ምርጫ ከመካሄዱ በፊት ሕዝቡ መሪውን ራሱ እንዲመርጥ የሚያስችለውን አሠራር (ፕሬዚዳንታዊ መንግስት) ወይም ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርቲው መሪውን እንዲመርጥለት የሚያደርገውን አሠራር (ጠቅላይ ሚኒስቴራዊ መንግስት)፤ ከሁለቱ መንገዶች አንዱን መርጦ ፈቃዱን እንዲያስታውቅ ለሕዝቡ ቀዳሚ የምርጫ ዕድል ይሰጠው ዘንድ ለመሞገት አራት ማስረጃዎች አቀርባለሁ።
1ኛ/ ሕዝቡ አዋቂ ነውና እናውቅልሃለን ከእንግዲህ አይሰራም
እናውቅልሃለን የሚሉ ሊሂቃን አንዴ ንጉስ፥ አንዴ ፕሬዚዳንት፥ አሁን አሁን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር እያሉ መንግስት መሰረቱ። የለውጥ አየር እየነፈሰለት እፎይታን በማጣጣም ላይ ያለውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእሳት ተፈትኖ አዋቂ የሆነ ነውና፥ ዛሬ ላይ ቆመን ቀንበር እንደ በፊቱ ባናሸክመው መልካም ነው። ጊዜውን የሚመጥን አካሄድ በመከተል ሕዝቡ መሪዉን ብቻ ሳይሆን የመንግስቱን ዓይነት /system/ ጭምር እንዲመርጥ ቢደረግ የሚመሰረተው መንግስት የሕዝብ መንግስት ለመሆኑ ዋስትና በመስጠት ያፀናዋል። ሊሂቃን የትኛው እንደሚበጅ በየፊናቸው ጥናታቸውንና አመለካከታቸውን ለሕዝብ በውይይትና በክርክር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ከዚያ ባለፈ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቃት ባገናዘበ ሁኔታ፥ እኛ እናውቅልሃለን ብለው ከመወሰን ተቆጥበው፥ ፍርዱን ለሕዝብ እንዲተው ለሂሊናቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ። ይህን አዋቂና ትልቅ ሕዝብ በማክበር ሕዝቡ ያለው እንዲሆን ውሳኔውን ለሕዝብ ይለቃሉ የሚል እምነት አለኝ።
2ኛ/ ሕገ መንግስቱን ማስታመም
ሕገ መንግስቱ ተዐማኒ እንዲሆን ሕዝብ በመረጠው ሞግዚትነት ይፈተሽ ዘንድ ይገባዋል። ስለዚህ የሕዝብ መንግስት እስኪኖረን ድረስ ወደድንም ጠላንም በዚህ ሕገ መንግስት ታስረናል። ዝም ብለን በዚህ ሕገ መንግስት ደግሞ ወደ ምርጫው እንዳንሄድ የሕዝብ መንግስት ለመመስረት ብቃት አይሰጠንም። ስለዚህ ቢያንስ ቢያንስ ምርጫውን በተመለከተ ሕገ መንግስቱ ይፈታን ዘንድ ማሻሻያ ማድረግ የግድ ነው። ይህን የምርጫ ማሻሻያ ለማድረግ ደግሞ ያለው ፓርላማ አሁንም የሕዝብ ስላልሆነ (በሀቀኛ ምርጫ) ውሳኔ ሊያስተላልፍልን አቅም የለውም። ስለዚህ ሕገ መንግስቱን የማሻሻያ አውድ ሕዝቡ ራሱ እንዲሰጥ የመንግስትን ዓይነት ለመወሰን (ፕሬዚዳንት ወይስ ጠ/ሚኒስቴር) የሚለውን እንዲረዳ ይህን ቀዳሚ ምርጫ ማድረግ የሕዝብን መንግስት ለመውለድ ተዐማኒነት ይሰጣል።
3ኛ/ ሁሉ አቀፍ መግባባት ወሳኝ ነው
ዶ/ር አብይ እንደ ሽግግር መንግስት ለማገልገል አሁን አይችሉም። በአሁን ወቅት ተልዕኳቸው የዲሞክራሲ አዋላጅ መሆን ብቻ ነው። ከአምባገነንነት ወደ ሕዝብ መንግስትነት የሚያሻግረን በመጀመሪያ ምርጫ የሚመሰረተው የሕዝብ መንግስት ነው። የመጀመሪያ የሕዝብ መንግስት ለወደፊቱ መሰረት የሚጥል፥ ሕገ መንግስቱን ሕዝባዊ የሚያደርግ፥ አሻጋሪ መንግስት ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ምርጫ ወደፊት ከምናደርጋቸው ምርጫዎች የተለየና ፈር ቀዳጅ ነው። ስለዚህ ወደዚህ በዓይነቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዋላጅ ወደሆነው ምርጫ ስንሄድ ከሞላ ጎደል ሁሉ አቀፍ መግባባት መኖር አለበት። ለምሳሌ ፕሮፌሰር መራራ ምርጫ እንዳይራዘም ሲሉ፥ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ሊራዘምም ይችላል ሲሉ ይታያሉ። ሁለቱም የተፈተኑ ንፁህ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ ልባቸው ለኢትዮጵያ ደህንነት እንዲሆን በማለት ብቻ ይህንን ተቃራኒ አሳብ ያነሳሉ። ታዲያ ቀዳሚ ምርጫ በሚደረግበት ጊዜ፥ ለዋናው ምርጫ ግብሃት የሚሆን መረጃ /data/ በሁለቱም ጎራ ለተሰለፉ የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ይኖራቸዋል። ቀዳሚ ምርጫ ሲደረግ የምናየሁ ሁኔታ ምርጫውን ለማድረግ መቼ መቻልን እንደምናገኝ ፍንጭ በመስጠት መግባባት ላይ ያደርሰናል።
4ኛ/ እንከን የለሽ ምርጫ የግድ ነው
ከዚህ በፊት እንደጠቀስኩት የመጀመሪያው ምርጫ የተለየ ነው። እንከን የለሽ መሆን ያለበትና ውዝግብ የማያመጣ ፍፁምነትን የተላበሰ ምርጫ ማካሄድ እንዳለብን ለድርድር አይቀርብም። ታዲያ ከዚህ በፊት የተደረጉት ምርጫዎች ውሸት ስለነበሩ የምንማርበት ሆነው አይጠቅሙንም። ቀዳሚ ምርጫ ብናደርግ ግን፥ ለወሳኙ ምርጫ መማሪያና ወደፊት ምርጫም ሲደረግ እንከን የለሽ እንዲሆን ቀደም ተብሎ ማስተካከያ ለማድረግ ዕድል ይሰጣል። ቀዳሚ ምርጫ ማድረጉ ከታለመለት ዓላማ ተጨማሪ ድምፅ የመስጠት ልምድ የምንቀስምበትና ራሳችንን በብቃት ለምርጫ የምናበቃበት አድማስ ያሰፋልናል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ።
ይጎበኛታልም።
Email: Z@myEthiopia.com