እንደ መግቢያ
ለመሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ፣ ምሥረታና ግንባታ አስፈላጊነታቸው የግድ ከሚሉ ሁኔታዎች መካከል አንዱ የዜጎች ንቁና ዘላቂነት ያለው ተሳትፎ ነው ። ይህ ተሳትፎ ከሚገለፅባቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ የመንግሥት ሥልጣንና ሃላፊነት ከዜጎች ነፃና ዴሞክራሲዊ ምርጫ የሚመነጭ መሆኑ ነው። ይህ መሠረታዊ መብት በተራው ዜጎች መርጠው ሥልጣን ላይ ያስቀመጡት መንግሥት ሥልጣኑንና ተግባሩን በአግባቡ አልተወጣም ብለው ባመኑ ጊዜ ከሥልጣን በማውረድ ይበጀል በሚሉት ለመተካት እንዲችሉ መብትና ሥልጣን ያጎናፅፋቸዋል ። በህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ምንጭ (source of power and authority) ህዝብ እንደሆነ ሁሉ ልኡላዊነቱም ( sovereignty ) የህዝብ ነው የሚባለውም ለዚህ ነው ።
አንድ ዓመት ሊሆነው ሁለት ወራት ያህል በቀረው የለውጥ ጅማሮ ሂደት የታዩ እርምጃዎች ወደዚሁ አይነት ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር እንደሚቻል ተስፋን የሚያጭሩ መሆኑ እውነት ነው። የተስፋውን ጭላንጭል ወደታሰበለት ግብ ሊያስደርግ በሚችል መንግድና ሁኔታ ላይ ስለመሆናችን ግን እርግጠኞች አይደለንም። ለዚህ ደግሞ ግልፅ ምክንያት አለው። ለዘመናት የተወሳሰበው ሁለንተናዊ ችግራችን በቀላሉ ሊፈታ እንደማይችል እንዳለ ሆኖ ወንጀለኝነታቸው እረፍት የሚነሳቸውን የፀረ-ለውጥ ወገኖች ሴራ በሰከነ አስተሳሰብ ፣ በሞራል ልእልና እና በተደራጀ የጋራ ትግል ለማስተናገድ አለመቻላችን ከባድና አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለን ነው ። ከሥልጣን ብልግና የሚገኘው ገደብ የለሽ ጥቅማችን ቀረብን የሚሉ ወገኖች ችግር መፍጠራቸው የሚጠበቅ መሆኑን ተረድቶ ተመጣጣኝ ብቻ ሳይሆን የላቀ የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በደምሳሳው ፀረ-ለውጥ ፣ ፀረ-አንድነት ፣ ፀረ- ዴሞክራሲ፣ ሁከት ፈላጊ ፣ ዘራፊ ፣ አረመኔ፣ ወዘተ በሚል የውግዘትና የእርግማን ፖለቲካ ወራትን አስቆጥሮ አመት መድፈን ትክክል አይደለምና ቆም ብሎ እራስን መፈተሽ የግድ ነው። ይኸ ለሁሉም አይነት የእራስ ድክመት (ውድቀት) ሰበብ (execuse) የመደርደር አስቀያሚ የፖለቲካ ልማድ ተገቢው እርምት ካልተደረገበት እያታለለ ጠልፎ የሚጥል መሆኑን ልብ ማለት አዋቂነት ነው ።
በእውነት ከተነጋገርን እንደቀደሙት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ ይኸኛው እንቅስቃሴም የተከፈለበት መስዋእትነት ከባድና መሪር ቢሆንም መከራና ውርደት ባስከተለው የቁጭትና የምሬት ስሜት እንጅ በጠንካራ የጋራ አስተሳሰብ ፣ በሞራልና ድርጅታዊ ልእልና የታገዘ አልነበረም ። አሁንም በዚህ ረገድ ትርጉም ያለው ልዩነት አይታይም ። ቀድሞውንም ለሩብ ክፍለ ዘመን የመከራና የውርደት ቀንበር ተሸክመን የዘለቅነው በባለጌ ገዥዎች ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን ለጋራ ነፃነትና ፍትህ እውን መሆን የሚያበቃ የአስተሳሰብ፣ የሞራልና የመደራጀት ልእልና መፍጠር ባለመቻላችን የመሆኑን እውነት ብዙም የተማርንበት አንመስልም ። የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከኢህአዴ የጥገና ለውጥ (reform) አልፎ ወደ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገር ካለበት ይህን ስፋትና ጥልቀት ያለውን ክፍተት ለመሙላት እልህ አስጨራሽ ጥረት ይጠይቃል ። ምክንያቱ ይህ መሠረታዊ ግብአት ባልተፈጠረበትና ባልተጠናከረበት ሁኔታ እውተኛ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንኳን እውን ሊሆን ሊታሰብም የሚችል ነገር አይደለም። በአስተሳሰብ ፣ በሞራልና በመደራጀት ልእልና ያልተገመደ የለውጥ እንቅስቃሴ ፀረ-ለውጦች ባይገፈትሩት እንኳ በራሱ ይወድቃል።
የራስን ድርሻ (ግዴታ) በሚገባ ሳይወጡ ሁልጊዜና በማነኛውም ጉዳይ ጣትን በሌላው ላይ መቀሰር በምንም አይነት የነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጋ ባህሪ ሊሆን አይገባውም ። መብትን ለማስከበር የሚደረግ ትግል የእየራስን ግዴታ መወጣት ግድ ይላል ። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መብትንና ሥልጣንን ከግዴታ ( ሃላፊነትና ተጠያቂነት) ጋር አጣሞሮ የሚይዝ ስለመሆኑ ከቶ ሊዘነጋ አይገባውም ። የህዝብ ሥልጣንና መብት ከሌለ አምባገነንነት ፣ ግዴታ ከሌለ ደግሞ ሥርዓተ አልበኝነትነውና በሁለቱ መካከል ሊኖር የሚገባውን ሚዛን መጠበቅ የግድ ነው ። የሁለቱን መስተጋብር ሚዛናዊነት በሚያሳጣ ሥርዓተ ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲ ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም ። እናም በሁለቱ መካከል መኖር የሚገባውን ሚዛናዊ ግኑኝነት በአግባቡ ጠብቆ ለማያቋርጥ ማህበረሰባዊ ሰላምና እድገት (ብልፅግና) ለማዋል ይቻል ዘንድ ለዜጎች ሁሉ በእኩልነትና በእኩልነት ብቻ የሚያገለግል የህግ የበላይነት ማስፈን የግድ ነው ። ይህ ደግሞ ያለአስተሳሰብ ፣ ያለሞራልና ያለድርጅታዊ ልእልና ከቶ የሚሆን አይደለም። ስለ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥ ስናስብ መልሰን መላልሰን ማሰብ ያለብን ከዚሁ መሠረታዊ ሁኔታ አንፃር መሆን አለበት ። ከአሁን በፊት የተሞከሩት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴዎቻችን እየከሸፉ የጨካኝ አምባገነን ገዥዎች የመከራና የውርደት ሥርዓተ መንግሥታት ሰለባዎች ሆነን ዘመናት ያስቆጠርንባቸው አይነተኛ ምክንያቶች የሚመነጩት ከዚሁ እጅግ ሥር የሰደደ ጉድለታችን መሆኑን አምኖ በመቀበል ተገቢውን እርምት ማድረግም ትልቅ አዋቂነት ነው ። ይህን ሆነን እና አድርገን ካልተገኘን ከመቃብር አፋፍ በተመለሰው ኢህአዴግ ጥገናዊ ለውጥ አካሄድ (reform) መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ አይቻለንም ።
እንደመግቢያ ይህን ካልኩ ሃሳቤንና አስተያዬቴን ይበልጥ ግልፅ ወደ ማደርግበት ክፍል ልለፍ ። አቀራረቤ እንደ አንድ የአገሩን የፖለቲካ ታሪክ በአግባቡ እንደሚገነዘብ እና ከምንደሰኩረው እፁብ ድንቅ ቃለ-ነቢብ (rhetoric) ባሻገር ያለውን የገሃዱ ዓለም እውነታ በቅንነት ፣ በተስፋና በሥጋት እንደሚከታተል ተራ (ordinary ) ኢትዮጵያዊ እንጅ አንዳንድ ወገኖቼ እንደሚያስቡት ከለውጥ ሃዋርያው ቡድን ጋር ለመደመር ያስችለኛል ወይስ አያስችለኝም ከሚል እሳቤ እንዳልሆነ ግልፅ ይሁንልኝ ። የእይታዬ ትኩረት ለዘመናት ሁለነተናዊ የመከራና የውርደት ህይወት ያካከናነበንን ሥርዓተ ፖለቲካ ተጨማሪ የህይወትና የቁም ስቃይ መስዋእትነት ሳይጠይቀን አስወግደን ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚያስችለን የአስተሳሰብ ፣የሞራልና የመደራጀት ልእልና ግድ ይለናል ለማለት እንጅ ተገቢውን እውቅና እና ድጋፍ ልንሰሰጣቸው የሚገባን አወንታዊና አበረታች ኩነቶች ፈፅሞ የሉም ለማለት እንዳልሆነም ግልፅ ይሁንልኝ ።
የአስተሰብ ልእልና
የአስተሳሰብ ልእልና እንደ ግለሰብ ዜጋም ሆነ እንደ ማህበረሰብ ህልውናን ለማቆየት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ፍትህን ፣ነፃነትን ፣ መቻቻልን (መከባበርን) ፣ ሰላምን ፣ የማያቋርጥ እድገትንና ብልፅግናን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ ሃሳቦችንና የሃሳብ ማስፈፀሚያ ዘዴዎችን (instruments) ተጨንቆና አምጦ የመውለድ እንጅ በየምነታችንና በየፍላጎታችን የምናውጠነጥናቸውን ሃሳቦች በርዕቱ አንደበታችን አግዝፎና ቅርብ የሆነውን የስሜት ክፍላችን ለመግዛት እንዲችሉ አድርጎ የማቅረብ ጉዳይ አይደለም ። ይህ ቢሆንማ በዓለም የፖለቲካ ታሪክና አሁንም ድረስ አንደበታቸው የቅዱሳንን ቃላት የሚተፋ አምባገነን መሪዎችና (ፖለቲከኞች) ብቻ ሳይሆኑ እጅግ ደካማ የአመራር ሰብእና ያላቸው መሪ ( ፖለቲከኛ) ተብየዎችም የአስተሳሰብ ልእልና ባለቤቶች በሆኑ ነበር ።
የአስተሳሰብ ልእልና ውስጠ ህሊና ተጨንቆና አምጦ የሚወልደው መልካም (የተቀደሰ) ሃብት። የሚቆምበት መሠረትም ከቶ የ ማይዋዥቅ ማንነትና መርህ ነው ። የአስተሳሰብ ልእልና የምናስበውን ሃሳብ ምንነት አግዝፎና አሳምሮ የማሳየት ጉዳይ ሳይሆን ለምን? እንዴት? ወደየት ? በማንና ለማን ? መቼ? ከዚያስ? የሚሉ የሂደትንና የውጤትን ምንነትና እንዴትነት ጥያቄዎች ግልፅ እና ግልፅ የማድረግ ፈቃደኝነት፣ ችሎታና አቅም ነው ። የአስተሳሰብ ልእልና ሃሳቦችና የተግባራዊነታቸው ምንነትንና እንዴትነት በነፃነት ተንሸራሽረውና የጋራ ግንዛቤን ፈጥረው ለህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ህሊናዊና ቁሳዊ ሃይል እንዲሆኑ የማስቻል ፈቃደኝነትና ዝግጁነት እንጅ ከላይ ወደታች የሚወርዱ ተአምራዊ ሥጦታዎችን የማቅረብ ጉዳይ አይደለም ። ሊሆንም አይችልም ።
በሚቀጥለው ጥያቄ ወደ እኛው ወቅታዊ ጉዳይ ልለፍ ። ለመሆኑ በደግም ሆነ በክፉ ረጅም የጋራ ታሪክ እንዳለው የአንድ አገር ህዝብ ከዘመን ጋር አብሮ በመዘመን ላይ የሚገኝ የአስተሳሰብ (የአመለካከት) ልእልና ላይ ነው የምንገኘው ?
ይህን ጥያቄ በደምሳሳው አዎን ወይም አይደለም በሚሉ ቃላት መመለስ ግልብ ለሆነው ስሜታችን ካልሆነ በስተቀር ለገሃዱ ዓለም እኛነታችንና ወዴትነታችን የሚመጥን መልስ አይሆንም። ”አዎን ! ” ካልን የምክንያታችን መነሻ ሊሆን የሚችለው “እንኳን የአንድ አገር ህዝብ እንደ ህዝብ ይቅርና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ማህበረሰባዊ መስተጋብር በአወንታዊነት የሚታዩ ኩነቶች ጨርሶ አይኖሩትም ማለት የተፈጥሮንም ሆነ የማህበረሰባዊ የእድገት ህግን አለመረዳት ወይም አለመቀበል ስለሚሆን የእኛም የአስተሳሰብ ወይም የአመለካከት ለውጥ ከዚሁ አኳያ መታየት አለበት” የሚል ነው ሊሆን የሚችለው ። በሌላ አገላለፅ “የትኛውም ማህበረሰባዊ እድገት ፍፁማዊ ሳይሆን አንፃራዊ ስለሆነ በተለይ ካለፉት አሥር ወራት ወዲህ እየተካሄደ ባለው የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴ ሂደት የታዩት አወንታዊ ኩነቶች ከዚሁ እውነታ አንፃር መታየት አለባቸው” የሚለው አጠቃላይ እውነታም ( general truth) ስለሆነ አያወዛግበንም።
ፈታኙ ጉዳይ ግን የራሱ አመጣጥ ፣ ባህሪ ፣ ሂደትና ውጤት ያለውን የእኛነታችንን እውነታ በወኔና በቅንነት ተቀብለን የሚበጀንን ማድረግ ሲሳነን (ሲያቅተን) ነው ። ግልፅና ቀላል በሆኑ የጋራ (አገራዊ) ጉዳዮቻችን ዙሪያ በመከባበርና በመቻቻል ተደማምጠን የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ባልቻልንበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን “ከዘመን ጋር በአስተሳሰብ (በአመለካከት) ልእልና ተራምደናል ወይም እየተራመድን ነው ” የምንል ከሆነ አሁንም በለየለት ድንቁርና ወይም እራሳችንን የማታለል የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እየተንቦጫረቅን ነን ማለት ነው ።
መነሻውንና መዳረሻውን ጠንቅቆ በሚያወቅና በፀና መርህ ላይ ሳይሆን ክስተቶችንና ፖለቲከኞችን እየተከተለ የሚነሳና የሚወድቅ አስተሳሰብ (አመለካከት) እንኳን መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ማድረግ የዛሬን ህይወት ከትናንቱ እና የነገውን ደግሞ ከዛሬው የተሻለ ትርጉም ያለው አያደርገውም ። ለመቀበል ፈለግን ወይም አልፈለግን ይህ የአሁኑ የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴ ሂደት የታጀበው በእንዲህ አይነት የአስተሳሰብ ድባብ ነውና የሚሻለው ሃቁን ተነጋግሮ የሚበጀውን የጋራ መፍትሄ ማበጀት ነው ። እናም ከምንደሰኩረው ዲስኩር በስተጀርባ ከተሸከምነው ልክ የሌለው የአስተሳሰብ (የአመለካከት) ድህነት እራሳችን ነፃ ሳናወጣ ከለውጥ ጅማሬው በቀኝም እንቁም በግራ ወይም እንደመርም እንቀነስ የምናመጣው ትርጉም ያለው ልዩነት አይኖርም ።
ይህ ትውልድ የአምባገነን ገዥዎችን የመከራና የውርደት ቀንበር እድሜ በአስተሳሰብ፣ በሞራል እና በድርጅታዊ ልእልና ማሳጠር እየቻለ ነገር ግን ሆኖና አድርጎ ባለመገኘቱ የከፈለው ግዙፍ የመስዋትነት ዋጋ መሪር ትምህርት ሊሆነው ይገባል ። ከገባበትና እየዘቀጠ ካለበት የጎሳና የመንደር ፖለቲካ ማንነት ባርነት ፣ ከአድርባይነት (መስሎና አስመስሎ ከመኖር) ክፉ ልክፍት ፣ ካልሰከነ (ከስሜት ትኩሳት) ፖለቲካ፣ ከማህበራዊ ሚዲያ የስድብ እሽኮለሌ ፣ ወዘተ እራሱን ነፃ ማውጣት ይኖርበታል ። አዎ! ይህ ትውልድ አሁን ከአለበት ዘመን ጋር እየኖረ ያለው በአካል እንጅ ሙሉ ሰብእናውን ከሚያጎናፅፈው የአስተሳሰብና የአኗኗር ልእልና ጋር አለመሆኑን አውቆ ከዚህ አይነቱ ማንነት ነፃ ለመውጣት የሚያስችለውን የአስተሳሰብ ልእልና መላበስ ይኖርበታል ።
እዚያም እዚህም የሚከሰቱ አስከፊ ችግሮች እንዳሉ ሆነው የዚች ምድር ( የዓለም) ህዝቦች ከዜግነት መለስ ያለውን ግንኙነት (መስተጋብር) ይበልጥ እየተገነዘቡና አንዱ ያለሌላው የተሟላ ህልውና እንደሌለው እየተረዱ በሄዱበት በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊው/ዊቱ ኢትዮጵያዊይውን/ዊቷን በገንዛ አገሩ/ሯ መኖሪያ ሥፍራ ሲያሳጣው/ ስታሳጣት ከማየት የባሰ የአስተሳሰብ ዝቅጠት የት አለ ?
ከዚህ የባሰ የሞራል ውድቀትስ (ቀውስስ) የት አለ?
የሚያስቀድማቸው እጅግ አንገብጋቢ አገራዊ (የጋራ እጣ ፈንታ) ጉዳዮች ከፊት ለፊቱ አፍጥጠውበት ባሉበት ሁኔታ ለአያሌ ዘመናት እንደማነኛውም አገር በአገር አርማነት (መለያነት) ሲውለበለብ የኖረን ባንዲራ አታሳዩኝ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚል ትውልድና የአስተሳሰብ ልእልና በምን ይገናኛሉ ?
ማቅረብ የሚፈልገውን የመብትና ሌላም ጥያቄ የጋራ እጣ ፈንታውን ከሚወስኑ ጉዳዮች ጋር እያመዛዘነ ማቅረብና ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ ለማድረግ ፈቃደኛና ዝግጇ መሆን የተሳነው ትውልድ እንዴት የእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለቤት ለመሆን ይቻለዋል ?
የመከራውና የውርደቱ ዋነኛው ምክንያት ለዜጎቿ ሁሉ የተመቼች ህዝባዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚያስችል የአስተሳሰብ፣ የሞራል፣ የአደረጃጀትና የአብሮነት ልእልና ላይ መቆም እንዳይችል ክፉ ገዥዎች ካስለከፉት ልክፍት ነፃ ለመውጣት ትግል ማድረግን የግድ በሚለው በዚህ ወሳኝ ወቅት የመንደርና የቋንቋ ማንነት “የፖለቲካ ክለቦችን” ማራባቱን የቀጠለ ትውልድ የእርሱው የሆነውን ነገና ከነገ ወዲያን የተሻለ ለማድረግ እንዴት ይቻለዋል ?
ከትክክለኛም ይሁን ከተሳሳተ መነሻ የሚነሱ የታሪክ ውዝግቦችን በእውቀት ፣ በጥበብ፣ በገንቢ ምክንያታዊነት ፣ በሃቅ ፣ አብሮነትን በሚጋብዝና የጋራ የወደፊት እጣ ፈንታውን የተቃና በሚያደርግ አኳኋን ከማስተናገድ ይልቅ ጥያቄ ወይም ቅሬታ አለኝ የሚለውን ወገን የአንድነት ጠላት አርጎ የመቁጠር የአስተሳሰብ ድህነትስ የት ያደርሳል?
በሁለቱ መካከል ቆሞ “እኔ ምን አገባኝ” የሚለው ወገን በበዛበት ማህበረሰብ ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግእንዴት ይቻላል?
ባገኘው የመማር እድል ተጠቅሞ ትውልድ የሚቀርፅ የአስተሳሰብ ልእልና ሊኖረው የሚገባው የህብረተሰብ ክፍል እራሱን ከዚሁ ክፉ ልክፍት ነፃ ለማውጣት ተስኖት በሚልፈሰፈስበት ሁኔታ ውስጥ እውነተኛዋ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንዴት እውን ትሆናለች?
የሃይማኖዊ እምነት መሪዎችና ሰባኪዎች ይህ ትውልድ ፈጣሪ ያደለውን አእምሮ ተጠቅሞ የራሱን በጎ ራእይ ፣ ነፃ አስተሳሰብ እና ገንቢ ተልእኮ እንዲያራምድና አገሩንና እራሱን እንዲታደግ በአርአያነት ለመቆም ባልቻሉበት ማህበረሰብ ውስጥ የተሻለ ነገን እንዴት በቀላሉ እውን ማድረግ ይቻላል?
ትውልድን ከግጭት ከመከላከል ጀምሮ ከግጭት በኋላ ሊኖሩ ለሚችሉ ማህበረሰባዊ እንከኖች ከተፈጥሮና ከህይወቱ ተሞክሮ ባገኘው ያልተበከለ እውቀትና ጥበብ መፍትሄ በመስጠት የሚታወቀው የሽምግልና ባህላችን የፖለቲካ ነፋሱን እየተከተለ በሚነጉድበት በዚህ ዘመን ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት በቀላሉ እውን ይሆናል?
ይህ አባባል ከሟርት ወይም ከጨለምተኝነት ወይም ከተስፋ ቢስነት የሚነሳ ሳይሆን ቀን በቀን እየተናነቀን ያለው መሪር እውነት መገለጫ ወይም ነፀብራቅ ነው ። ለነገሩ ነገራችን ሁሉ እየተበላሸ ያስቸገረን የራሳችን መሪር ሃቅ በደፋርነት ተቀብለን የሚበጀንን ከማድረግ ይልቅ በራሳችን ላይ የአስመሳይነትና የአድርባይነት ካባ የደረብን እለት ነው ። በዚህ የለውጥ ፍለጋ እንቅስቃሴ ወቅትም ይህ አስቀያሚ አስተሳሰባችን (ባህሪያችን) መልኩን ከመቀየር በስተቀር ከምንመኘው መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን አንፃር ትርጉም ያለው ለውጥ የሚታይበት አይመስልም ። አዎ! ይህ ትውልድ ቅድመ አያቶቹና አያቶቹ የነበሩበት ዘመንና ሁኔታ ይጠይቅ የነበረውን በደምና በአጥንት መስዋእትነት ልኡላዊትና ውብ አገር የማቆየትንና የማስረከብን ታላቅ የታሪካ ቅብብሎሽ ተረክቦ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን በማድረግ የተሟላ የዜግነት ነፃነቱን መጎናፀፍ ያልቻለበትን እንቆቅልሽ መፍታት ይኖርበታል ። የእንቆቅልሹ መፍቻም የአስተሳሰብ (የአመለካከት) ልእልና መሆኑን ከምር አምኖ በመቀበልና ከምር የተቀናጀ የጋራ ትግል በማድረግ የተሟላ ነፃነቱን ማረጋገጥ ይኖርበታል ። ይህን ለማድረግ ሌላ ተጨማሪ የመከራና የውርደት ዓመታትን መቁጠር አይኖርበትም ።
ከትናንት ዛሬን የተሻለ የሚያስመስሉ ኩነቶች ስለሰማንና ስለአየን “እንቆቅልሹ እየተፈታ ነው ወይም ተፈቷል” የሚል ቅዠት ውስጥ እንዳንዘፈቅ የሚያስችለን የአስተሳሰብ ልእልና ግድ ይለናል። ይህ የአስተሳሰብ ልእልና በታሪክ ሂደት በበጎም ሆነ በክፉ የሆኑት ኩነቶች ሁሉ ለዚህ ዘመን እኛነታችን ትምህርት እንጅ መነታረኪያ እንዲሆኑ ጨርሶ መፍቀድ እንደሌለብን አዉቀን ወደ ፊት እንድንራመድ ያስችለናልና ከምር ልብ ልንለው ይገባል ። ይህ ካልሆነ ዴሞክራሲን አንደበታችን እንጅ ውስጠ ህሊናችን (አስተሳሰባችን) ጨርሶ አያውቀውም ማለት ነው። አንደበታችን (ዲስኩራችን) ውስጠ ህሊናችንን እንዲደልለው (እንዲያታልለው) ከፈቀድንለት ደግሞ ከተጠናወተን የአስተሳሰብ ድህነት ለመውጣት ከቶ የሚቻለን አይሆንም ። በዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ወቅትም እጅግ ከባድ ከሆኑ ፈተናዎቻችን አንዱ ይኸው ነው ። በተለይ ተምሮ በመገኘት ልሂቅ ነኝ የሚለውና ለፖለቲካው ጨዋታም ቅርብ ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል በዚህ ረገድ ያለበት ድህነት አንገትን ቀና አድርጎ የሚያስኬድ አይደለም ።
በዚህ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እራሳችን ከሰብአዊ ፍጡር በታች ያወረድነው ርሃብን ተዋግተን አለማሸነፋችን መሪር ሃፍረት መሆኑ አልበቃን ብሎ ባገኘነው ገዳይ ቁስ (መሣሪያ) ሁሉ እየተገዳደልን ፣ እያገዳደልን እና የዘር ሃረግ እየመዘዝን ይህ የአንተ/የአንች ክልልና ቀየ አይደለምና ነፍስህን/ሽን ይዘህ/ሽ ውጣ/ጭ እያልን የትና ለምን እንደተወለዱ እንኳ የማያውቁ ህፃናትን ጨምሮ አያሌ ንፁሃን ዜጎችን የሰቆቃ ሰለባዎች ያደረግን እለት ነው ። አዎ! አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ህሊናችንን (አስተሳሰባችንን) ያረከስነው “እንደሰው የሰው ዘር ነን ፥ የራሱ አገር እንዳለው ህዝብ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ነን ፥ እንደ ብሄረሰብ/ ጎሳ ደግሞ የየራሳችን ቋንቋና ይትባህል ያለን ኢትዮጵያውያን ነን የሚለውን ጥልቅና ገንቢ አስተሳሰብ መቀበል የተቸገርን እለት ነው ። በእውነት ከተነጋገርን በእኩይ ገዥዎች ለእኩይ ዓላማቸው በሚመች አኳኋን ተከልሎ የተሰጠውን “የክልል ሉአላዊነት” ያሳነሰበት እየመሰለው ኢትዮጵያን እንደ አገር በስሟ መጥራት እንዲቸገር (እንዲፀየፍ) የተደረገ የዚህ ትውልድ አባል ቁጥር የሚናቅ ባልሆነበት ሁኔታ ውስጥ የአስተሳሰብ ልእልናን የሚጠይቀውን ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እንዴት እውን ማድረግ ይቻላል ?
ይህ የአስተሳሰብ ድህነት የበሰበሰውና የከረፋው የኢህዴግ/ህወሃት ሥርዓት እንደ ሥርዓት ባልተወገደበት ፖለቲካዊ እውነታ ውስጥ ቢሆንም የነፃነትና የፍትህ ትግሉን በመሪነት የተቀላቀሉትንም ያባልጋል እንጅ ሃላፊነታቸውንና ተጠያቂነታቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አያደርጋቸውም ። አዲስና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ በአርበኝነት መንፈስ እንዲዘልቁ ከተፈለገ የሚበጀው ነገር ሃቁን በግልፅና በቀጥታ መነጋገሩ ነው ። በዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ወቅትም እንኳን የጋራ ግንዛቤንና አስተሳሰብን አዳብረን ለጋራ ስኬታማነታችን እውን መሆን በአብሮነት ልንቆም በመከባበርና በመቻቻል መንፈስ ለመደማመጥና ለመማማር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር አልቻልንም።
በእውነት ስለእውነት እየተነጋገርን ከሆነ ከዛሬ አሥር ወራት በፊት ጀምሮ እየታዩ ያሉ አበረታች እርምጃዎች መኖራቸው እውነት ቢሆንም የበሰበሰዉንና የከረፋውን የኢህአዴግን ሥርዓተ ፖለቲካ እንደ ሥርዓት አስወግዶ ወደ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ የሚያሸጋግር አካሄድ ግን እያየን አይደለም ። እጅግ በጣት ከሚቆጠሩ ምሁራንና ፖለቲከኞች በስተቀር የአብዛኞቻችን የፖለቲካ ጨዋታ የሚሽከረከረው በጣት የሚቆጠሩ ፖለቲከኞችን (መሪዎችን) በዘወትር ፀሎት የክርስቶስን ስም የምንጠራውን ያህል እየደጋገምን በመጥራት “እናንተ የሌላችሁ እለት እንኳን የለውጥ ሂደት የአንድ አገር ህዝብነት ህልውናችንም ያልቅለታል” በሚል እጅግ የወረደ አስተሳሰብ ዙሪያ ነው ። ወደ ተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር የሚደረገውን እንቅስቃሴ በውዴታ ግዴታ ለተቀላቀሉ መሪዎች ደህንነት ማሰብና ለስኬታማነታቸውም ሄሳዊ ድጋፍ መስጠት ክርክር የሚያስነሳ መሆን የለበትም ። ክርክር ከማስነሳት አልፎ እንደ ትውልድ እራስን ዝቅ የሚያስደርገው የፖለቲካ አስተሳሰብ ግን መንበሩ ላይ ያለ መሪ እክል ቢገጥመው ወይም በራሱ ምክንያት ከጨዋታ ውጭ ቢሆን “እኛ እንችላለን (we can do it!)” የሚሉ ዜጎችን ለማዘጋጀት አለመቻል ነው ።
መሪዎችም (በተለይ ጠቅላይ ሚኔስትሩ) የዚህን “መተኪያ የለሽነት (indespensiblity)” የፖለቲካ ሰብእናን ወይ በቅንነት ልብ አላሉትም ፣ ወይም ወኔና እውቀቱ ያለው አማካሪ የላቸውም ፣ያለዚያም ወደውታል ማለት ነው ። ይህ ባይሆን ኖሮ ከተራ ስልጠና ጀምሮ በአጠቃላይ የፖለቲካና የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የማስገንዘቢያ መድረኮች ላይ ቢያንስ የካቢኔ አባሎቻቸውን እና እውቀትና ተሞክሮ ያላቸውና በህዝብ ዘንድም አወንታዊ ተቀባይነት ያላቸውን ዜጎች ጉልህ ተሳትፎ ማየት እንችል ነበር ። ግን አላየንም ። እያየንም አይደለም ። በእውነት ስለእውነት እንነጋገር ካልን አገር በጣት ከሚቆጠሩ መሪዎችና ፖለቲከኞች ውጭ ችሎታን ፣ እውቀትንና ተሞክሮን አገርን ከማዳን የአርበኝነት ወኔ ጋር አጣምረው የያዙ ዜጎች መናጤ ደህና የሆነች ይመስላል ቢባል ማጋነን የሚሆን አይመስለኝም ።
ለረጅም ጊዜ ከመሪ ተብየዎች ስለአገሩም ሆነ ስለራሱ በጎ ቃላትን እንኳ ሳይሰማ በመኖሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አንደበት የሚወጡትን ቃላት “ከሰው ሳይሆን ከሰማይ መላእክት ከአንዱ የሚወጡ ናቸው” እስከማለት የከጀለው የአገሬ ህዝብ የሌላ ሰው (ባለስልጣን ወይም ባለሙያ) አንደበት አልጥመው በማለቱ “ያን ሰው ካላመጣችሁልኝ አልሰማም” ቢል ምን ያስገርማል? ስህተቱስ የፖለቲከኞች በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትሩ እንጅ የማን ሊሆን ይችላል ? ይህ አይነቱ ልማድ እያደረና እየዋለ ሲሄድ ደግሞ በማነኛውም አስፈላጊ በሆነ ጊዜና ሁኔታ ወደ ላይም ሆነ ወደጎን (vertically and horizontally) ክፍተትን የሚሸፍኑ ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን መሸከም የሚችሉ ፖለቲከኞችን (መሪዎችን) ለማፍራት ጨርሶ አይመችም ።አዎ! የዚህ አይነቱ አስተሳሰብ አሉታዊ ተፅዕኖ ከዚህም የዘለለና ምናልባትም የባሰ የመሆን እድሉ የሰፋ ነው ። እራሳችን ከማታለል አልፈን ህዝብንም እናታለው ካላልን በስተቀር አብዛኛው የአገሬ ህዝብ የለውጡን አወንታዊነት የሚያየው ከነበረበት ሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ህይወት በአንፃራዊነት እፎይ እንዲል ከረዱት ፖለቲከኞች (መሪዎች) አኳያ እንጅ የበሰበሰውና የከረፋው የኢህአዴግ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ተወግዶ መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን አለበት ከሚል ደረጃ አይደለም ። ወደዚህ ደረጃ ለመምጣት ጊዜ የሚፈልግ ቢሆንም ከአሁኑ ከምር ካልጀመርነው ጊዜ ጠብቆ በአንዳች ተአምር ነገር የሚወለድ አይደለም ።
ይህ አይነቱ የአስተሳሰብ (የአመለካከት) ድህነት የገዥዎችን የድንቁርና አገዛዝ ቀንበር ተሸክሞ ከኖረው ከተራው (ordinary) የአገሬ ሰው አልፎ ልሂቅ ነኝ በሚለው የህብረተሰብ ክፍልም በሰፊው የምናስተውለው ፈተና ነው ። ከወደ አገር ቤት ምርጫ ተብየው በወቅቱ ይካሄድ ወይስ ይተላለፍ? በሚል የጠረጴዛ ዙሪያ በተደረገ አንድ ውይይት ላይ አንቱ ከሚባሉት ምሁራን አንዱ “መተላለፍ የለበትም” ለሚለው ማሳመኛ ብለው ያቀረቡት ምክንት ጨርሶ ልፍስፍስ ነበር ። አሁን ያለንበት እጅግ ውስብስብና በቅጡ መልክ ለማስያዝ ያልቻልነውን መሪር እውነታ ከግምት ውስጥ ያለማስገባታቸው እንዴትነት እንዳለ ሆኖ በአማራ ክልል በተደጋጋሚ ሲዘዋወሩ ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እንደሚወድ እና በምርጫም እርሳቸውን እንደሚመርጥ በእርግጠኝነት ሲናገሩ በአንክሮ አዳመጥኩ ። አካፋን አካፋ ማለት ትክክል ነውና እንዲህ አይነቱ በሥርዓት ለውጥ ላይ ሳይሆን በግለሰብ መሪዎች ላይ የተንጠለጠለና ደምሳሳ የምሥክርነት ድምዳሜ በተለይ ከምሁራን ሲመጣ ትክክል አለመሆን ብቻ ሳይሆን በእጅጉ አሳሳችም ነው ። የጥሩ ምሁርነት ባህሪ ይዘትም የለውም ።
ከተወሰኑ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ ከተዘፈቁበት የህወሃት/ኢህአዴን የክፉ አገዛዝ ሰንሰለት በአንፃራዊነት ባልተጠበቀ ወኔ እራሳቸውን ነፃ በማድረግ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴውን በመሪነት ተቀላቅለው ባሳዩት አንፃራዊ በጎ እርምጃ ህዝብ ይወዳቸዋል የሚለውን ጥያቄ ውስጥ ማስገባት አልፈልግም ። ትክክልም አይሆንምና። ከዚህ ባሻገር ባሉ የሥርዓት ለውጥ ጉዳዮች ዙሪያ ግን ጥያቄ ማንሳት በእጅጉ ተገቢ ነው ። እንደ እኔ አረዳድና እምነት የበሰበሰውና የከረፋው የኢህአዴግ ሥርዓት እንደ ሥርዓት ተወግዶ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በማይረጋገጥበት የፖለቲካ ድባብ ሥር ጠቅላይ ሚኔስትሩና በጣት የምንቆጥራቸው የእንቅስቃሴው ባልደረቦቻቸው ስለሚመረጡ ምርጫው መተላለፍ የለበትም ፧ ከተላለፈ አለመረጋጋት ያስከትላል የሚለው ትርክት ልፍስፍስ ነው ። በአንድ በኩል ፍትህን በፈሩና ጠቅማችን ተጓደለ በሚሉ የኢህአዴግ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች የሚቀነባበረውና የሚፈፀመው እጅግ አስከፊ ድርጊት አገርን በሚያተራምስበት ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ለዚህ አስቀድሞም ሆነ ቀውሱ ከተከሰተ በኋላ አጥጋቢ ነው በሚያሰኝ ደረጃ እርምጃ ለመውሰድ ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ቢካሄድ መረጋጋት ያመጣል የሚለውን ክርክር ለመረዳት በእጅጉ ያስቸግራል። ምሁራን እና የአገሪቱን ፖለቲካ ጠንቅቀን እናውቃለን ከሚሉ ሲመጣ ደግሞ የባሰ ግራ ያጋባል ።
ታዲያ በዚህ አኳኋናችን ፖለቲከኞቻች (መሪዎች) ከመቃብር አፋፍ የተመለሰው ኢህአዴግ እንደ ሥርዓት በቀጠለበት እውነታ ውስጥ የጥልቅ ተሃድሶን ( reform) “ትሩፋት ” እየተረኩ የትግሉ ኢላማ ከሆነው መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና መሥረታ ወዲህ ማዶ እንደማያስቀሩን እንዴት እርግጠኞች መሆን ይቻለናል ? በፖለቲካ ሥርዓቷ አዲስና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ከምር የምንሻ ከሆነ በዚህ ረገድ ያለብንን ልፍስፍስ አስተሳሰብ (አመለካከት) በደፋርነት ተቀብለን ወደ ፊት መራመድ ግድ ይለናል ። ከስሙ ጀምሮ እስከተግባሩ የበሰበሰውና የከረፋው ኢህአዴግ “በቆራጥነት ጀምሬዋለሁና ተከተሉኝ” እያለ በሚመፃደቅበት ጥገናዊ ለውጥ (reform) አማካኝነት እንደ ሥርዓት ሊቀጥል አይገባውም ብሎ ለመከራከር መሽከረመም የአስተሳሰብ ልእልና (ልሂቅነት) ሳይሆን ወይ የለየለት ድንቁርና ነው ወይም ደግሞ የለየለት የአድርባይነት ክፉ ልክፍት ነው ።
ተምሮ በማስተማር ወይም አውቆ በማሳወቅ ታሪክ ሠሪ ትውልድ መቅረፅ የሚጠበቅበት የህብረተሰብ ክፍል መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚያስችል የአስተሳሰብ (የአመለካከት) ልእልና ድህነት ሰለባ በሆነበት አገር እንዴት የአስተሳሰብ ልእልናን መጠበቅ ይቻላል ? አስተሳሰቡን ከዘመን ጋር የሚያዘምንበት መሠረታዊ የእውቀትና የማቴሪያል አቅም የማግኘት እድል እንዲኖረው የሚያደርግ ሁኔታ ፈፅሞ ተመቻችቶለት የማያውቀው አብዛኛው የአገሬ ህዝብ በመስዋትነት ያመጣውን የለውጥ ጅማሮ ፖለቲከኞች (መሪዎችን ጨምሮ) “ሽግግር ማለት የተያያዝነው ጥልቅ ተድሃሶዋዊ ክንውን ነው ሲሉት”አሜን ብሎ ቢቀበል ቢያሳዝን እንጅ ምን ያስገርማል? በፅዕኑ ዓላማና መርህ ላይ ለመቆም የሚያስችል አስተሳሰብን (አመለካከትን) ከዘመን ጋር ማዘመን የማይችል ማህበረሰብ እንኳን የዴሞክራሲ ሥርዓት ባለቤት ሊሆን እንደ ማህበረሰብ ህልውናውን ለማስቀጠል በእጅጉ ይቸገራል ። እናም ለህዝብ እውነቱ እየነገሩ ያለበትን ጉድለት አውቆ ተገቢውን ጥረት እንዲያደርግ ከማገዝ ይልቅ በአስተሳሰብ ነቅተን እንዳነቃነው ፧ በሞራል ተገንብተን አርአያ እንደሆነው እና ብሎም የለውጥ ጅማሮውን በማያስቀለብስ አኳኋን እንዲያስኬደነው (እንዳደራጀነው) መንገር (መስበክ) ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው ።
የሞራሉ ጉዳይስ ?
የሞራል ሰብእና ፅንሰ ሃሳብ ብቻ ሳይሆን የገሃዱ ዓለም የጤናማ ማህበረሰብ እሴት (value) መሆኑን ጤናማና ቅን አስተሳሰብ ያለው ዜጋ ከእለት ተዕለት ማህበራዊ መስተጋብር የሚገነዘበው ስለሆነ ብዙም የምለው የለኝም ።በአጭሩ ግን የሚከተለውን ልበል።
በቀላል አገላለፅ ሞራላዊ ሰብእና (moral quality/character) ስንል በጎውንና ክፉውን ወይም ትክክል የሆነውንና ትክክል ያልሆነውን ለይቶ በማወቅ ክፉውንና ትክክል ያልሆነውን ተፀይፎ በጎና ትክክል የሆነውን የመከተልና የማድረግ ሰብአዊ ባህሪ ማለታችን ነው ። የሞራል ግዴታ (moral obligation) ስንልም ሰው ሠራሽ ህግን ጨምሮ በውጫዊ አካል አስገዳጅነት ሳይሆን በእኛው በራሳችን ውስጠ ህሊና አስገዳጅነት (ዳኝነት) ክፉውን ወይም ትክክል ያልሆነው ያለማድረግ (የመቃወም) እና በጎ ወይም ትክክለኛ ሆነውን የማድረግ (የመቀበል) የውዴታ ግዴታ ማለታችን ነው ።
የሞራል ልእልና አንዳች ተአምራዊ ነገር ሳይሆን ውስጠ ህሊናችንን ምክንያታዊነትን ፣ ገንቢነትን ፣ ሃቀኝነትን ፣ መተማመንን ፣ መቻቻልን ፣ መከባበርን ፣ አብሮነትን ፣ እኩልነትን ፣ ነፃነትን ፣ ፍትህን፣ ሰላምን ፣ ፍቅርንና የጋራ ብልፅግናን መነሻና መዳረሻ ላደረገ ሰብእና ክፍት የማድረግ ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ነው ።
እናም ውሸት (ሃሰት)፣ አጭበርባሪነት፣ አለመታመን ፣ ጥላቻ፣ መናቆርና መገዳደል ፣ ቂም በቀለኝነት ፣ ኢሰባዊነት፣ ሌብነት፣ ርህራሄ አልባነት ፧ አለመከባበር፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባይነት ፣ ወዘተ እጅግ ከፍተኛ ችግር በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ማድረግ በእጅጉ ከባድ ነው ። ከክብደትም አልፎ የማይቻል ሊሆንም ይቸላል ።
መሪሩን ሃቅ ለመቀበል ቢቸግረንም በዚህ የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ እንቅስቃሴ ወቅትም አበረታችና ተስፋ ሰጭ ሁኔታዎች የመኖራቸው ጉዳይ እውነት ቢሆንም የምናስተውላቸው አስቀያሚና አስከፊ ኩነቶች ግን ግዙፍና ውስብስብ ፈተናዎቻችን ናቸው ። የሞራላዊ ሰብእናችን አድማስና ጥልቀት በእጅጉ ደካማ ነው ።በዚህ ረገድ ያለብን ድህነት ከዓለማዊ እስከ መንፈሳዊ ተቋሞቻችን ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት ያለውን የህብረተሰብ አካላችን ፥ ልዩ ልዩ የሙያና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላትን ወዘተ ያዳረሰ የመሆኑ ጉዳይ ከዚህ ለመውጣት የምናደርገውን (የምንሞክረውን) ጥረት በእጅጉ አክብዶታል (ያከብደዋል)።
ከሁሉም በባሰ ደግሞ በብሄረሰብ (በጎሳ) ማንነት ላይ የተመሠረተው የእብደት ፖለቲካችን ሞራላዊ ሰብእናችንን (ሰብአዊ ፍጡሮች መሆናችንን) እየተፈታተነና የቁም ሙቶች እያደረገን ይኸውና አሁንም የቀን ተቀን የመርዶ ዜና ያሰማናል ። እኛም ተቆጥተን ከዚህ አዘቅት የሚያወጣንን የጋራ ጥረት ከማድረግ ይልቅ የሰቆቃ ወሬ (ዜና) እየሰማን ከንፈር ከመምጠት ብዙም አላለፍንም። የሰማዩንም ሆነ የምድሩን የሞራል አስተምህሮና ምሳሌነት የተሸከሙት የሃይማኖታዊ እምነት መሪዎችና ሰባኪዎችም ብዙም የተሳካላቸው አይደሉም ። የህዝብ ለህዝብ ጠላትነት አለመሆኑ እየታወቀ ፖለቲከኞቻችን (መሪዎችን ጨምሮ) “የህዝብ ችግር ሳይሆን በአንዳንድ በዚህ ሴራ የተሠማሩ እኩያን ምክንያት የተከሰተ ውድመት ነው”ሲሉን እሱን መልሰን እንደበቀቀን እናስተጋባለን ። ለማነኛውም ፈተናው የከበደውን ያህል ይክበድ እንደ አንድ አገር ህዝብ ተከባብረንና ተከብረን የምንኖርበትን የፖለቲካ ሥርዓት እውን ከማድረግ ውጭ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ የለም። ለዚህ ነው ለነፃነት፣ለፍትህና ለእኩልነት ብሎም ለጋራ ብልፅግና የሞራል ልእልና የግድ የሚሆነው ።
የመደራጀቱ ፋይዳስ?
የህብረተሰብ የእድገት ታሪክ እንደሚነግረን የሰው ልጅ ከሌሎች እንስሳት ተለይቶ አሁን ካለበት የሥልጣኔ ደረጃ ለመድረስ ካስቻሉት ሁኔታዎች መካከል ዋነኛው በተናጠልና በዘፈቀደ አካሄድ እንኳን ህይወቱን የተሻለ ለማድረግ ህልውናውንም ለማስቀጠል እንደማይቻለው አውቆ ይበልጥ ለመቀራረብና ለመረዳዳት መቻሉን ነው ። ቤተሰብን እንደ መሠረታዊ ማህበረሰባዊ ድርጅት እና የሥራ ክፍፍልን ደግሞ እንደ አንድ የህብረተሰብ የሥራ ሃላፊነት አደረጃጀት የጀመረበት ታሪክ የሚነግረንን ቁም ነገር ልብ ካልነው ከሚሊዮን ዓመታት በኋላና በዚህ ክፍለ ዘመን ምን እየሆን እና ምን እያደረግን ነው ብለን እራሳችን ለመጠየቅ ይረዳናል ። እንደ አንድ ህዝብና በአጠቃላይ እንደ ሰው ጤናማ ለሆነ ሁለንተናዊ እድገታችን ይበጃል የምንለውን ሃሳብ ወይም አስተሳሰብ መልክ አስይዘንና ወደ ድርጅታዊ ሃይል ለውጠን የምንፍልገው (የምንመኘው) የነፃነት፣ የፍትህ ፣ የእኩልነትና የጋራ ብልፅግና የተረጋገጠበትን ሥርዓት እውን ማድረግ ለምንና እንዴት ተሳነን ብለን እራሳችን መጠየቅና ትክክለኛውን መልስ መፈለግ ይኖርብናል ።
በተስፋና በከፍተኛ ሥጋት ከተወጠረ አውደ ፖለቲካ ያለተጨማሪ መስዋእትነት መውጣት ወይም ከነበርንበት በባሰ ወደ ኋላ መንሸራተት ከሌለብን የአስተሳሰብና የሞራል እሴቶቻችን ወደ ተደራጀ የለውጥ ሃይልነት ማሸጋገርን ግድ ይለናል ።
የአምባገነን ገዥ ቡድኖቸን አፈና ፣ የቁም ስቃይና ግድያ ለመታገስ የማይችልበት ደረጃ ላይ የደረሰው ወጣት ትውልድ በጨካኞች ጥይት መሞት ብቻ ሳይሆን በቁም እየሞቱ ኖርኩ ከማለት አንድ ቀን እውን ለሚሆን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት መስዋት መሆኑን መርጦ ባካሄደው ትግል አሁኑ የምናየው የለውጥ ጅማሮና ተስፋ እውን ሆኗል ። በወቅቱ ኬሮ ፣ ፋኖ ፣ ዘርማ ፣ ወዘተ በሚል የእንቅስቃሴ ማስተባበሪያ ስያሜዎችን ተጠቅሟል ። በወቅቱ ለነበረው እንቅቃሴ ማስተባበሪያነት የነበረውን አወንታዊ ሚና አሁን ካለው አወንታዊ ኩነት መረዳት አያስቸግርም ። በህወሃት የበላይነት ይካሄድ የነበረውን አስከፊ ሁለንተናዊ አፈና እና ሰቆቃ ህወሃትን ሃይል በማሳጣት አንፃራዊ እፎይታ ከማስገኘት አንፃር የነበረውን ሚናም ማስተባበል አይቻልም ።
የትግሉ አይነተኛ መነሻና መዳረሻ ግን ህወሃትን ሃይሉን አሳጥቶ በጥገናዊ ለውጥ “ትሩፋት” እፎይታ ማግኘት ሳይሆን መሠረታዊ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሆነባትና ለዜጎቿ ሁሉ ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው ።ከዚህ አንፃር ከላይ በጠቀስኳቸው ስያሜዎች ይጠሩ የነበሩት የወጣቶች እንቅስቃሴዎች ከትክክለኛው የአደረጃጀት ባህሪና መርህ አንፃር ሲታዩ ጉድለታቸው ቅርፅ አልባ (amorphous ) ከመሆን ይጀምራል ። በይዘት ደረጃ ደግሞ በጋራ ግንዛቤና መግባባት ላይ የተመሠረተ የጋራ ራእይ ያልተገመዱ ፣ በጋራ መርህና ህገ-ደንብ ያልተሳሰሩ ፣ በጋራ ዲስፕሊን ያልታረቁ፣ ከየመንደሩ /ከየአካባቢው ውጭ (በአገር አቀፍ ደረጃ) መሬት ላይ ያልወረዱ ፣ እና ወደ የብሄረሰቡ (ወደ የጎሳው) የፖለቲካ ማንነት እየተመለሱ የመፍትሄ አካል ከመሆን ይልቅ የችግር አካል እየሆኑ የመምጣታቸውን አዝማሚያ ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም ። ይህ አይነቱ የፖለቲካ አደረጃጀት ባህሪና አካሄድ ደግሞ እውን እንዲሆን ለምንፈልገው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጨርሶ አይመጥንም ። በሌላ አባባል ከአስተሳሰብ ልእልና ድህነት የሚቀዳ አካሄድ ድርጅታዊ ልእልና እንዲኖረው መጠበቅ አይቻልም ።
ይህ ትውልድ የነገን ብሩህ ተስፋ እውን ማድረግ ካለበት ከትንንሿ የየእራሱ ዓለም ፣ ከስሜታዊነት ትኩሳት ፣ ከጊዚያዊ እፎይታ ቅዠት፣ የራስን ሃላፊነት ሳይወጡ በሌላው ላይ የእርግማንና የውግዘት ናዳ ከማውረድ ፣ አወንታዊና አሉታዊ ክስተቶችን እየተከተሉ ከመዋዠቅ ክፉ ልማድ መውጣት ግድ ይለዋል ። ከዚህ ለመውጣት ደግሞ አንድም ከመንደር (ከጎሳ ማንነቱ) ባሻገር ከሁሉም የአገሩ ልጆች (ኢትዮጵያዊያን) ጋር በሚያስተሳስረው አኳኋን በራሱ አነሳሽነት የራሱ የፖለቲካ ድርጅት መሥርቶ ፣ ወይም ደግሞ ዜጎቿ በእኩለነት የሚኖሩባትን ኢትዮጵያ ዓላማ አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ተቀላቅሎ መታገል ይኖርበታል ። ከዚህ ውጭ ያለው ምርጫ ሆድ በባሰው (ኑሮ በመረረው ቁጥር) በአገኘው አጋጣሚና ሥፍራ ሁሉ የምሬትና የተስፋ ቢስነት አቤቱታውን ለመሪዎች የማሰማቱ ( ከሰሙት) ደካማ ልማድ ብቻ ሳይሆን የተሸናፊነት ጩኸቱን መቀጠል ነው ። ይህ ደግሞ አንዴ ብቻ ሳይሆን መላልሶ በቁም መሞት ነው ።
ከሰሞኑ ከመንግሥት (ከኢህአዴግ) ጋር ለመነጋገር በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ ከመቶ በላይ ፖርቲ ነን የሚሉ ስብስቦች የመገኘታቸውን ጉዳይ ከዜናነቱ አልፎ በጥሞና ለሚታዘብ ቅን ኢትዮጵያዊ የአስተሳሰባችን ድህነት ያስከተለው የአደረጃጀት ዝቅጠት ምን ያህል ግዝፈትና ጥልቀት ያለው መሆኑን ለመረዳት የሚችገር አይመስለኝም ። ኢህአዴግም “ሰብሰብ ሰብሰብ በሉና ለምርጫው ተዘጋጁ፥ ብትሸነፉ ወይም ብንሸነፍ ተጨባብጠን ሥልጣን እንረካከባለን” በማለት ይሳለቅባቸዋል ።
በአንፃራዊነት የተሻለ አገራዊ ራእይና የፖለቲካ አጀንዳ አላቸው የሚባሉትም ከእነሱ ድክመት ብቻ ሳይሆን እንደዜጋ በገንዛ አገራቸው ተንቀሳቅሰው የፖለቲካ ሥራ ሊያሠራቸው ይቅርና እንደ ፓርቲ የአመራር አባላት ያለሥጋት ሊዘዋወሩበት የሚችሉበት ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ የፈቃደኘነት ወይም የቁም እስር ላይ ናቸው ቢባል ማጋነን አይመስለኝም ። እናም ያላቸው አማራጭ ከሞት አፋፍ የተመለሰው ኢህአዴግ እንደሥርዓት በቀጠለበት ሁኔታ የለውጥ አራማጅ በሚል አንድና ሁለት እያልን የምንቆጥራቸው መሪዎችን ቅን አስተሳሰብና አንዳንድ አበረታች እርምጃዎች ወደ ተፈላጊው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሊያሸጋግረን ይችል ይሆናል በሚል ተስፋ ማድረግ ነው ። ይህ አይነት አካሄድ እውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የማድረግ ልእልና እንዳለው ለመቀበል ቀርቶ ለመረዳትም በእጅጉ ይቸግራል ።
ለህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን የሲቭል ማህበራት መጠናከርና ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከቶውንም ችላ የሚባል ጉዳይ አይደለም ። የሙያ ማህበራት፣ የሠራተኛ ማህበራት ፣ የተማሪዎች ማህበራት ፣ የወጣቶች ማህበራት፣ የሴቶች ማህበራት፣ ወዘተ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ በተለይም ከ1960ዎቹ ወዲህ ወደግራም ይዘመሙ ወደ ቀኝ የነበራቸው ሚና እና ተፅዕኖ በእጅጉ የጎላ ነበር ። ታዲያ በዚህ እጅግ ወሳኝ የፖለቲካ ምእራፍ ወቅት እንኳን ተሳትፏቸውን ህልውናቸውንም የሚያረጋግጥ እንቅስቃሴ ለማየት ያለመቻላችን ጉዳይ ምን እንበለው? በእውነት ከተነጋገርን በዚህ የመደራጀት ልእልናን የግድ በሚለን ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎት፣ ጥቅም፣ ቅሬታ ፣ ሥጋት ፣ ወዘተ የሚገለፅባቸውን የሲቭል ማህበራት እንዴትነትና ወዴትነት ትርጉም ባለው ኦኳኋን ለማየት አለመቻል በብርቱ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው ።
ለማጠቃለል
በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ በር የማስከፈቱ ስኬት የሚያበረታታና ለተሟላ ስኬታማነቱ የሚያነሳሳ መሆኑ እውነት ነው። ይሁን እንጅ ለረጅም ዘመን ከተከማቸውና ከተወሳሰበው የፖለቲካ ታሪካችን እና አሁንም በብርቱ እየተፈታተኑን ካሉት ሁኔታዎች አንፃር የምነገኝበት የአስተሳሰብ ፣ የሞራልና የአደረጃጀት እውነታ ብርቱ የልእልና ጉድለት እንዳለበት ተቀብሎና ተረድቶ በጊዜ ተገቢውን ማድረግ ከክሽፈት ይታደጋል። የመሞጋገሱንም ሆነ የመተቻቸቱን አቀራረብና ይዘት ለመማማር እንዲሆን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ እንጅ የእራሳችን ከሆነው መሪር ሃቅ ዙሪያ አናሽከርክረው ። ምክንያቱም “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ነውና ። ምንም እንኳ ሰው የመሆን ባህሪያችን አብሮን ያለውን የራሳችን እውነታ በተለይ ደግሞ ከሃላፊነትና ተጠያቂነት ጋር የተያያዘ እውነትን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ በአግባቡ ለማስተናገድ ቢያስቸግረንም መልሶ እራሳችን እስኪጎዳን ድረስ መሄዱን ግን በፍፁም ልንታገሰው አይገባም ። አዎ! “ይዋል ይደር እንጅ እውነት ያሽንፋል እንደሚባለው የምንገኝበት የነፃነትና የፍትህ ፍለጋ ተጋድሎም እውነት ነውና አንደ ቀን ይሰምራል” በሚለው አጠቃላይ እውነት (general truth) እስማማለሁ ። ይህ ስለተባለ ግን በጊዜው ማድረግ የሚገባንን ሳናደርግ የህን አጠቃላይ እውነት የድክመት (የውድቀት) ማሳበቢያ (excuse) በማድረጉ ልማድ ግን ጨርሶ አልስማማም።