ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው የሚነሱት ግጭቶች የፈረንጆቹን አባባል elephant in the room (ዝሆን በቤት ውስጥ) አስታወሰኝ።
እንዳየሁት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ግጭቶች ለማስቆም ብዙ ስራ እየተሰራ ነዉ። ያንንም ችግር የሚመለከትና ምፍትሄ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ በመንግስት በኩል የሰላም ሚንስቴር (Peace Ministry) ተቁዋቁምዋል። ህዝብን ለማግባባት በፌድራልም ሆነ በክልል መንግስታት ጥረት እየተደርገ ነዉ። የመንግስት ሙከራ መልካምና የተመሰገነ ሆኖ ሳለ አንድ ነገር ይጎለዋል ብዬ አምናለሁ።
የግጭቶቹ መንፅኤ በሚገባው መልኩ አይታይምም በግልጽም አይነገርም ብዬ አምናለሁ። መንፅኤው ካልተመረመረና በግልጽ ውይይቶች ካልተደረገበት ለችግሮቹ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሊገኝላቸው አይችልም።
ወደድንም ጠላንም የአብዛኛው ግጭቶኝ መንፅኤ ብሄርተኝነት ነዉ። ይሄንንም ያመጣው የሀገሪቱ የፌደራል ሲስተም አወቃቀር ይመስላል። በአንድ ሀገር ውስጥ ዘጠኝ ሀገሮች የተመሰረቱበት ሁኔታ ነዉ ያለው። የብሔር እኩልነትንና ህዝብ በራሱ ቅዋንቅዋ እየተነጋገረ ባህሉን እያዳበረ እንዲኖር የማይፈልግ ማንም አለ ብዬ አላምንም። ቢሆንም ሃገርን ሁለተኛ አርጎ ብሔርን ያስቀደመ ሲስተም መጨረሻው ግጭትና ውድቀት ይሆናል። ግጭቱንም እያየንው ነዉ።
አካሄዳችን ፈረንጆች እንደሚሉት the elephant in the room አይነት ነዉ። ቤታችን ውስጥ ትልቅ ዝሆን እያለ እንደሌለ አርገን ባጠገቡ እንደማለፍ ነዉ። አንድ ቀን ያዝሆን ተነስቶ ቤታችንን ከማፍረሱ በፊት ዘለቄታዊ መፍትሔ ቢፈለግለት ይመከራል።
በመጀመሪያ ደረጃ ዝሆኑ ቤታችን ውስጥ እንዳለ መቀበል ይኖርብናል። ቀጥለንም እንዴት ቤታችን ውስጥ ሊገባ ቻለ; ኖሮስ ምን ጠቀመን; መውጣት አለበት ካልን እንዴት በሰላም እናስወጣዋለን; ይቅርም ካልን ቤቱን ሳያፈርስ እንዴት አብረን መኖር እንችላለን የሚሉትን ጥያቄዎች በግልጽ ተወያይተን ላሉት ግጭቶች ዘለቄታዊ መፍትሔ ማግኘት ይጠበቅብናል።