~የወልዲያው ጉዞ በፍቅር ተጠልፏል
~ዓድዋን በልባቸው የሚጓዙት ታዳጊዎች
~ተኳሽ አራሽና አጉራሽ የዓደዋ ጀግኖች
ዮናስ በልሁ የድሬ ልጅ ነው። ከጓደኞቹ አመለሸጋው ወንድወሰን ኪዳኔ፤ ከጠቢቡ በኃይሉ ሙሉጌታ እና ከጨዋታ አዋቂው ኪሩቤል ዘርፉ ጋር ከሐረር ተነስተው 44 ጀግና ኢትዮጵያዊያንን አዲስ አበባ ላይ ቀላቅለው በዘንድሮው ጉዞ ዓድዋ 6 በፍቅር እየተመሙ ድፍን አንድ ሺህ ኪ.ሜትሮችን አቆራርጠው ወደ ዓድዋ እየገሰገሱ ነው።
ዮናስ ከፍተኛ የሆነ የእንስሣት ፍቅር ያለው ተጓዥ ነው። ዘንድሮ ከደብረ ብርሐን አንጎለላ በፍቃዷ የተቀላቀለችውን ውሻ የሚንከባከባትም እሱ ነው። “ታሪክ” የሚል ስምም ይጠራታል። የደብረሲናን ቁልቁለት መንገድ በመጓዝ ላይ እያሉ በራሪ መኪና የኋላ ሁለት እግሮቿን እና መቀመጫዋን ገጭቷት ሔደ።
ይህቺ ውሻ በሞትና በህይወት መካከል ስታቃስት በሰውነቱ ሸጉጦ ከመሬት አነሳት። በእንባ ስሜት ሀዘኑን ከመግለጽ በላይ እንደምትድን ያመነውም እሱ ነው። ይቺ ውሻ ደብረ ሲና ከተገጨች በኋላ ተጓዦች ትተዋት መሔድ እንደሌለባቸው በማሳሰብ ከጉዳቷ እስታገግም ይንከባከባት ጀመር። እንደ ታዳጊ ልጅ በጀርባው እያዘለ እንደ አራስ ህፃን በእጆቹ እየታቀፈ ያንቀሳቅሳታል።
“ታሪክ” በርሐማውን የሀገራችንን ክፍል እንደ አምናዋ ወዶ ዘማች ውሻ (ባሻ ቡቺ) ለማቋረጥ ባትታደልም በዮናስ በልሁ እንክብካቤ ግን ዛሬም ከጉዞው አልተለየችም። ጤንነቷም ከእለት እለት እየተመለሰ ነው። ወንዝ ወርደው መታጠብ ሲያምራቸው ታሪክ ከዚህ ፍስሐ አትጎልም – ይዟት ይሄዳልና።
ፊታውራሪ ተክለ ኃዋርያት ተክለማርያም “ኦቶ ባዮግራፊ” በሚለው በመጽሐፋቸው የዓድዋ ድል ባለውለታዎች ደከመኝ የማያውቁት ሴቶች እና እንስሣት መሆናቸውን በማውሳት “ያለነሱ የዓድዋ ድል የማይታሰብ ነው” ሲሉ ለገለፁት ውለታ ይህቺን ውሻ እየተንከባከባት ይገኛል።
“ለእንስሳት ልቡ የሚራራ፤ለሰውም እንዲሁ ነው” እንደሚባለው ሁሉ። ከዘንድሮው ጀግና ተጓዥ ሴቶች መሐል አንዷ የሆነችው ትዕግስት አሸናፊ በህመም ምክንያት ስትሰቃይ አይቶ ኪሎሜትሮችን በሸክም የወሰዳት ዮናስ ነው። በየመንገዱ እንጨት ሰብረው ለመሸከም የከበዳቸውን እናቶች ያለመድከም ሰርክ የሚረዳውም እሱ ነው። በባዶ እግሩ ከመጓዝ ያላቋረጠው መንፈሰ ጽኑው ኤርሚያስ መኮንንንም ተሸክሞ ለመውሰድ የጠየቀው ቢሆንም ኤርሚያስ ግን ከአካሉ በላይ ልቡ ጠንካራ ነውና “አመሰግናለሁ! እኔን ይለፈኝ” ብሎታል።
ይህንን አይነት ድጋፍ ዘውትር ለመስጠት የማይሳሳው፤ ለድካም የማይሸነፈው ዮናስ በልሁ የዓድዋን ድል ለማክበር በየ አመቱ በሚካሔደው ጉዞ ዓድዋ ላይ ከተሳተፉ በሙሉ የሚልቀው ነገር አለ። መርዳት ባህሪው ነው። በመጀመሪያዎቹ የጉዞ ቀናት ብቻ የማይወሰነው አዛኝነቱ፤ ሰው በመርዳት ደስታ የማግኘት ባህሪው አንድ ሺህ ኪ.ሜትሮችን አቆራርጦም ቢሆን አልቀዘቀዘም።
የድሬዳዋ ልጆች በየአመቱ እልፍ ሆነው ሊበዙ ፈረሶችንም በጉዞው ሊያሳትፉ ከጉዞ ዓድዋ አዘጋጆች ጋር እየመከሩ ነው።
ከዮናስ በልሁ ወግ መለስ ስንል፤ ከደሴ በኋላ እስከ ሐይቅ ከተማ ድረስ በእግራቸው ሽኝት ያደረጉት የደሴዎቹ መስፍንና ጓደኞቹ የዘንድሮ ተጓዦችን ጽናትና አድካሚውን መንገድ በእግር ለማቋረጥ ያላቸው ብርታት አድንቀው ከተመለሱ በኋላ የሐይቅ ከተማ አስተዳደር ስንቅ አቅርቦ በመሸኘት ጉዞውን በድጋፍ አሳልጧል።
በየዓመቱ በድምቀት አቀባበል ያደርጉ የነበሩት የአንባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ ሰዎች ዘንድሮ ድምጻቸው የጠፋ ግዜ ምን አዲስ ነገር አለ? ብለን ጠየቅን። “ደጓ እመቤት ወ/ሮ ፀሐይ ብጡል የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት ቦታቸው ላይ የሉም” መልካም ሰው ሁሌም የማታጣው ሀገራችን አቶ እሸቱ እና ወ/ሮ ሚሚ የተባሉ የጢሳ አባ ሊማ አንባሰል ምግብ ቤት ባለቤቶች ራት አሰናድተው ተጓዦችን ተቀብለዋል። እንግዶቻቸውንም በርሃ ከማደር ታድገው ቁጥሩ ብዙ የሆነውን ተጓዥ በቤታቸው በረንዳ ጎዝጉዘው አስተኝተዋል።
የድሬዎቹ የነዮናስ አንድ ሺህኛ ኪሎሜትር ጉዞ የተከበረው በደጋጎቹ የሰሜን ወሎ እንቁዋች የሀብሩ ወረዳ መርሳ አባጌትዬ ልጆች ዘንድ ነበር። በወ/ት ትዕግስት እና አቶ እሸቱ በተባሉ የሐብሩ ወረዳ የመንግስት ባለስጣናት አስተባባሪነት ያልተጠበቀ አቀባበል በመርሳ ከተማ ተደረገ። ያደፈ ገላ ውሀ ተገኘ። ለቆሸሸ ልብስም ማጠቢያ እንዲሁ። የፍቅር ራት ተበላ። ጋባዣቸውን በጉርሻ ሲያጨናንቁ ያመሹት ተጓዦች የሐብሩ ወረዳ ኃልፊዎችን ከልባቸው በማመስገን በተዘጋጀላቸው መኝታ ረፍት አድርገዋል።
በማግስቱ የነበረው የወልዲያ ጉዞ ወልዲያ ከመድረሱ በፊት በፍቅር ተጠለፈ። ጠላፊዎቹ ደግሞ የሲሪንቃ ግብርና ምርምር ተቋም ኃላፊዎች እነ አቶ ገዝኻኝ ጌታቸው ነበሩ። ግቢያችን ሳትገቡ አትሔዱም ብለው አስቸገሩ።
ከደቡብ አፍሪካ በግ ጋር ዝርያቸው የተዳቀሉ ሁለት የሲሪንቃ በጎች እየተንጎማለሉ ብቅ አሉ። መለስተኛ ጥጃ የሚያክሉት በጎች ተባርከው ምሳ እና ራት ሆኑ። ባመረው ቅጥር ግቢያቸው ውስጥም የእውቀት ልውውጥና የዓድዋ ታሪክ ንባብ ባማረ ሁኔታ ተካሂዶ አዳር እዚያው ሆነ። በማግስቱም በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ተደርጎ የዓድዋ ድል ተዘክሯል።
በዘንድሮው ጉዞ ዓድዋ ላይ በስንቅ አቀባይነት ያልተሳተፈ የለም። አቶ አበበ አሰፋ ከአሜሪካ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ ሰራተኞች በአስተባባሪያቸው በአቶ ጌዲዮን አማካኝነት የስንቅ ድጋፍ በማድረግ በርቱ ማለታቸውን ቀጥለዋል። በዘንድሮው ጉዞ፤ የዓድዋ ድል በተኳሹ ብቻ ሳይሆን በአራሹም በአጉራሹም የተገኘ መሆኑን የሚያስመሰክሩ ኢትዮጵያዊያን ተበራክተዋል።
የፊታችን አርብ የጉዞ ዓድዋ 3 ተጓዥ ሽመልስ ታደሰ እና የጉዞ ዓድዋ 5 ተጓዥ በኃይሉ አድማሱ በ20 ቀናት ሩጫ ዓድዋ ለመድረስ ከአዲስ አበባ ይነሳሉ።
ወደ ቀደመ ወጋችን ስንመለስ “ለመሆኑ ለውሻዋ ‘ታሪክ’ የሚል ስም እንዴት አወጣህላት?” የሚል ጥያቄ የተጠየቀው ዮናስ በልሁ እንዲህ ሲል ነበር መልስ የሰጠው። “ለታሪክ ስም ያወጣሁላት እኔ አይደለሁም። ደብረብርሐን ከተማ እንደገባን አንድ የ10 አመት ታዳጊ ውሻዋን እየተከተልኩ ስሔድ እየሮጠ ከኋላዬ ይከተለኛል። በኋላ ቆም ስልለት እንዲህ አለኝ። ‘ለውሻዋ ስም ላወጣላት ፈልጌ ነው። እባካችሁም ታሪክ በሏት’ አለኝ። ከዚያ ቀን ጀምሮ ታሪክ እያልኩ መጥራት ጀመርኩ። አሁን ስሟን ለምዳው ታሪክ ባልኳት ቁጥር ቀና ብላ ታየኛለች። ከህመሟ በፍጥነት እያገገመች በመምጣቷ ስሟን የሚመጥን ታሪክ እንደምትሰራ እርግጠኛ ነኝ። የደብረ ብርሐኑን ታዳጊ ለማስታወስም እስከ ዓድዋ ተራራ ጫፍ ድረስ ታሪክ እያልኩ እጠራታለሁ” ሲል ገልጿል።
ፊታውራሪ ተክለኃዋሪያት ተክለማርያም በልጅነት እድሜያቸው የልዑል ራስ መኮንንን ጦር ተከትለው ዓድዋ መዝመታቸውን በማሰብ የዛሬ ህፃናትም ልባቸው ዓድዋ መዝመቱን ልብ እንላለን።
#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!