የኢት. ሄራልድ መ/ቤታችን አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት 7ኛ ፎቅ ላይ ነበር። ለቡና ወደ ሰራተኞች ክለብ እንወርድና ካራንቡላ እንጫወታለን። አሪፎች ካራንቡላ ሲጫወቱ ለማየት፣ ሰዉ ግጥም ይልና ቦታዋ ትንሽዋ ስታድዮም ትመስላለች። አንድ ጊዜ ካራንቡላ ስጫወት፣ የማተሚያ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበረው ተወዳጁ አቶ አስፋው ከበደ ይገባል (አስፋው ከበደ የአምባሳደር ካሳ ከበደ ታናሽ ወንድም መሆኑን ልብ ይሏል)። ጎርነን ባለው ድምጹና ፈገግታ ባጀበው ፊት፣ “እነ አብርሃ በላይ ካራንቡላ እየተጫወቱ ሰምተን ነው ለማየት የመጣነው” ብሎ የሁላችንም ትኩረት ይስባል። አስፋው ገብቶ ጨዋታ ሲያይ አይቸው አላውቅም። በመላው ሰራተኛ ግን እንደ አስፋው ከበደ ያለ እጅግ የተወደደና የተከበረ ሥራ-አስኪያጅ አላውቅም። አስፋው ዛሬም ተወልዶ ባደገባት አዲሳባ ይኖራል።
ታድያ እየተጫወትን እያለ፣ የካራንቡላችን ክፍል በር ገርበብ ብሏል። ከክለቡ ራቅ ካለው ካንዱ ጠርዝ የኪሮስ አለማየሁ ዘፈን ራቅ ብሎ ይደመጣል። ከተመልካቾቹ “በሩን እስቲ ክፍቱት፣ የኪሮስ ዘፈን እንስማበት” ይላሉ። ሌላው ደግሞ “ትግርኛ ባልውቅም ኪሮስ ሲዘፍን ግን ይመስጠኛል” ይላል። ይህ እንግዲህ አቶ ወያኔ አዲስ አበባ ሳይገባ፣ ደርግ ስልጣን ላይ እያለ ነው። (በነገራችን ላይ፣ ኪሮስ ወያኔዎች እንደገቡ ነገሩ ቶሎ ገብቶት፣ “አማራ፣ ኦሮሞ – ትግሬ፣ ጉራጌ” እያላችሁ አትከፋፍሉን ብሎ አዲስ ዘፈን አወጣ። ዘረኝነትን የሚያወግዝ፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ነበር። ኪሮስ እነሱን የደፈረ የመጀመሪያ ጀግና አርቲስት ነበር። ወያኔዎች ኪሮስ በህዝብ የነበረው ተወዳጅነት አይተው ሊተክሉት ያቀዱትን የዘር ፖለቲካ እንደሚያበላሽባቸው ግልጽ ነበር። ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ብለው ወድያው በሞት ቀጡት)።
የታሪክ ክር ወደ ኋላ ልመልሰውና በጃንሆይ ጊዜ እንዲህ ሆነላችሁ።
አንድ ፈረንጅ ኢትዮጵያን ሲጎበኝ፣ አንድ ነገር ይታዘባል። አዲስ አበባ በምሽት ከአማርኛ ሌላ ትግርኛ ሲነገር ያስተውላል። ቋንቋው ይወቀው አይወቀው፣ ባስተርጓሚ ይነገረው፣ አይነገረው የማውቀው ነገር የለም። እኔም ደርሸበት ሳይሆን አንጋፋዎቹ አስተማሪዎቻችን እነ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር፣ ከበደ አኒሳ፣ ያዕቆብ ወ/ማርያም፣ ናራያን ኤስዋራን ወዘተ አልፎ አልፎ ሲጫወቱ ከሰማነው ቁምነገሮች ወስደን ነው። እና ፈረንጅ ሆዬም ጉብኝቱ ጨርሶ አንድ ሪፖርት ጽፎ በኢትዮጵያን ሄራልድ ይታተማል። ርእሱም እንዲህ የሚል ነበር፦ “Addis Speaks Tigrinya After Mid Night” (አዲስ አበባ የሌሊት ቋንቋዋ ትግርኛ ነው)።
ያ ሁሉ ታለፈና፣ አቶ ወያኔ ስልጣን ይዞ 27 አመት ሙሉ ጥላቻ ሲዘራ ኖረ። የዘራውን የሚያጭድበት ጊዜም ደረሰ። ጥቂት የህወሃት መሪዎች የትግራይ ሰው በሀገሩ በኢትዮጵያ እንደ ኪሮስ አለማየሁ ተወዶና ተከበሮ እንዳይኖር አረጉት። አዋረዱት። ክብሩን ገፈፉት። የስርቆት እና የጭካኔ ተምሳሌት አረጉት። የትግራይ ሰው ኢትዮጵያዊ ክብሩን እንዳጣ መቅረት የለበትም። ክብሩን ማስመለስ የሚችለው ደግሞ ትግራይ ከኢትዮጵያዊው ወገኑ ጋር ቁሞ፣ በስሙ እየነገዱ ኢትዮጵያን ሲዘርፏት እና ዜጎችዋን ሲያሰቃዩ የኖሩት፣ መቀሌ የመሸጉትን ወንጀለኞች ይዞ ለህግ ካቀረበ በኋላ ነው። ትግራዋይ ቀበቶህን ጠበቅ አርግ! ሌላ አማራጭ መንገድ የለም!
ክብር እና ፍቅር ለኢትዮጵያ ህዝብ!