የክፉ ቀን ወዳጅ-ኢሳት | ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)

የክፉ ቀን ወዳጅ-ኢሳት | ታሪኩ ደሳለኝ (ሚኪ)

ዓለም ተለዋዋጭ ነው። ከልዋጩም ጋር የሚሄደውና የሚመጣው እልፍ ነው። የካቻምናው፣ አምና አልነበረም፤ የአምናው፣ ዘንድሮ የለም። የዘንድሮ…እያለ፣ እያለ ይቀጥላል። ቴክኖሎጂውም (የት ለመድረስ እንደሁ እንጃ) ፍጥነቱ አይጣል ነው።

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ጉልበተኛና ርጉም መንግሥታትን ለመከስከሻነት የተተገበረው ስልትም ተቀይሯል። ብረት-ነካሹ አመጽ፣ በዘናጩ የቀለም አብዮት ተተክቶ ጫካና ነፍጥ ወደ ውስጥ ተብሏል። ለአረብ ስፕሪንግ ፌስቡክና አልጄዚራ የማይተካ ሚና ነበራቸው። ወያኔን እንዲህ እንደ ዛሬው ተረት በማድረጉ ግብግብስ ማን እንደ ኢሳት! ገፀ-ስውሩ ጌታቸው አሰፋ፣ ኢሳትን ለማፈን ያል’ፈሳበት’ ተራራ የለም። እንደው ልፋ ቢለው እንጂ፣ ሕዝብን ከቶም ማሸነፍ አይቻልም-ከሚዲያው ጀርባ ነበርና።

“በኢንስ” መስሪያ ቤት ፊት አውራሪነት ማሰራጫ ጣቢያው ተደጋጋሚ ጊዜያት ጃም ቢደረግም፣ ኢሳት እንደ በረሃው ዘመን ቆንጥር ለቆንጠር ዘሏል (ከአረብ ሳት ወደ ናየል፤ ከፍሪኪዌንሲ ወደ ፍሪኪዌንሲ፣ ከአየር ወደ አየር…)

በርግጥ ዛሬ ጌቾ እድለኛ ነው፣ መብቱ ቢረገጥ፣ እስር ቤት (አይቀርለትም ብዬ ነው) ስቅየት ቢደርስበት የሚጮኽለት ኢሳት አለለት። ኢሳት ውሉም ሆነ ውገናው ከሕዝብ ጋር ነው፤ ይህ ትላንት ያየነው ሀቅ ነው (ለዚህ ደግሞ አንደኛ ምስክር እኔው እራሴ ነኝ፤ በዝዋይ ማጎሪያ በወንድሜ ላይ ይፈጸም የነበረውን የመብት ጥሰት ከኢሳትና ቪኦኤ በላይ የሞገተ ሚዲያ አላታውስም)

በመጨረሻም እንሆኝ የኢሳት ካፒቴኖች ወደምትወዷት አናት አገራችው በሰላም ትገቡ ዘንድ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዤ እመኛለሁ።

የካቲት ዘጠኝማ ማን ይቀራል?! በሚሊንየም አዳራሽ

ጥር 27/2011
አዲስ አበባ

LEAVE A REPLY