁታል)።
በተባለው ገዳም ውስጥ አንዲት መናኝ መነኩሴ ከሁለት መንትያ ሴት ልጆቻቸው ጋር ይኖሩ ነበር። ከሁለቱ መንትያ ሴት ህፃናት ውስጥ አንዷ ህፃን ዮዲት ስትባል በመነኮሳቱና በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ወደፊት መከራ ታመጣለች የሚል ንግርት ነበር ይላሉ…ነዋሪዎቹ። ከጥቂት አመታት በኋላ ይቺ ልጅ ትጠፋለች። ዮዲት ወደ ገዳሙ የተመለሰችው ከረጅም አመታት በኋላ ሲሆን ስትመለስ ግን ብቻዋን ሳይሆን ከአንድ ወጣት ሰው ጋር ነበርወጣቱም ገዳሙን ተዘዋውሮ ተመልክቶ ተመልሶ ወደመጣበት ሄደ። ይህ ሁሉ የሆነው በደርግ ዘመነ መንግስት ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ አንድ መነኩሴ ቆቡን ደፍቶ ወደ ገዳሙ መጣ።
ይህ መነኩሴ ከአመታት በፊት ወደ ገዳሙ መጥቶ የነበረው ወጣት ሲሆን አሁን ግን ስሙ አባ ገብሬ ተብሎ ምንኩስና ተቀብያለሁ ይላል። የመጣሁት ከጎንደር ነው ቢሉም የአካባቢው ነዋሪ ግን ከትግራይ እንደመጡ ይናገራል። እኚህ ሰውዬ መልዕክቱን የላኩልህ የገዳሙ አስተዳዳሪ ናቸው።
ሰውየው ወደ አካባቢው እንደመጡ ከማህበረሰቡ ጋር በጣም መልካምና ጥብቅ ግንኙነት ነበራቸው።
ገበሬው ዝናብና ዶፍ እህሉን ያወድምበት የነበረውንም ሰውዬው መላ አበጁለት። የተቸገረ ይረዳሉ። በሬ ለሌለው በሬ…ቤት መስራት ጀምሮ አቅም ላነሰው በጎደለ እየሞሉ መልካም ስምና ተቀባይነት አገኙ። የአካባቢው ህዝብም “የተባረኩ አባት አገኘን” ብሎ በተራው ለእሳቸው ምን ማድረግ እንዳለበት ከመከረ በኋላ ህዝቡ በጋራ የሚጠቀምበትን የወል መሬት አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። ሰውየውም የዋዛ ስላልነበሩ በየቦታው እየሄዱ ቃለ ጉባኤ እያስያዙ የህዝቡን መሬት በእጅ አደረጉ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ህዝቡ ሰውየውን መጠራጠር ጀመረ። መሬታችንን ተዘረፍን ማለትም ጀመረ። ሰውየው እኩይ አጀንዳ እንዳላቸው ጠረጠረ። ተጭበረበርን አለ።
አስተዳዳሪውም ከእርሳቸው በፊት የነበሩ የበቁ መነኮሳትና መናንያንን አባረሩ። ገዳሙንም ለብቻቸው ያዙት። ጠመንጃ ይታጠቃሉ።
በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ያለው የሚታረስ መሬት እጥረትና መጨናነቅ ደግሞ ችግሩን አባባሰው። አንድ እርምጃ የማትሞላ መሬት ገፋኸኝ ተብሎ ሰው እርስ በርሱ በሚጋደልበት አካባቢ አስተዳዳሪው በገዳሟ ስም ይሄን ያህል መሬት መያዛቸው ደግሞ ችግሩን እንደሚያባብሰው ግልፅ ነው።
ህዝቡም ተሰብስቦ “መሬታችን ይመለስልን” አለ። እርሳቸው ግን “ምነው ነገሩን የህፃናት ጨዋታ አደረጋችሁት…ከሰጣችሁ በኋላ መልሶ መውሰድ የለም” አሉ። ህዝቡ ለአስተዳደር አካላት አቤት ቢልም መሬቱ የተላለፈው በህጋዊ መንገድ በመሆኑ ምንም ማድረግ እንደማይቻል ተነገራቸው።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአካባቢው የህፃናት ጋብቻ በጣም የተለመደ በመሆኑ እነኚህ ህፃናት ሴቶች ከቤተሰብ ሲጣሉ ጸብ እንዳለ ስለሚያቁ ሮጠው ወደ ገዳሙ ይሄዱ ጀመር። ባልየው ሚስቱን ሊወስድ ወደ ገዳሙ ሲሄድም ” ድሮ ነበር እንጂ ሚስትን ተንከባክቦ መያዝ..አሁንማ መነኮሰች እኮ..ቆብ አስጥለህማ መውሰድ አትችልም” ተብሎ አንገቱን ደፍቶ ሲመለስ እሳቸው ለሴቶቹ ሌላ ሥም ያወጡላቸዋል።
“እማሆይ አትጠገብ” “እማሆይ ሥነ ፀሐይ”ብለው ሲጣሩ ራሱ በጆሮየ ሰምቻለሁ ብላኛለች አንድ መምህርት። ህዝቡም መሬታችንን ብቻ ሳይሆን ሚስትና ልጆቻችንን ጭምር ዘረፉን ማለት ጀመረ።
በአስተዳዳሪውና በህዝቡ መሃከል ችግሩ በጣም ከመባባሱ የተነሳ ሰውየው ሲያጠምቁ እንኳን ጠመንጃቸውን ከትክሻቸው አይለዮም። ህዝቡም ጥይት አይመታቸውም ብሎ አምኗል። ገዳሙ ውስጥ ሰውየው ብቻቸውን ባላቸውን ጥለው ከመጡ ወጣት ሴቶች ጋር ይኖራሉ። ገዳሙ ውስጥ ቴሌቪዥንን( ወቅቱ በ1990ዎቹ ነው)ጨምሮ የሌለ ነገር የለም። ወደ ሆነ ቦታ መንቀሳቀስ ሲፈልጉ ስልክ ወደ ሉማሜ አስተዳዳሪው ዘንድ ይደውላሉ። ኮብራ መኪና ይላክልቸዋል።
ከህዝቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም ከመበላሸቱ የተነሳ በልዮ ሃይል ይታጀቡ ጀመር። ለበዓላት ታቦት አይወጣም። ወጥቶም አያውቅም። ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን አይሄድም። በገዳሙ በኩል ራሱሱ ሲያልፍ ጥይት ይመታናል በማለት በሩጫ ያልፍ ነበር። ሊቃውንት በሞሉበት አገር ከሳምንት አንድ ቀን ከደብረ ማርቆስ ቀሳውስት አበል ተከፍሏቸው መጥተው ይቀድሳሉ። ሰውየውም ህዝቡን ለማስፈራራት ከስዮም መስፍን፣ ከአዜብ መስፍን እንዲሁም ከሌሎች ትላልቅ ባለስልጣናት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ያወራሉ። ያስወራሉ። ማህበረሰቡም “ጅኒናር ገብሬ” ብሎ ይጠራቸው ጀምሯል።
ህዝቡ ቂም ቋጥሮ ትክክለኛውን ጊዜ ሲጠብቅ ከኖረ በኋላ ሰውየው ወደ ሌላ ቦታ የሚሄዱበትን ወቅት እርምጃ ለመውሰድ መከረ። ከላይ እንደነገርኩህ ሰውየው ከሉማሜ ኮብራ ተልኮላቸው በመኪና ስለሚንቀሳቀሱ የመኪናዋ መምጣትና መሄድ የሰውየውን መኖር አለመኖር ይጠቁማል።
ያናገርኳት መምህርት የሚከተለውን ነግራኛለች “በ1999 ዓ.ም የተወሰኑ ገበሬዎች ዛፍ ጥላ ስር ተሰብስበው ነበር…የፀረ ኤድስ ክበብ ሰብሳቢ ስለነበርኩኝ በሳምንት ለተወሰነ ጊዜ ስለ ኤች አይ ቪ እናስተምር ነበርና ወደ እነርሱ ጉዞ ስንጀምር ገበሬዎቹ “መምህርት ወዲህ ከሆነ ተመለሱ። ምንም አንሰማም አሁን” ብለው አስመለሱን። ወዲያው ጥሩንባ መንፋት ተጀመረ። ህዝቡም ያገኘውን መሳሪያ ጠመንጃ ያለው ጠመንጃውን ሌላውም መጥረቢያውን ያገኘውን ይዞ ወደ ገዳሙ ተመመ።
ሰውየው ስለሌሉ ገዳሙ ውስጥ የቀሩት ሳይመነኩሱ መነኮሱ እየተባሉ ቆብ የደፉት ከባሎቻቸው የጠፉት ሴቶች ብቻ ነበሩ። ህዝቡ ገዳሙ ውስጥ የተሰበሰበውን እህል ዘርፎ ተካፈለ። ውስጥ የተገኙ የእጅ ቦንቦች ሳይቀር ዘረፈ። ገዳሙ ውስጥ ሲያገለግሉ በነበሩ ሊቃውንት የተጻፉ የብራና ፅሁፎችንና መጻሕፍትን ልጆቻቸው የአባቴ ነው የአያቴ ነው በሚል ወሰዱ። ከዘረፋው በኋላ ገዳሙ ውስጥ የሚገኘውን የአስተዳዳሪውን ቤት አቃጠሉት። ገበሬዎቹ ያሰቡት ቤቱ መቃጠሉን ሲሰማ ሰውየው ወደዚህ አይመለስም ብለው ነበር።
በግርግሩ ወቅት ወደ ሰማይ እተኩሳለሁ ብሎ የሴት ልጁን እጅ የመታ ገበሬም ነበር። በሁለተኛው ቀን ሰውየው አማርኛ የማይሰሙ የማይናገሩ ወታደሮችን ይዞ ከች አለ። የአካባቢውን ገበሬ ከትምህርት ቤቱ ፊት ለፊት ያለ የኮረኮንች መንገድ ላይ አናት አናቱን እያሉ አነጠፉት።
ዘርፌ አመልጣለሁ ብሎ የነበረን ገበሬ ሁሉ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ከደበደቡት በኋላ ጥቂቶቹ ጋር ደብረ ማርቆስ ክስ ተመሰረተባቸው። ጉዳዮ እንዲህ ተሸፋፍኖ ለአመታት ከዘለቀ በኋላ አባ ገብሬ ገዳሙን አድኑልኝ የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ አንተም ስትዘግበው ሳይ ሁለተኛና ሶስተኛ ክፍል እያለሁ እነጋትራ የምታስተምር እህቴ ስለ ሰውየው ስትናገር የሰማሁት ትዝ ብሎኝ የሚያርሰው ኩርማን ታክል መሬት አጥቶ ወደ አዲስ አበባ የሚሰደደው የአካባቢው ገበሬ ነው ትዝ አለኝ። የተወጋ ቢረሳ የወጋ አልረሳ አለ ብሎ ነበር ጃዋር።
ህዝቡ ከአስተዳዳሪው እንጂ ከገዳሙ ችግር የለበትም። ዘንድሮ ለጥምቀት ታቦት አልወጣም የሚሉት ድሮም ታቦቱ ወጥቶ አያቅም። ስንት የበቁ አባቶችን አባረው ለብቻቸው ገዳሙን ከያዙት ዘመናት አለፉ። እነሞጨራ የሚባል ሃገር ከዚህ ገዳም ወጥተው የሚኖሩ አንዲት አይነ ስውር መነኩሲት እስከ ቅርብ ጊዜ ነበሩ። ብቻ ገዳሙ ገዳምነቱን ትቶ የሰውየው የግል ንብረት ሆኗል። ህዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን አይመጣም። ክብረ በአላት አይከበሩም። ታቦት አይወጣም። መኖሩን የሚጠራጠሩም አሉ።
ለውጥ መጥቷል ከተባለ በኋላ በተለመደው ዘዴ ህዝቡን አስፈራርተው መኖር አልተቻላቸውም። ባለፉት ዘመናት ህዝቡን ለማስፈራራት ከትላልቅ ባለ ሥልጣናት ጋር ግንኙነት አለኝ ብለው ሲያስወሩ መኖራቸው ደግሞ በህዝቡ ዘንድ የድሮው ስርአት ደጋፊና ባለሟል ስለሆኑ አገራችንን ይልቀቁልን፣ መሬታችንንም ይመልሱልን የሚል ጥያቄ አስነስቷል።