የበረከት ስምኦን መታሰር ብዙም sense አይሰጥም. | መሐመድ አሊ መሐመድ

የበረከት ስምኦን መታሰር ብዙም sense አይሰጥም. | መሐመድ አሊ መሐመድ

በረከት ስምኦን በተለይ በዘመነ-መለስ ዜናዊ የህወሓት/ኢህአዴግና የሚመራው መንግሥት ሁለተኛ ሰው ነበር ሰው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በረከት በድርጅቱም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ሁለተኛ ሰው ተደርጎ ይታይ የነበረው ለመለስ በነበረው ቅርበት ሳይሆን በብቃቱ እንደነበር አይካድም፡፡ አቶ መለስም በብቃት ደረጃ ሰው ቁጠር ቢባል ከራሱ ቀሎ “በረከት” እንደሚል አያጠራጥርም፡፡ በእኔ እይታና ግምገማ፣ የመለስም ሆነ የበረከት ብቃት በአራት መሠረታዊ መለኪያዎች ሊገለፅ ይችላል፡፡

አንደኛ ሁለቱም የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ጠላት ተኮር አስተምህሮና የአፈና ስልቶች ጠንቅቀው የሚያውቁና በእሱም የሚራቀቁ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር የማይታረቅ ቅራኔ መኖሩንና ግንኙነታቸውንም የአጥፊና ጠፊ አድርገው በመሳል ረገድ ሁለቱ ሰዎች ወደር አይገኝላቸውም፡፡ ሦስተኛ ተቀናቃኞቻቸውን ጠልፈው መጣል የሚችሉበትን ሴራ በማውጠንጠንና በረቀቀ ስልታቸው እየገፉ ወዳስቀመጡላቸውና በቀላሉ መውጣት ወደማይችሉበት ወጥመድ የማስገባቱን ጥበብ የተካኑና በሌሎች ውድቀት የሚሳለቁ ጨካኞች ናቸው፡፡ አራተኛው ሁለቱም ቅንነት በጎደለው መንገድ፣ በፀጉር ስንጠቃና በቃላት ጨዋታ የሚራቀቁ፣ ሌሎችን ለማሳሳት የሚችሉ፣ በተንኮል የተሞሉ አደገኛ ሰዎች ናቸው፡፡

መለስ ዜናዊ በረከት ስምኦንን በእጅጉ ይፈልገውና ይጠቀምበት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ለአብነት ለማሳዬት ያህል፣ መለስ ከተቀናቃኞቹ ጋር ለመነጋገርና ሴራ ለመሸረብ በረከትን የሚተካ ሰው አይታዬውም፡፡ በግሌ በረከት ስምኦን በሚመራቸው የ”ድርድር” (ተብዬ) መድረኮች የተካፈልኩ ሲሆን ሰውዬው (በረከት) ተቃዋሚዎች የሚናገሩትን ብቻ ሳይሆን የሚያስቡትንም ጭምር አውቃለሁ ባይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን; በሀሳብ ሲሸነፍና ማጣፊያው ሲያጥረው በድርድሩ መሐል ወጣ ብሎ ቆይቶ ይመለሳል፡፡ ይህን የሚያደርገው ከመለስ ጋር ለመነጋገር የሚገመት ሲሆን ብዙውን ጊዜ በአሉታዊ መንፈስ ተሞልቶና ተኮሳትሮ ነው የሚመለሰው፡፡ በዚህ መንፈስ ከተመለስ በኋላ፣ በሀሳብ መሞገቱን ትቶ ዛቻና ማስፈራሪያውን መደርደር ይጀምራል፡፡ ከተደራዳሪዎቹ መካከልም በበረከት ዛቻና ማስፈራሪያ ኩምሽሽ ብሎ ድርድሩን የሚቀጥል ሲኖር፣ የደፈረ ሙግቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፣ ወይም የድርድር መድረኩን ረግጦ ይወጣል፡፡

ይህን ተከትሎ እነመለስ/በረከት በተቀናቃኞች ላይ አደገኛ ሴራ ይሸርባሉ፤ ያለርህራሄ “አከርካሪያቸውን የሚሰብር” የሚሉትን እርምጃ ይወሰዳሉ፡፡ በቀድሞው ኦነግ፣ ቅንጅትና ሌሎችም ተቀናቃኝ ኃይሎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ለዚህ ማሳያ ናቸው፡፡ እነመለስ ተቀናቃኝ ለሚሏቸው ይቅርና መከራውን አብረዋቸው ላለፉት የትግል ጓዶቻቸውም የሚራራ ልብ የላቸውም፡፡ ይኸ ደግሞ ገና በለጋ ዕድሜያቸው በህወሓት ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውንና “ህንፍሽፍሽ” ብለው የሚጠሩትን የውስጥ ችግር የፈቱበት መንገድና አብሯቸው ያደገ “ሰው ባላ” አካሄድ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር፣ በረከት ወደኋላ ላይ በረቀቀ ሴራና ተንኮሉ የሚታወቅ፣ የመለስ ቀኝ እጅና በሥርዓቱም ውስጥ የሚፈራ ሰው መሆን ችሎ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በረከትን የሚፈራው ራሱ መለስ ዜናዊ ጭምር እንደነበር በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ እኔ እንደማስበው፣ መለስ የሚያውጠነጥነውን ሴራ “እንከን የለሽ”ነት የሚያረጋግጠው ለበረከት ስምኦን ካካፈለውና በእሱ እይታ ካነጠረው በኋላ የሚመስለኝ ሲሆን የበረከት የተንኮል ብቃትና የመለስን አስተሳሰብ በቅርብና እስከጥግ ማወቁ በመለስ ዜናዊ ዘንድ ስጋትና ፍርሃት ሳይፈጥር አልቀረም፡፡ በወቅቱ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ቢለቅም “ሊተካው የሚችለው የቅርብ ሰው በረከት ስምኦን ነው” የሚሉ ግምቶች የመለስን ሥጋት የሚያጠናክሩና ሰውዬውን ገፍቶ/ከእይታው ሳያርቅም በነፃነት ሳይለቅም በጥንቃቄ እንዲይዘው የሚያደርጉ ነበሩ ማለትም ይቻላል፡፡

ለዚህም ይመስላል፣ መለስ ዜናዊ በረከት ስምኦንን ቀና ባለ ቁጥር ሲኮረኩመውና ከደረጃው ዝቅ በማድረግ የሌሎች መነጋገሪያ ሲያደርገው የነበረው፡፡ ባንድ ወቅት የመንግሥት ጉዳዮ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ሚንስትር አድርጎ ሲያስቀምጠው፣ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ጨዋነትና ትዘብት በተቀላቀለበት አነጋገር “እንዳው ግን የጽ/ቤት ሚኒስትር የሚባል ነገር፣ አቶ በረከት እርስዎንስ ያሳምነዎታል? እንዴትስ ይቀበሉታል?” ሲሉ ጥያቄያቸውን ከመለስ ወደበረከት በማዞር እንደዋዛ በፓርላማው ውስጥ የነበርነውን አስቀውናል፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን በቀጥታ ሲሰራጭ የነበረውን የፓርላማ ክርክር ሲከታተል የነበረው ህዝብም በስፋት መሳቁ ተነግሯል፡፡ “ወድደው አይስቁ” አሉ!!!

የጽሁፌ ዓላማ፣ በረከት ስምኦን (ልዕለ-ኢህአዴግ መለስ ዜናዊ በመሩት) በዚያ አስከፊ/የግፍ ሥርዓት ውስጥ የማይተካ ሚና (indispensable role) እንደነበረው ማሳዬት ነው፡፡ ያ ሥርዓት ደግሞ የሀገርን ህልውናና ጥቅም አደጋ ላይ በመጣል፣ የሀገርን አንጡራ ሀብት በመዝረፍ፣ ጥቂቶች በአቋራጭ የሚከብሩበትን; በአንፃሩ ብዙሃኑ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚማቅቅበትንና በፈታኝ የኑሮ ውድነት የሚሰቃይበትን ሁኔታ በመፍጠር፣ ይህም አልበቃ ብሎ ዘርን መሠረት ያደረጉ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ወንጀል ሊጠየቅ የሚገባው ነው፡፡ በዚያ ሥርዓት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፤ ሌሎች በርካቶች በአካላቸው ላይ እጅግ አሰቃቂ፣ ዘግናኝና አረመኔያዊ የጭካኔ ድርጊቶች ተፈፅመውባቸዋል፡፡ በዚያ ሥርዓት፣ ኢትዮጵያውያን በዘርና/በቋንቋ በመከፋፈል፣ የተበዳይና በዳይነት ትርክቶችን በመፍጠር፣ በርካታ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ ለጥቃት እንዲጋለጡ፣ ጥረው ግረው ያፈሩትን ሀብትና ንብረት ጥለው/ተነጥቀው ከሚኖሩበት አካባቢ እንዲፈናቀሉ፣ ሌሎች በርካቶች ደግሞ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርጓል፡፡ ዛሬም ቢሆን ሥርዓቱ ከፈጠረው አስፈሪ ሁኔታና ሥጋት በቀላሉ መላቀቅ አልቻልንም፡፡

ስለሆነም በሀገር ደህንነትና ህልውና፣ በዜጎች ሰብኣዊ መብቶች፣ በሀገር አንጡራ ሀብትና በመሰል አበይት ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደረሱና እስካሁንም የቀጠሉ የሀገርና የህዝብ ደህንነት ሥጋቶችን የፈጠሩ የሥርዓቱ ፊታውራሪዎች በአገሸባቡ ለህግ መቅረብና መጠየቅ አለባቸው፡፡ ምናልባትም በአንዳንድ ወገኖች እይታ፣ የእነሱ ለህግ መቅረብና መጠየቅ በሀገር ደረጃ የሚጨበጥ ፋይዳ የሌለውና ለብሔራዊ እርቅ እንቅፋት የሚፈጥር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በእርግጥ በሀገር ደረጃ ብሔራዊ እርቅ ለመፍጠር ያለፈውን መተውና ይቅር መባባል እንዳለብን እሙን ነው፡፡ ይሁንና፣ እውነተኛ ብሔራዊ መግባባት፣ ከልብ የመነጨ ይቅርታና እርቅ ሊፈጠር የሚችለው ተበዳይና በዳዩ በግልፅ ታውቆ፣ የተበደለው ሲካስ ወይም “ይቅር” የሚልበት ሁኔታ ሲፈጠር ነው፡፡

አሁን እየሆነ ያለው ግን; አነጋጋሪና አስተዛዛቢ ነገር ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናዬው; በዚያ አስፈሪ ሥርዓት ውስጥ ትዕዛዝ በመስጠትና በቀጥታ ወንጀል በመፈፀም የሚታወቁ ሰዎች ለህግ መቅረብና ተጠያቂ መሆን አልቻሉም፡፡ እንዳውም በከፍተኛ የሰብኣዊ መብት ጥሰትና የሀገርን ሀብት በመመዝበር ወንጀሎች ተከስሰው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የነበሩ ሰዎች በዋስ እየተለቀቁ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ ወገኖች ጩኸትና ተገቢ ያልሆነ ከለላ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመያዝ ባልተቻለበት ሁኔታ አንድ በረከት ስምኦንን በተራ “የሙስና ወንጀል ተጠርጥረዋል” በሚል ወደ ባህርዳር መውሰድ ብዙም sense አይሰጥም፡፡

የበረከት ጉዳይ ስሜት የማይሰጠው ከበርካታ ወንጀለኞች መካከል እሱ ብቻውን ተነጥሎ መታሰሩ አይደለም፡፡ ይልቁንም “ተጠርጥሮበታል” ተብሎ የተገለፀው ወንጀል፣ ባለፉት 27 ዓመታት በሀገር ጥቅም፣ ደህንነትና ህልውና ላይ ከደረሰው አጠቃላይ ጉዳት፣ በንፁሃን ዜጎች ላይ ከተፈፀሙት ፈርጀ-ብዙ ግፍና በደሎች፣ ቢያንስ በሚዲያ ከሰማናቸውና ካየናቸው ዘግናኝ; አረመኔያዊና የጭካኔ ድርጊቶች አንፃር በበረከት ስምኦን “ተጠርጥሮበታል” የተባለው ወንጀል ጉዳዩን እጅግ አቃልሎ እንደማዬትና በህዝብ ስሜት ላይ እንደመቀለድ የሚቆጠር ነው፡፡ ስለሆነም በሀገር ደረጃ በተቀናጀ መልኩ ተገቢው ማስረጃ ተሰብስቦና ተጠናቅሮ በዚያ አስከፊ/የግፍ ሥርዓትና በሥርዓቱ ፊታውራሪዎች ላይ ተገቢው ክስ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ሌላውን ነገር ከዚያ በኋላ የምንደርስበት ይሆናል፡፡

ከወንጀል ቅጣት ዓላማዎች አንዱና ዋናው “ማስተማር” መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል!!!

LEAVE A REPLY