ከከሚሴ በኋላ እንዲህ ሆነ:- ደሴ – ጉዞ ዓድዋ 6 | ያሬድ ሹመቴ

ከከሚሴ በኋላ እንዲህ ሆነ:- ደሴ – ጉዞ ዓድዋ 6 | ያሬድ ሹመቴ

“[ደሴና] ኮምቦልቻ ከሚሴና ሐርቡ
የነ ሸግዬ ሐገር የ’ናይጠገቡ”

~ ከአዲስ አበባ ዓድዋ ድረስ በ20 ቀናት ብቻ የሚጠናቀቅ ሩጫ ሊጀመር ነው።
~ “አያቶቻችንን በድለናቸዋል”
~ ገጣሚ ኤፍሬም ስዩምና ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ ግጥሞቻቸውን በአካል ተገኝተው አቅርበዋል

ከከሚሴ በኋላ እንዲህ ሆነ:-

*ሐርቡ
~ በእግራቸው ከሐረር የተነሱት የዘንድሮዎቹ እንቁዎች የድሬ ልጆች ከቤታቸው ከወጡ ጥር 22 ቀን ድፍን አንድ ወር ሞልቷቸዋል። በፀባይና ተግባቢነታቸው የተደነቁት የድሬዳዋ ልጆች የጉዞ ዓድዋ 6 ምርጦች እንደሆኑ ጉዞውን ቀጥለዋል።

~ የሐርቡ ከተማ አስተዳደር ደማቅ አቀባበል በማድረግ የወሎን እንግዳ ተቀባይነት ዳግም አረጋግጧል።

~ የፍንጭቶ ፏፏቴ ላይ አስደሳች ቆይታ ያደረጉት የጉዞ ዓድዋ 6 አባላት ቀደምት አያቶቻችን ላደረጉት ተጋድሎ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር የነበረውን አጋዥነት በማውሳት ተፈጥሮ ከእኛ ወገን መሆኗን መስክረዋል።

*ኮምቦልቻ
~ ታዋቂዋ የፎንተኒና መንደር በንጋት ቀድመው የደረሱት ተጓዦች ከኮምቦልቻ ከተማ አቀባበል ለማድረግ መንገድ የጀመሩት የከተማው ወጣቶችና የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች እስኪደርሱ ድረስ መጠነኛ ረፍት አድርገው ወደ ታሪክ ንባብ ገብተዋል። ግሩም መስተንግዶም ተደርጓል።

176D1A2A-F488-4F45-9343-6411239896B8~ ከደማቁ የኮምቦልቻ ከተማ አቀባበል በኋላ በኮምቦልቻ ከተማ ባህል አዳራሽ ውስጥ በተሰናዳ የተጓዦች አቀባበል ልዩ ኪናዊ ዝግጅት ላይ የከተማው ባህል ቡድን የተለያዩ ጣዕመ ዜማዎችን እና ሙዚቃዊ ድራማ አቅርቧል።

~ ታዋቂው ገጣሚና ባለ ቅኔ ኤፍሬም ስዩምና ገጣሚ ሰለሞን ሳህለ ከአዲስ አበባ ድረስ በመምጣት በመድረኩ ላይ የጥበብ ውጤቶቻቸውን አቅርበዋል። ሁለቱም ገጣሚያን ለጉዞ ዓድዋ 6 አባላት መልካም ጉዞ በመመኘት የግጥም ስራዎቻቸውን ለቡድኑ አባላት በስጦታ አበርክተዋል።

~በጋዜጠኛ ማይክ መቅድም እና በመድረክ አጋፋሪው ሀበሻ የተመራው የእለቱ መሰናድኦ በሁል ግዜ የኮምቦልቻ ከተማ አጋራችን በቢጂአይ ኢትዮጵያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ዋነኛ ደጋፊነት የእራት ግብዣ እና ምቹ መኝታ ተሰናድቶ ተጓዦችን ደስተኛ አድርጓል።

~በግብዣ ሥነስርዓቱ ላይ የጉዞ አጋሮቹን ወክሎ ንግግር ያደረገው ተጓዥ ታሪኩ ዳኜ የሚከተለውን ሐሳብ አካፍሏል። “እኛ የአያቶቻችንን ታሪክ ለመዘከር ጥቂት ሙከራ በማድረጋችን ያገኘነውን ክብር ስናይ፤ ያንን ግዙፍ ታሪክ የሰሩ አያቶቻችንን እስከ አሁን ምን ያህል በድለናቸው እንደኖርን ነው የገባን”

*ደሴ
~የጉዞ ዓድዋ 6 አባላት፤ በኮምቦልቻ ከተማ ወጣቶች (በእግር) አጃቢነት የሐረጎን ጠመዝማዛ መንገድ አልፈው ገና ጄሜ መንደር ብቅ እንዳሉ በፈረሰኞች የተዋቡት የደሴ ጀግኖች፤ አርበኞችና የጉዞ ዓድዋን ምልክት በልብሳቸው ላይ ያተሙ ወጣቶች በርከት ብለው መንደሩን በድል ዜማ አጨናነቁት። በሆታና በእልልታ አጀብ ደሴ ከተማ ድረስ በመዝለቅ ከህዝቡ የተለየ ፍቅርና አክብሮት ያገኙት ተጓዦች አድካሚ ዳገት መውጣታቸውን ዘንግተው በአዲስ ጉልበት የድል ዜማዎችን እያዜሙ ከተማውን በመዞር ለህዝቡ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

~በደሴ ከተማ አባት በንጉስ ሚካኤል ቤተ መንግስት በነበረው የምሽት ኪነጥበባዊ ዝግጅት ላይ የተገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባ ክቡር አቶ መላኩ ሚካኤል ተጓዦችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት “በምትደርሱበት ቦታ ሁሉ የደሴን ህዝብ ሰላምታ አድርሱልን” በማለት አስደሳች ንግግር አቅርበዋል።

3FA7B995-6D64-4032-B5FB-1977DF4234E0~በወጣት መስፍን ሰለሞን እና ጓደኞቹ አስተባባሪነት በሃይኒከን ሶፊ ማልት ደጋፊነት በነ ባለቅኔው መንግስቱ ዘገየ ጃኖ አጃቢነት የደሴ ከተማ ወጣቶች ማብላት ማጠጣታቸው ሳይንስ ይኸው ደግሞ ተጓዦችን ለመሸኘት በእግራቸው እስከ ሐይቅ ከተማ ድረስ ተጉዘዋል።

*አዲስ አበባ
~ የጦማር አድራሽ ዘማቾችን የሚወክል የግስገሳ ጉዞ በ20 ቀናት ውስጥ 1010 ኪ.ሜትሮችን በሩጫ አጠናቆ ዓድዋ ለመድረስ የታቀደ የሩጫ ትዕይንት በይፋ እንደሚካሔድ የጉዞ ዓድዋ አስተባባሪዎች ገልፀዋል።

~ በ20 ቀናት ብቻ ዓድዋ ለመድረስ ሩጫ የሚጀምሩት ከዚህ ቀደም በጉዞ ዓድዋ 3 እና 5 ላይ ጠንካራ ተሳታፊ የነበሩት ተጓዥ ሽመልስ ታደሰ እና በኃይሉ አድማሱ ሲሆኑ ተገቢውን ዝግጅታቸውን አጠናቀው በየ ቀኑ የማራቶን ሩጫ በማድረግ ዓድዋ ድረስ ይዘልቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

~የዓድዋ 1010 ኪ.ሜ ሩጫ ከሳምንት በኋላ ይጀመራል።

#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!!
#የምናቋርጣቸው_የሀገራችንን_መንደሮች_እንጂ_ድንበሮች_አይደለም!!
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!

LEAVE A REPLY