የታከለ ኡማ ቤት ኪራይና ተያያዥ ጉዳዮች | መሃመድ አሊ መሃመድ

የታከለ ኡማ ቤት ኪራይና ተያያዥ ጉዳዮች | መሃመድ አሊ መሃመድ

ሰሞኑን ይኸን ጉዳይ ሲዘዋወር አይቼው ቀለል አድርጌ አልፌው ነበር፡፡ አሁን ግን የተለያዩ ወገኖች ከግራና ከቀኝ ወጥረው እየያዙት ነው፡፡ በርግጥ የታከለ ኡማ ቤት ኪራይ ዋጋ ብቻውን አነጋጋሪ ነው? ወይስ የሌሎች የፖለቲካ ትኩሳቶች ማሳያ?

ታከለ ኡማ የሚተቹትና የሚከሰሱት በተጋነነ የቤት ኪራይ ዋጋ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አነጋጋሪ ጉዳዮች ነው፡፡ ለአብነትም የአዲስ አበባን የሥነ-ህዝብ ጥንቅርና ሚዛን (demography) በማዛባትም ይታማሉ፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የአዲስ አበባ ነዋሪ ላልሆኑ ወገኖች መታወቂያ በገፍ መታደሉ ይነገራል፡፡ በአንድ የቤት ቁጥር በርካታ መታወቂያዎች መገኘታቸውም በአስረጅነት ይቀርባል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አንደኛ ነገር እነዚህ መታወቂያዎች የታደሉት መቼ ነው? እኔ እስከማውቀው ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ የራሱ ቤት/የይዞታ መብት ለሌለው ሰው (እኔን ጨምሮ) መታወቂያ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም አንዳንድ ቤት ያላቸው ሰዎች ለዘመዶቻቸው፣ ለወዳጆቻቸው፣ አንዳንዶች ደግሞ ገንዘብም ተቀብለው በአንድ ቤት ቁጥር ለብዙ ሰዎች መታወቂያ ማውጣታቸውን አውቃለሁ፡፡ ስለሆነም በአንድ ቤት ቁጥር ብዙ መታወቂያ መቼና እንዴት እንደተሰጠ መጥራት ያለበት ይመስለኛል፡፡

ከዚሁ በተጓዳኝ ኢ/ር ታከለ ኡማ/አስተዳደራቸው አንድን ወገን በማፈናቀል ሌላውን ለመትከል ይሠራል በሚልም ይታማል፡፡ በርግጥ ይህን አድርገው ከሆነ በፖለቲካ ብቻ ሳይሆን በህግም እንዲጠየቁ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ግን በተጫባጭ ማስረጃ ማረጋገጥና ማስረዳት ከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ከ”ተራ አሉባልታ” ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡

የምር መነሳት ያለበት ጥያቄ ግን፣ በርግጥ ኢ/ር ታከለ ኡማ የአዲስ አበባን የሥነ-ህዝብ ጥንቅርና ሚዛን ለማዛባት አቅደውና መዋቅራዊ በሆነ መንገድ (systematically) ይሠራሉ? ወይስ እሳቸው በከንቲባነት በመሾማቸው ብቻ አስተዳደሩ ለአንድ ወገን የሚያደላ ሆነ? አሁን ያለው አስተዳደራዊ መዋቅርና አሠራርስ (the system) ይህን ለማድረግ ዕድል የሚሰጥ ነው ወይ? እነዚህ ጉዳዮች አንገብጋቢና (sensitive) አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆኑ አሉታዊ አንደምታቸውም ያንኑ ያህል ነው፡፡ ስለሆነም ባልተረጋገጠ መረጃ ላይ ተመስርተው የሚሰራጩ ወሬዎች በከተማው አስተዳደር ላይ ግርታን ከመፍጠር አልፈው ከመገፋትና/ከገፊነት ሥነ-ልቦና ከሚመነጭና “እኛና እነሱ” ከሚል የትርክት አዙሪት እንዳንወጣ ሊያደርጉን ይችላሉ የሚል ሥጋት አለኝ፡፡

ወደ ከንቲባው የቤት ኪራይ ዋጋ ጉዳይ ስንመጣም እንዲሁ መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ በግሌ የከንቲባውን የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ በሚመለከት መረጃው የለኝም፡፡ የተባለውን ብር 140,000 ብር ብንቀበል እንኳ መጠየቅ ያለበት የቤቱ ዋጋ ብቻ ሳይሆን የቤቱ ሁኔታስ የከንቲባውን ደረጃ የሚመጥን ነው? ወይስ ቅንጦት የበዛበት ነው? የሚለውንም ጭምር ነው፡፡ ለንፅፅርም ከእሳቸው በፊት የነበሩ ከንቲባዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች ምን ዓይነትና/ደረጃ ያላቸው ነበሩ? የሚለውንም ማዬት ያስፈልጋል፡፡ ታከለ ኡማ ከሳቸው በፊት ከነበሩት ከንቲባዎች በተለዬ ሁኔታ ዋጋው ውድ የሆነ ቤት ተከራይተው በቅንጦት የሚኖሩ ከሆነ መተቸታቸውና መከሰሳቸው አግባብ ነው፡፡

በርግጥም ከአብዛኛው ህዝብ ገቢና የኑሮ ሁኔታ አንፃር የተጠቀሰው የቤት ኪራይ ዋጋ የተጋነነ ሆኖ መታዬቱ አይቀርም። ሆኖም ግን አሁን በከተማችን ከ100,000 – 150,000 የሚከራዩ ቤቶች እንኳን ለከተማው ከንቲባና መካከለኛ ገቢ ላለው ነዋሪም የሚመጥኑ አይመስሉም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከ10,000 ብር በታች ሲከራዩ የነበሩ ቤቶችኮ ዛሬ ላይ ከ100,000 ብር በላይ ነው የሚጠራባቸው፡፡ ይህን ተከትሎ አንዳንድ ሰዎች መሐል ከተማ ላይ የሚገኙ (ባለአንድ ፎቅ) ቪላ ቤቶቻቸውን እስከ 150,000.00 በማከራዬት እነሱ ከከተማው መሐል ወጣ ብለው ቀነስ ባለ ዋጋ ተከራይተው እንደሚኖሩ ይታወቃል፡፡

ከዚህም በመነሳት ከንቲባው ከመሐል ከተማ ወጣ ብለው ቢከራዩ ከሥራቸውና ከደህንነታቸው ጋር በተያያዘ ችግር አይፈጥርባቸውም ወይ? የሚል ጥያቄም ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ አንድ ሰው የሀገር/የመንግሥት መሪ ከሆነ በኋላ “ደሳሳ ጎጆ ውስጥ አድጎ” የሚለው መነሻ አሳማኝ መደምደሚያ ላይ አያደርስም፡፡ ይኸም “ትናት በኩራዝ ሲያጠና የነበረ ሰው የኤሌክትሪክ መብራት ምኑ ነው? መደብ ላይ እየተኛ ላደገ ሰው አልጋ ምኑ ነው? በእግሩ ሲኳትን ያደገ ሰው መኪና ምኑ ነው?” እያልን ልንቀጥል ነው፡፡

ይልቁንስ የመንግሥትን ወጭ ለመቀነስ፣ ቀደም ሲል “የኪራይ ቤቶች አስተዳደር” በሚባለው ተቋም ሥር የነበሩ ቤቶች የት ገቡ? ወይም በነማን ተይዘዋል? ከነዚህ ቤቶች ውስጥ ለከንቲባው ደረጃና ደህንነት የሚመጥኑ ቤቶች የሉም ወይ? ከዚህ በፊት በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ ሰዎች የሥልጣን/አገልግሎት ዘመናቸውን ሲጨርሱ እንዲህ ዓይነት ቤቶችን እንደያዙ ቀሩ ወይ? እንዳውም አንዳንድ ባለሥልጣናት በመንግሥት ቤቶች እየኖሩ እነሱ የገነቧቸውን ዘመናዊ ቪላዎችና ህንፃዎች በውድ ዋጋ እንደሚያከራዩ ይታወቃል፡፡ በዚህ ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድና ግልፅ የሆነ የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ አንፃር ኢ/ር ታከለ ኡማ ትርፍ የመንግሥት ቤቶችን የያዙ ሰዎችን በማስለቀቅ ቤት ለሌላቸው/ለአቅመ-ደካሞች በመስጠትበተጨባጭ የወሰዷቸው እርምጃዎች መኖራቸውን እናውቃለን፡፡ ይሁንና፣ እነዚያ ሊበረታቱ የሚገባቸው እርምጃዎች በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍልና በታችኛው የሥልጣን እርከን አካባቢ ተወስነው የቀሩ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም በዚህ ላይ ግልፅ የሆነ የህግ ማዕቀፍ መቅረፅና የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አለበዚያ ግን እዚህም እዚያም ለሚፈጠሩ አሉባልታዎችና ሀሰተኛ ወሬዎች ክፍተት መፍጠሩና “ውሸት ሲደጋገም እውነት …” መሆኑና የማይናቅ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡

ይኸው ነው!!!

LEAVE A REPLY