ጉዞ ዓድዋ 6 – በህብረ ቀለሟ ከሚሴ /ያሬድ ሹመቴ/

ጉዞ ዓድዋ 6 – በህብረ ቀለሟ ከሚሴ /ያሬድ ሹመቴ/

~የዘመን ድራማ ከዋክብት ስንቅ ቋጥረው ከሚሴ ተገኝተዋል።

~ተዋናይ ሰለሞን ቦጋለ በባዶ እግሩ የሚጓዘውን ኤርሚያስ መኮንን በልመና አሳምኗል።

~”የዓድዋ ድል የእናንተ ብቻ ድል አይደለም” አሜሪካዊው ፎቶግራፈር Matt Andrea

*ቀሎ ከተባለችው ከአዲስ አበባ በ315 ኪ.ሜ. ከምትርቀው የገጠር መንደር የዘንድሮ ጉዞ ዓድዋ 6 ዘማቾች ለንባባ ረፍት በአንድ አዛውንት ቅጥር ግቢ ተገኝተዋል። ስንቅ ቋጥረው ተጓዦችን ለማበርታት ከአዲስ አበባ የተነሱት፣ በደራሲ መስፍን ጌታቸው የሚመሩት የዘመን ድራማ አባላት ከተሟሟቀው የታሪክ ንባብ መሐል ከተፍ አሉ።

*ተጓዦች በድንገቴው ክሰታ (ሰርፕራይዝ) ተገርመው ለሰላምታ ተረባረቡ። አመለ ሸጋው ሰለሞን ቦጋለ ዓይኑ የሥስት እንባ እንደቋጠረ ሁሉንም እየዞረ በማቀፍ ሰላምታ ሰጠ። ደራሲ መስፍን ጌታቸው እና ተዋናይት ሩታም ተጓዦችን በሙሉ እያቀፉ ሳሙ።

*ለደቂቃዎች የተቋረጠው ንብባ ቀጠለ። ስንቅ ሰፋሪ እንግዶች በተቀመጡበት የበርሊን ጉባኤን እና የአውሮፓ ኃያላኑ የአፍሪቃ ቅርምት ውል ንባብ ከየመጻህፍቱ መነበቡ ቀጠለ።

* ደራሲ መስፍን ጌታቸውና ባልደረቦቹ ከንባብ ፍፃሜው በኋላ በአገልግል ይዘው የመጡትን ጣፋጭ የአገልግል ስንቅ ተጓዦችን እየዞሩ በማጉረስ ያማረ የእለት ግብር ወጣ።

*ሰለሞን በተደጋጋሚ አንድ ጥያቄ ይጠይቃል። “ኤርሚያስ አሁንም አልደረሰም?” ኤርሚያስ መኮንን በተመደቡለት ሶስት የጉዞ ጓዶቹ ድጋፍ ከኋላ በእርጋታ እየመጡ መሆኑን ሰለሞን አይቷል። የኤርሚያስ የስቃይ እርምጃም አንጀቱን አንሰፍስፎታል። ከምንም በላይ ደግሞ እሱና ረዳት ጓዶቹ የእውቀት ልውውጥ ጊዜው እያለፋቸው መሆኑ አሳስቦታል። “እግሩ ላይ ወድቄ በባዶ እግሩ መጓዝ እንዲያቆም እለምነዋለሁ” ብሎ ምሳውን አቋርጦ ከመስፍን ጋር ወደ ኋላ ተመለሱ።

529E62CB-38E9-4AAF-BF08-09BCFD4F721D*መስፍንና ሰለሞን ኤርሚያስን ደግፈው ይዘውት ደረሱ። ኤርሚያስ በአገልግል ክዳን የተቀመጠለትን ምግብ እየጎረሰ ከሰለሞን ቦጋለ ጋር መወያየት ጀመሩ። ልቡ የተነካውን ሰው ልመና መቋቋም ያልቻለው ባለ ባዶ እግር ተጓዡ ኤርሚያስ “ከንጉስ ሚካኤል መዲና ደሴ ልድረስና በባዶ እግሬ መጓዝ አቆማለሁ” ሲል ቃሉን ሰጠው።

*የከሚሴ ከተማ ወጣቶች በከያኒ ሥነ ጊዮርጊስ እና ጓደኞቹ አስተባባሪነት ከከተማው አስተዳደር ጋር በመተባበር በከሚሴ ገዳ አዳራሽ ቅጥር ግቢ ባሰናዱት የምሽት ራት መሰናድኦ ላይ በነበረው ውብ የእሳት ዳር ጨዋታ ደራሲ መስፍን ጌታቸው እንዲህ ሲል ተናገረ “በየአመቱ የሚዘጋጀውን የጉዞ ዓድዋ ግዙፍ እንቅስቃሴ ላለፉት አመታት በትልቅ ትኩረት እንከታተላለን። ሁል ግዜም ኢትዮጵያን ከተጠናወታት የመነጣጠል ደዌ የሚያድን ልዩ መድኃኒት መሆኑን ስለምናምን የበኩላችንን በርቱ ለማለት ነው ዛሬ የዘመን ድራማ አባላትን መልዕክት እና ድጋፍ ይዘን የመጣነው። ሁልግዜም ከጎናችሁ ሆነን ቢያንስ የአንድ ቀን ስንቅ እናቀብላለን። በባዶ እግሩ የሚጓዘው ኤርሚያስ መኮንን ጫማ መጫማት ለተቸገሩ ሰዎች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትርፍ ጫማውን ልገሳ እንዲያደርጉ ያቀረበውን ጥሪም ሰምተናል። አሁን የሱ አላማ እንዲሳካ ከዚህ በኋላ ያለውን ኃላፊነት ወስደን ከግብ የማድረሱን ስራ እንወስዳለን። ስለዚህም ለሰለሞን የገባውን ቃል አክብሮ ቀጣዩን ጉዞ በጫማ እንዲጨርስ እንለምናለን። ካህናት ባንሆንም እንደ ወንድም ከደሴ በኋላ በባዶ እግሩ እንዳይጓዝ እናወግዛለን” በማለት መልዕክቱን አስተላልፏል።

*የተለያዩ ታሪክ ቀመስ መልዕክቶች በተላለፉበት በባህላዉ የቡና ምረቃ ስርዓት የተሟሸው የምሽቱ ስነ-ሥርዓት ላይ ከነ መስፍን ጋር ተጓዦችን ለማበረታታት የተገኙት አሜሪካዊው ታዋቂ ፎቶግራፈርና የኢትዮጵያ የምን ግዜም ወዳጅ አቶ Matt Andrea በዝግጅቱ ላይ መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

*”የዓድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ድል ብቻ አይደልም። የአፍሪካዊያንም ድል ብቻ አይደለም። የእኛ የአሜሪካውያንም ድል ነው። ምክንያቱም አሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ካለፈች በኋላ ጥቁር አሜሪካዊያን ይቆጩበት የነበረውን በሰውነት እኩል መብት የማግኘት ጥያቄ ቅርጽ ይዞ አሸናፊ እንዲሆን የዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያዊያን ወራሪን የማሸነፍ ድል ትልቅ መነሻ ሆኗቸዋል። አሁን አሜሪካ የምትኮራበት ‘ሰው ሁሉ እኩል ነው’ የሚለውን መርኋን የሰጣት የዓድዋ ድል መሆኑን አምናለሁ። ስለዚህም ‘የዓድዋ ድል የሰው ልጆች ሁሉ ድል ነው’ በሚለው መስማማት ይኖርብናል” በማለት መልዕክታቸውን አጋርተዋል። ለጉዞው አጋዥ ይሆን ዘንድም ለቀጣይ ቀን ስንቅ የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።

*በከሚሴ ወጣቶችና በከተማው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት ለተጓዡ ቡድኑ አባላት 6 ሴት ተጓዦች፣ ለጉዞው ዋና አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ፣ ለእንግዳው ፎቶግራፈር፣ ለዘመን ድራማ አባላት እና ለባዶ እግር ተጓዡ ኤርሚያስ መኮንን የከሚሴን ህበረ ቀለም የሚያሳዩ ባህላዊ አልባሳት ስጦታዎች በክብር አበርክተዋል። ኤርሚያስ ደሴ ያጠናቅቃል ተብሎ በሚጠበቀው የባዶ እግር ጉዞ ፍፃሜ በኋላም ስጦታውን የሚረከብ ይሆናል ሲሉ የጉዞው አዘጋጆች ገልፀዋል።

*ቅን ልብ ካላቸውን ከያንያን ጋር በከሚሴ ከተማ ላይ የእግር ጉዞ በማድረጋቸው የተደሰቱት የጉዞ ዓድዋ 6 አባላት በነ ሰለሞን ቦጋለ ምልጃ ጽኑው ኤርሚያስ መኮንን የባዶ እግር ጉዞውን ከደሴ ለማቆም በመወሰኑ ደስታቸው እጥፍ ድርብ ሆኖ አምሽቷል።

*የዛሬዎቹ ኢትዮጵያዊያን በአያቶቻችን የተከፈለልንን ዋጋ በማሰብ ህብረትና ፍቅራችን እንዳይጠፋ፤ የሀገራችንን መንደሮች እያቆራረጡ የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ዓድዋ ተራሮች አናት ለመድረስ የሚገሰግሱት የዘንድሮው ተጓዦች አሁንም እንዲህ ይላሉ፦

#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!
#የምናቋርጣቸው_የሐገራችን_መንደሮች_እንጂ_ድንበሮች_አይደሉም
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!

ሐሙስ ጥር 23 ኮምቦልቻ አርብ ጥር 24 ደሴ እንገናኝ።

LEAVE A REPLY